• Call Us
 • +251465512106

ባህላዊ የለቅሶ ሥርዓት በወላይታ

ደስታና ሐዘን የሰው ልጅ የሕይወት ገጽታዎች ሲሆኑ ገጽታዎቹ ከሥፍራ ሥፍራ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነት ይስተዋልባቸዋል፡፡

      የወላይታ ብሔር ሀዘን የሚገልጽባቸው የተለያዩ የለቅሶ ሥርዓት ሂደቶችና አውዶች  አሉት፡፡ እነዚህም፡- ቃሬታ (Qaretaa)፣ ባሊያ(baliyaa)፣ ፒቱዋ (pituwaa) እና ጋባ (gaabaa) ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ለባህላዊ ለቅሶ ሥርዓት አፈጻጸም የሚያስፈልጉትን የሙዚቃ መሣሪያዎችና አልባሳት የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ቃሬታ፡- አንድ ሰው በሞት እንደተለየ የአከባቢውም ሆነ የሩቅ ሰው ወዲያው መጥተው ድንጋጤአቸውንና ሐዘናቸውን የሚገልጹበት ሥርዓት ነው፡፡ በሂደቱ የሟች የቅርብ 3ቤተዘመዶች እራሳቸውን ይጎዳሉ ተብሎ ስለሚገመት በሰዎች ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል፡፡ በዕለቱ ለቀብሩ ቅድመ ዝግጅት ውይይት እና ተያያዥ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡  ለቤተዘመድ፣ ለአማች ቤት፣ ለጃላ ቤት መልዕክተኛ ይላካል፤ በተጨማሪም ለባሊያ ቀን ቤተዘመድ ቆሞ የሚያለቅሱበት ዳስ ወይም ድንኳን ይጣላል፡፡ በመጨረሻም ቀኑ ከታወቀ በኋላ ሟቹ ታዋቂ ከሆነ ታላቅነቱና ጀብዱ እየተገለጸ በገበያ ውስጥ ኤኬሌ ሞቷልና ቀብሩ ቀን በዚህ ቀን ይውላል በማለት በፈረስ እየዞሩ  ያውጃሉ፡፡ ለቀብሩ ዋዜማ ማታ ላይ ሰዎች በቡድን በቡድን ሆነው የሚያዘሙ ሲሆን ይህም የሀዘን እንጉርጉሮ “ኮይዜታ” ይባላል፡፡
 2.  ባሊያ፡- ባሊያ በነባሩ ባህል የባሊያ እና የቀብር ሥርዓት በተመሳሳይ (በአንድ) ቀን የሚፈጸም ሁኔታው በሂደት እየተለወጠ መጥቷል፡፡ በወላይታ ይህን ስንል ቀብሩ በሶስተኛ ቀን ተፈጽሞ ዘመድ አዝማድ ወይም ቤተሰብ ሩቅ ያለው ሰው ከሆነ ቤተሰቡ በተስማማበት ቀን ሊውል ይችላል፡፡ በቃሬታ ሥርዓት የተገኙም ቢሆን በባሊያ ሥርዓት ደግሞ እንዲገኙ በበህሉ ይፈለጋል፡፡ በባሊያ ሥርዓት በሚገኙ በርካታ የሀዘን ተካፋዮች ሳቢያ በሚፈጠረው ግፊያ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት የሟች ዘመዶች ከግቢ ውጭ አጥር አጠገብ በተጣለ ድንኳን መከታ በእንጨት እንደ አጥር ከፊለፊታቸው ላይ ተደርጎላቸው በዳስ ወይም ጥላ ሥር ሆነው ያለቅሳሉ፡፡  የባሊያ ለቀስተኞች ዳስ ውስጥ ወዳሉ የሟች ዘመዶች  በፈረስም ሆነ በእግር ሦስት ጊዜ በኃዘን እንጉርጉሮ (buttuluwaa) እየተመላለሱ ሀዘናቸውን  (alliyogaa) “አዬ… አዬ” እያሉ ኃዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡

በነባሩ ባህል እንደቅርበታቸው በፈረስ ላይ ኃዘንተኞች ራሳቸውን በአለንጋ ሲገርፉ፣ እግረኞች በመፍረጥ (hirxxiya) እየወደቁ ኃዘናቸውን የሚገልጹ ሲሆን ሴቶች  (shaashshaa) “ሻሻ” የሚባል ሳር እና በቆንጥር ፊታቸውን እየቧጨሩ፣ ፈረሰኞች፣ እግረኛ ወንዶችና ሴቶች በመሆን በቅደም ተከተል እየተመላለሱ ያለቅሳሉ፡፡ የባሊያ ተሳታፊዎች አስክሬኑ ከተቀበረ በኋላ ነው ምግብ የሚመገቡት፡፡ በባህሉ አስክሬን ሳይቀበር ለቀስተኛ ምግብ አይመገብምና፡፡ በዚህን ወቅት ሟቹ በአከባቢው ነዋሪ ከሆነ   በቤተዘመድ የቀብር ቦታ “በመካና” ይቀበራል፡፡ ሟቹ ከሌላ አከባቢ በሥራ ምክንያት ወይም በሌላ የመጣ ከሆነ  “በጉታራ” ይቀበራል፡፡

