• Call Us
 • +251465512106

ባህላዊ የምግብ ዓይነቶች በዎላይታ

የምግብ ዓይነቶችና አሠራሮች እንደየአከባቢው ይለያያሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ የወላይታ ብሔር ባህላዊ የምግብ ዓይነቶችና አዘገጃጀቶቹን በአጭሩ ለማስቃኘት ይሞከራል፡፡

ወላይታዎች የሚመገቧቸው የምግብ ዓይነቶች በሁለት ይመደባሉ፡፡ የመጀመሪያውና አብዛኛውን ጊዜ ለእንግዳ፣ ለክብረ በዓላት፣ ለተለያዩ ድግሶች የሚሰናዱ ተወዳጅና የሚጥም ምግብ ወይም በብሔሩ ቋንቋ (ማልኦ ቁማ) ሲሆን ሁለተኛው ዘወትር የሚመገቧቸው እና ከበዓላት ቀን ውጭ በአዘቦት ቀን የሚሆኑ ምግቦችን (ማሱኳ ቁማ) የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህም የምግብ ዓይነቶች በየክፍላቸው ቀጥለን በዝርዝር እናያቸዋለን፡፡

 1. "ማልኦ ቁማ" ወይም ተወዳጅና የሚጥም ምግብ

ተወዳጅና የሚጥም ምግብ "ማልኦ ቁማ" ማለት በወላይታ ለተለያዩ ድግሶች ለሰርግ፣ ለግርዛት፣ ለክብር እንግዳ መቀበያ እና ለክብረ በዓላት ጊዜ የሚሰጥ የምግብ ዓይነቶች ናቸው፡፡

ይህ ተወዳጅና የሚጥም ምግብ የሚሰራው በአከባቢው ከሚገኙ ከተለያዩ ነገሮች ነው፡፡ እነዚህም፡-

 1. ከእንስሳት ተዋጽዎች
 2. ከእንስሳት ተዋጽዎች
 3. ከተለያዩ የእህል ዘሮችና
 4. ከሥራ ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡

 

 1. የእንስሳት ተዋጽዎች

የእንስሳት ተዋጽኦች ስንል ለምግብነት የምንጠቀማቸው እንስሳት በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የነዚህ ተዋጽዎች በሁለት እንከፍላለን፡፡

  • የሥጋ ተዋጽዎች
  • የወተት ተዋጽዎች ናቸው፡፡

  

የሥጋ ተዋጽዎች

     የሥጋ ተዋጾዎች አብዛኛውን ጊዜ ሥጋ ብቻውንና ከሌሎች እህሎች ጋራ ተቀላቅሎ ይዘጋጃሉ፡፡ እነዚህም

"ቶልሱዋ" (ጥሬ ሥጋ)፡- ከበሬ ሥጋ ምርጥ ብልቶች "ገዳ፣ ሻኛ"… ተብሎ በመስቀያ ላይ ወይም በብሔሩ ቋንቋ "ኮጫ" ላይ ተሰቅሎ አሊያም እንደ ሁኔታው በሰፌድ፣ በትሪ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከቁርጥ ሥጋ "ቶልሱዋ" ጋር በማባያነት የሚቀርቡት በስሱ የተጋገረ የበቆሎ እና የቆጮ ቂጣና "ዳታ" በርበሬ በሁለት መልክ ተዘጋጅቶ ይቀርባል፡፡ ይህ የሚሰራው አብዛኛውን ጊዜ ለ"ግፋታ" (ዓመት መለወጫ) በዓል ቀንና ለተለያዩ ድግሶች ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሌላው ቶልሱዋ ለዘመን መለወጫ ሲቀርብ "ሙቿ፣ ባጭራ" አብሮ ይቀርባል፡፡ እነዚህ ተጨማሪ ምግቦች ለሌላ ድግሶችና ክብረ በዓላት ላያስፈልጉ ይችላሉ፡፡

"ዳታ በርበሬ" በወላይታ በጣም ታዋቂና ለቁርጥ ሥጋ እንደ ማባያነት ተወዳጅ ሆኖ የሚቀርብ ነው፡፡ ዳታ በርበሬ አዘገጃጀቱ በሁለት ዓይነት ነው፡፡ በርበሬው በነጭ ሽንኩርትና ከሌሎች ቅመሞች ጋር ተድጦ ብቻውን ቅቤው በጣም ስለሚጨመርበት በቋንቋው በርበሬ ተብሎ ይዘጋጃል፡፡ ሁለተኛው በርበሬው ላይ ከቅቤ በተጨማሪ "ማንጣ" ወይም ከወተት አንጀት በሚወጣ ፈሳሽ አጣፍጠው የሚሰሩት ነው፡፡ ሁለት ዓይነት የሚዘጋጀው አብዛኛውን ጊዜ ለዓመት መለወጫ "ግፋታ" ጊዜ ነው፡፡

 1. "ሱልሷ"፡- ከበሬ ሥጋ ቀያዩ ብቻ ተመርጦ  በጣም ደቆ ከተከተፈ በኋላ በነጠረ ቅቤ ከተለያዩ ቅመሞች ጋር ተለውሶ የሚሰራ ሲሆን በበቆሎና በቆጮ ቂጣ ይበላል፡፡ ሱልሷ ለክብር እንግዳ እና ለተለያዩ ድግሶች ይሰራል፡፡
 2. ቆጩቆጩዋ፡- ይህ የምግብ ዓይነት  ከበሬ፣ ከበግ፣ ከፍየል ሥጋ ሊሰራ ይችላል፡፡ ቆጭቆጩዋ በሁለት መንገድ የሚሰራ ሲሆን አንደኛው ከሥጋ ብቻ ሲሰራ ሁለተኛው ደግሞ ሥጋ ከጎመን ጋር ይሠራል፡፡ በሥጋ ብቻ የሚሠራው እላይ ከተጠቀሱት ማንኛውም ሥጋ ሊሆን ይችላል፡፡ በእሳት ላይ በማሰሮ ላይ ይጣድና በመስበቂያ ይሰበቃል፤ ለረዥም ሰዓት ቅቤ፣ ነጭ ሽንኩርትና የተለያዩ ቅመሞች ተጨምሮ የሚሰራ ሲሆን ለእንግዳና ለተለያዩ ድግሶች ይዘጋጃል፡፡ ሁለተኛው የቆጭቆጮ አይነት እላይ ከተጠቀሱት ሥጋዎች የትኛውም ከጎመን ጋር እሳት ላይ ይጣድና ይበስላል፡፡ ከዚያም አውጥቶ በጣም አድቅቆ ከተከተፈ በኋላ ቅቤ፣ ቅመምና ነጭ ሽንኩርት ተጨምሮበት እሳት ላይ ሞቅ ተደርጎ ይወጣል፡፡ ሁለቱም በበቆሎና በቆጮ ቂጣ ይበላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ይህ አዘገጃጀት በዓመት መለወጫ ግፋታ በዓል በዋለበት ጊዜ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ቀን ቤተሰብ በሚበዛበት ቤት ይዘወተራል፡፡
 3. ኩቶ አሹዋ ፋቴታ (የዶሮ ስጋ ቆጭቆጮ)፡- አሠራሩ ዶሮ ይበለትና በደንብ ከታጠበ በኋላ በማሰሮ ይጣዳል፡፡ በመስበቂያ ለረዥም ሰዓት ይሰበቃል፡፡ በቅቤ ብቻ ስለሚበስል ስጋው በስሎ ከአጥነቱ ለብቻ ተለያይቶ ይወጣል፡፡ ነጭ ሽንኩርትና ቀይ ሽንኩርት ተድጦ ከተለያዩ ቅመሞች ጋር ይጨመራል፡፡ መብሰሉ ታይቶ አጥንቱ ለብቻ ይወጣና ቅቤ በብዛት ተጨምሮ በመስበቂያ ይሰብቅና ይወጣል፡፡ ይህ ምግብ አብዛኛውን ጊዜ ለታመሙ ሰዎችና ለአራሶች የሚሰራ ነው፡፡ ቅቤው ነጥሮ ለብቻ ስለሚወጣ ከላዩ ላይ ይጠጣል፤ የተቀረው እስከሳምንትም ሊሆን ይችላል፤ በማንኪያ ወይም በብሔሩ ቋንቋ "ሞቂያ" እየተወሰደ ይበላል፡፡