      ከቀብር መልስ ለአማች፣ ለቤተዘመድ፣ ለጃላና ለአጃቢዎቻቸው አስከትለው የሟች እድሮችና ጎረቤቶች መስተንግዶ ያደርጋሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ንፍሮ፣ ቂጣ፣ በቅጠል ቡና እና በፍሬ ቡና መስተንግዶ የሚደረግ ሲሆን ሟቹና ቤተሰቡ ታዋቂ ከሆነ በሬ ታርዶ የስጋ መስተንግዶ ይደረጋል፡፡ ለቀስተኞች እንደየቅርበታቸው ለሟች ቤተሰብ የጭነት እህል (caanaa) ወይም ብር (yessaa) በማስተዛዘኛነት (ለማጽናኛነት) ይሰጣሉ፡፡ ከዚያም በኋላ “Hayquwa haysse otto” እያሉ መርቀው ይሄዳሉ፡፡ ማለትም ሞት እይንካችሁ፤ ዳግም አይምጣባችሁ ብለው መርቀው ይሄዳሉ፡፡

 

 1. Pittuwa (ጠረጋው ቀን)

pittuwa (ጠረጋው ቀን)፡- ሥርዓቱ ከባሊያ ፍጻሜ በኋላ ለወንድ አራተኛ ቀን ለሴት ሦስተኛ ቀን የሚደረግ ሥነ-ሥርዓት ሲሆን በዕለቱ የሟች ቤተሰብ ዕድርተኞ የሚሰበሰቡ ሲሆን በሂደቱ ሴቶች የሟቹን ቤትና ግቢ ያጸዳሉ፡፡ ወንዶች ደግሞ ለቀብር ቀን የተሠራ ዳስ (ድንኳን) የሚያነሱ ሲሆን ሴቶች ከየቤታቸው ያመጡትን  ቆጮ፣ ንፍሮ፣ ቂጣ፣ እንጀራ፣ ቡና በማስተናገድ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

    “Gaabaa” (ማሳረጊያ)

      “ጋባ” (ማሳረጊያ)፡- በባህሉ ከባሊያ አራት ቀን በኋላ ረዥም ቀጭን ለጋ እንጨት ተቆርጦ ይላጥና በሟች ቤተሰብ በራፍ ላይ ይደረጋል፡፡ ለቅሶው ይቁም ለቀስተኛ (ኃዘንተኛ) አይምጣ የቤቱም አያልቅስ እንደማለት ነው፡፡

ከባሊያ ፍጻሚ አራት ቀን በኋላ የሟች ቤተሰብ እንዳያዝን ቢከለከሉም እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሀዘንተኛ እንደሆኑ የሟች ቤተዘመድ ሴቶች ፀጉራቸውን ሳይላጩ ወንዶች ሳይቆረጡ፣ ወደ መዝናኛ ሥፍራዎች አይሄዱም፤ ገበያም አይወጡም፡፡ ሟች የሞተው በክብር በዓላት ጊዜ ከሆነ ክብረ በዓሉን በኃዘን ያሳልፋሉ፡፡ ለበዓሉ ጎረቤት ከየቤታቸው አምጥተው ያበላሉ እንጂ ቤተሰቡ አያርድም፡፡

የሐዘን እንጉርጉሮ (Buuttuluwaa)

      በባህሉ ለሟቹ መታሰቢያ የሀዘን እንጉርጉሮ (Buuttuluwaa) በጾታ፣ በዕድሜ እና ለአከባቢው ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን ይለያያል፡፡

ወጣት ሴት ከሞተች

ቴሬና ቃውኤ

       Teerenna qa’uea

    Yelaga mulssee… እያሉ የልጅቱን ወጣትነትና ገና መሆኑዋን እየገለጹ በዜማ ያለቅሳሉ፡፡

 • እመጫት ከሞተች

Makki makki naagiyore neyyoo… yeeho

Maana wodiyan aggiyaare neyyo yeeho

ትርጉሙ፡- ተሰናድቶ የሚጠብቅሽን ሳትቋደሽ የሞትሽብን እያሉ በመሪሪ ሐዘን ያለቅሳሉ፡፡

 • ሟች ሀብታም ከሆነች

Godiya goojjaamiya lil’iyaaro

Lil’aa lil’ada ayiyaaro

Godiya goojjaamiya lil’iyaaro

 • ባልቴት ከሞተች

Balttette bayiree

Goojjaame lill’ee

ትርጓሜውም የባልቴቶች ሁሉ ታላቅ….”