የወተት ተዋጾኦች

      የወተት ተዋጾዎች የምንላቸው ትኩስ ወተት፣ አሬራ፣ አይብና ቅቤ ናቸው፡፡ እነዚህንም አብዛኛውን ጊዜ "ለማልኦ ቁማ" ሥራ የምንጠቀማቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ ቅቤ በሁሉም የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ይጨመራል፡፡ በዚህ ክፍል ከአይብ የሚሰሩ ምግቦችንና አይነታቸውን በዝርዝር እናያለን፡፡

      አይብ ማለት አሬራ ወተት እሳት ዳር ተጥዶ የሚወጣ የምግብ አይነት ነው፡፡ ከአይብ አራት አይነት ምግብ ይሰራበታል፡፡ እነሱም፡-

 1. አይብ ብቻውን
 2. አይብ በጎመን
 3. አይብ በገብስ
 4. አይብ በሥጋ ናቸው፡፡
 1. አይብ ብቻውን፡- ማለት አይብ በቅቤና በቅመማ ቅመም የሚሠራ ነው፡፡ ይህም ለድንገተኛ እንግዳ እና ለቤተሰብ ይሠራል/ይበላል፡፡
 2. አይብ በጎመን፡- ጎመን በሚገባ ከበሰለ በኋላ ይከተፍና ከአይብ ጋር ተቀላቅሎ የተለያየ ቅመማ ቅመምና ቅቤ ተደርጎ የሚሠራ የምግብ ዓይነት ነው፡፡
 3. አይብ በገብስ፡- ገብሱ በሁለት ዓይነት ሊሰራ ይችላል፡፡ አንደኛው እንደ ቅንጨ ተደርጎ ሌላው በሰል ያለ ገብስ ተፈጭቶ ይሰራል፡፡ ቅንጨው ተቀቅሎ ይወጣና ከአይቡና ከቅመሙ ጋር የሚሰራ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ ክብረ በዓላት ጊዜ በርካታ ቤተሰብ ባለበት ቤት ውስጥ ይዘወተራል፡፡
 4. አይብ በሥጋ ፡- ሁለት የአሰራር አይነቶች አሉት፡፡ እነሱም፡-
  • አይብ በበሰለ ሥጋ "ሎጎሙዋ"
  • አይብ በጥሬ ሥጋና በጥሬ ቅቤ "ጉጉዋ"

"ሎጎሙዋ" (አይብ በበሰለ ሥጋ) - የምንለው ከሥጋዎቹ መሀል ምርጥ ቀይ ሥጋ ተመርጦ ይዘለዘልና ይበስላል፡፡ ከበሰለ በኋላ ደቀቅ ተደርጎ ይከተፋል፡፡ ከዚያም ቅቤና ቅመም ተጨምሮ ሥጋው እሳት ላይ ከተንተከተከ በኋላ ወጥቶ አይብ ይጨመርበታል፡፡ ይህ የሚሰራው አብዛኛውን ጊዜ ለሠርግ፣ ለመልስ፣ ለግርዛትና ዘመድ ቤት ለመውሰድ የሚሠራ የምግብ አይነት ነው፡፡

"ጉጉዋ" (አይብ በጥሬ ሥጋና በጥሬ ቅቤ) - ማለት ምርጥ ቀይ ሥጋ በጥሬው በሚገባ ተከትፎ ምንም እሳት ሳይነካው ከአይብ ጋር ይቀላቀላል፤ ቅቤውም በጥሬ ይጨመርበታል፡፤ ይህ የሚሰራው አብዛኛውን ጊዜ ለመድሓኒትነትና ለግንባታ ነው፡፡ ይሀው ምግብ  ለብርድ/ውጋት ለሚያማቸውና ለአራስ ሴቶች ይሰራል፡፡

2. የእንሰት ተዋጾዎች

      የእንሰት ተዋጾዎች "ማልኦ ቁማ"  ወይም ተወዳጅና የሚጥም ምግብ ከሚሰራባቸው ተዋጾዎች አንዱ ነው፡፡ የእንሰት ተዋጾዎች የምንላቸው እንሰቱ ከተፋቀ በኋላ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነሱም፡- እትማ፣ ጎዲያ እና ጎላ ናቸው፡፡ ከነዚህ የሚሰሩ የምግብ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ሙቿ፡- ከእትማ ወይም ከቡልኣ ይሰራል፡፡ ቡልኣ በምጣድ ተነኩሮ ይወጣና ትኩስ ወተት ይርከፈከፍበታል፡፡ ከዚያም በቅጠል ተደርጎ በመካከለኛ እንስራ ይቀቀልና ከበሰለ በኋላ በዋዲያት ተገልብጦ የተለያዩ ቅመሞችና የተነጠረ ቅቤ በብዛት በላዩ ላይ ይደረግና ተማስሎ ይቀርባል፡፡ ይህ ለተለያዩ ድግሶች ክብረ በዓላት እና ለተከበረ እንግዳም ይሰራል፡፡
 2. ባጭራ፡- የሚሰራው ከተመረጠ ቆጮ ወይም በብሔሩ ቋንቋ ጎዴታ ኡንጫ ከሚባለው ነው፡፡ ቆጮው በቃጫ እየተጠቀለለ ተጨምቆ ከደረቀ በኋላ በወንፊት ተነፍቶ በምጣድ እስኪበስል ይኖከርና ወተት ተርከፍክፎበት የተለያዩ ቅመሞችና ቅቤ ተጨምሮበት የሚሠራ የምግብ ዓይነት ነው፡፡
 3. "ሞኪ ውላ" (የቡልኣ ገንፎ)  የደረቀው ቡልኣ በውሃ ተበጥብጦ በፈላ ወተት ላይ ተጨምሮ ይሰራል፡፡ እየተሰራም ቅቤ ይጨመርበታል፣ ተሰርቶ ከወጣም በኋላ ቅቤ, የሚጨመርበት ሲሆን በበርበሬ ይበላል፡፡ ይኸው ምግብ ብዙን ጊዜ ለወላድ ሴት ይዘጋጃል፡፡

3.ከተለያዩ የእህል ዘሮች

 1. ፖሻሟ፡- ከበቆሎ እህል የሚዘጋጅ ሲሆን ነው፡፡ በቆሎ ብዙም ሳይበስል ታምሶና ተፈጭቶ በማሰሮ ትንሽ ወተት ተጨምሮ ከፈላ በኋላ ዱቄቱ ይጨመራል፡፡ መብሰሉና ውሃ መምጠጡ ታይቶ ይወጣና የተለያዩ ቅመሞችና ቅቤ በብዛት ተጨምሮ ይማሰላል፤ ከዛም ወጥቶ ይበላል፡፡ የሚሰራው ለክብር እንግዳና ለቤተሰብ ይሰራል፡፡
 2. ጉርዷ- ከገብስ የሚሰራ ነው፡፡ አሠራሩም ገብሱ ይፈተግና ታምሶ ይከካል፤ ከዛም በማሰሮ ይቀቀላል፤ ከበሰለ በኋላ ወጥቶ ቅመማ ቅመምና ቅቤ በብዛት ተጨምሮ ተማስሎ ይበላል፡፡ ለእንግዳና ለቤተሰብ የሚሰራ ምግብ ነው፡፡
 3. ባንጋ ቡራቷ- ከገብስ ቆሎ ይሰራል፡፡ አሰራሩም ጥሬው ገብስ በሚገባ ተፈትጎ በሰማ ምጣድ ይቆላል፡፤ ከዚያም ተደጋግሞ ይሸከሸካል፡፡ ገለባው በሚገባ ከወጣ በኋላ የተነጠረ ቅቤ ከተለያዩ ቅመምና ከተፈጨ ጨው ጋር ተደርጎ አንድ ላይ በማሸት የሚሰራ የምግብ አይነት ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለመንገደኛና ወደ አደንና ጦርነት ለሚሄዱ ሰዎች የሚዘጋጅ ነው፡፡
 4. ሸንዴራ (ገንፎ) ከተለያዩ የእህል ዘሮች ዱቄት ይሰራል፡፡ ከበቆሎ፣ ከገብስ፣ ከጤፍ ከማሽላ እንዲሁም ከቡልኣ ሊሰራ ይችላል፡፡  ደቆ የተፈጨ ከላይ ከተገለጹት አንዱ እህል በፈላ ውሃ እየተጨመረ ለረዥም ሰዓት ይማሰላል፡፡ ከዚያም እንደበሰለ ይወጣና ከተነጠረ ቅቤ ከተለወሰ በርበሬ ጋር ይበላል፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት እህሎች አንዱ በወተት እና ቅቤ ብቻ ከተሰራ በብሔሩ ቋንቋ "ኤሬታ" ይባላል፡፡ ይህ ዘመዷ ለአራስ የምትሰራላት የምግብ ዓይነት ነው፡፡
 5. ቡንቼታ (ጨጨብሳ)ከበቆሎ፣ ከማሽላ፣ ከጤፍ የተጋገረ ቂጣ በዋዲያት ተፈርፍሮ ቅቤ በብዛት እና ቅመም ተጨምሮበት የሚዘጋጅ ሲሆን ለድንገተኛ እንግዳ የሚቀርብ ምግብ ነው፡፡

4. የሥራ ሥር ምግቦች

አብዛኛው ጊዜ የሥራ ሥር ምግቦች ለማሱካ ወይም ዘወትር የሚበሉ ምግቦች ቢሆኑም "ለማልኦ ቁማ" ወይም ለተወዳጅ ምግብነትም የሚያገለግሉ፡፡ እነሱም፡-

 1. ፕጫታ፡- ከ"ቦየ" (ወጭኖ) የሚዘጋጅ ምግብ ሲሆን በሚገባ ታጥቦና ተፍቆ ይቀቀላል፡፡ ቀጥሎ የበሰለው በዋዲያት ተከትክቶ ቅመማ ቅመም ተጨምሮበት ለተከበረ እንግዳ ወይም ለቤተሰብና አልፎ አልፎም ለግፋታ ወይም አመት መለወጫ ቀን በ"ቆሬ ብርሸታ"ነት ይቀርባል፡፡
 2. ጫድያ፡- ከቦይና (ጎዳሬ) ይሰራል፡፡ ይህም ቦይና (ጎዳሬው)  ----------- ተፍቆ እሳት ላይ ይበስላል፡፡ ቀጥሎም ነጭ ነጩ ተለቅሞ ይከተከታል፡፤ ዳታ በርበሬ በቅቤ በሚገባ ተዘጋጅቶ የሚበላ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በቤተሰብ ደረጃ የሚበላ እና ለአራስ ሴትም ይቀርባል፡፡

2. "ማሱካ ቁማ" (በአዘቦት ቀን የሚዘወተሩ ምግቦች)

"ማሱካ ቁማ" ማለት አብዛኛውን ጊዜ ተዘውትሮ የሚመገቧቸውና የተለመዱ ምግቦች እንደማለት ነው፡፡ እነዚህ "ማሱካ ቁማ" ወይም በአዘቦት ቀን የሚመገቧቸው የዘውትር ምግቦች ሲሆኑ የሚጋገሩ፣ የሚቀቀሉ እና የሚቆሉ ተብሎ በሶስት ከፍለን እናያቸዋልን፡፡

የሚጋገሩ የምንላቸው አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ እህሎች ተፈጭተው የሚጋገሩትን (oyitta) ያጠቃልላል፡፡ የሚቀቀሉ ቦዬ፣ ቦይና፣ ሹካሪያ፣ ድንች፣ ኮካ የመሳሰሉት ሲሆኑ ሶስተኛው ተቆልቶ የሚበሉ ናቸው፡፡ ከጤፍ ውጭ በማንኛውም እህል በጥሬው ተቆልቶ ይበላል፡፡ እነዚህ በአጠቃላይ በማንኛውም ሰው ቤት በአዘቦት ቀን የምናገኛቸው ምግቦች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በወላይታ ባህላዊ የምግብ አይነቶችንና አዘገጃጀቱን ከሞላ ጎደል ለመጥቀስ ተሞክሯል፡፡ ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት የምግብ ዓይነቶች በተጨማሪ ሌሎችን የምግብ ዓይነቶች አንዱን የምግብ ዓይነት ከሌላው ጋር በማቀላቀል እጅግ በጣም ብዙ የምግብ አይነቶች ሊሰሩ እንደሚችሉ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡

እነዚህ ባህላዊ ምግቦች በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ እድገት ምክንያት እየቀሩ ያሉ የምግብ ዓይነቶች በሳይንሳዊ አመጋገብ ዘዴ በመታገዝ ምርምር ማካሄድና በጽሑፍ በማስቀመጥ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ቢደረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለን እናምናለን፡፡