 • ሟች የጀግና ሚስት ከሆነች

Olawu odolchchaa kooriyaaro

Banggaa buraatuwa shinqqiyaro

Ojonchcha gassa gochchiyaro ጀግናው ለጦርነት ሲሄድና ሲመጣ የምታደርግለትን የተባባሪነትና የተሳታፊነት ሚናዋን ይገልጻሉ፡፡

 1. ሟች ወንድ ከሆነ የሀዘን እንጉርጉሮው (ቡተቱሉዋ))እንደ ሟች ዕድሜ እና ለአከባቢው ባበረከተው አስተዋጽኦ መጠን ይለያያል፡፡
  • ሟች ወጣት ወንድ ከሆነ

Onakko nayi xinqqay meqiis

Onakko nayi woyishshay woddiis

 • ጓደኛ ሲሞት

Ayye laggee aayye laggee

Aayye miyyee aayye miyyee

  ዋይ ጓደኛ ዋይ ወገን እንደማለት ነው፡፡

 • ሟች አስተዳዳሪ (Daannaa) ከሆነ

Dabaabawu daaddaara

Allagawu ayifiyara

 • ጀግና ከሞተ

Onakko nay daama gaammoy

Daama gaammoy bazzo hasoy

የእገሌ ልጅ እምቦሶ .. የእገሌ ልጅ ዘንዶ እያሉ ጉብዝናውን ይገልጻሉ፡፡

 

 • ጠላትን የገደለ “ወራቲያ” ከሆነ

Ho solo … ዜማ አዝማቹ (ተቀባዩ የሟች ግዳይ እየገለጸ ጀግንነቱን በመዘከር ያለቅሳላቸዋል፡፡

 • አዛውንት (ሽማግሌ) ከሞተ

Tobbe ba kombbee ba

Zaallay za’iis wolay woddiis.… አማካሪያችንን ነጠቀብን፤ አለታችን ተሰነጠቀ--- ወደቀ እያሉ የቅርስነት ፋይዳውን እየገለጹ ያለቅሳሉ፡፡

 • ሟች ባህላዊ ሹማምንት ሐረግ ከሆነ

Deriyappe deexuwa nawu

Kawaappe kaaluwa na’awu

የንጉሥ ታናሽ ልጅ እያሉ ስልጣኑን እያሞካሹ ያለቅሳሉ፡፡

 • ሟች የተማረ  ከሆነ

Erawu Eessawu koottay me’iis.

Garuwawun garxxiya xam’’ay

የእውቀት ባለቤት ተሰበረ፣ ለሩቅ የምንልከው ሰው አጣን እንደማለት ነው፡፡

 • ሀብታም ወይም “Liqqa” (መቶ እና ከመቶ በላይ ከብት ያረባ)

Miizzaa deegaraa daaliyaga

Biraa miilooniya shiishshiya

 • ህፃን ልጅ ከሞተ

Aayye galddee

Aayye mulssee

      የሀዘን እንጉርጉሮዎቹ ወንድ ለቀስተኞች በሁለት ተከፋፍለው የሚያንጎራጉሩት ሲሆን ለባሊያ ድምቀት ይሰጣሉ፤ የሟቹን ገድሎችና አስተዋጽኦ በማስታወስ ልዩ የሀዘን ድባብ ይፈጥራሉ፡፡    ሌላው ደግሞ ጭቃሹም ከሞተ አስክሬኑ ሲነሳ የሚዘመው

     Hoo hosttagesaallagee

      Dannattee darottette.  ያባልለታል፡፡

 በለቀስተኞቹ (Buttuluwaa) በቡድን የሚዜም ሲሆን በባህሉ የሟች ቤተዘመዶች የሟቹን ውሎ፣ ገድል፣ አስተዋጽኦ፣ ቁመና፣ የዘር ሐረግ … በዜማዊ ቅላጼ (zilaassaa) እያንጎራጎሩ ሐዘናቸውን ይገልጻሉ፡፡

      በለቅሶው ወቅት የለቅሶ አውድ የሟች ቤተዘመዶች ልብሳቸውን ገልብጠው ይለብሳሉ፡፡

የቤቱ አባወራ ከሞተ ሚስት የሟቹን ሱሪ ወደ ትከሻዋ ጣል ታደርጋለች፣ እህት፣ አክስት፣ እና የልጅ ሚስት ካሉ በነጠላቸው ላይ “ዋሩዋ” (ማቅ) ይደርባሉ፡፡ ሟች በጦርነትና በአደን ጊዜ ጀብድ ግዳይ የጣለ ከሆነ የሟች ባለቤትና ዘመዶች      “baalliya” በጸጉራቸው ይሰካሉ፡፡

      የጦር መሪ ከሞተ ለቅሶውን የሚያደምቁ ቀረርቶ የሚችሉ ሁለት ሰዎች የአንበሳ፣ የነብር ቆዳና ድንጉዛ (ሀዲያ) ደርበው ጎፈር በራሳቸው በመድፋና አድርገው keexaa woykko guchchiya ላባ አጊጤው በቀረርቶ መልክ ሙሾ እያወረዱ ያለቅሳሉ፡፡

      ሟች ጀግና ከሆነ ፈረስ በጌጤኛ አልባሳትና ጌጣጌጦች  ተውቦ በጭንቅላቱ ሁለት ላባዎች ሰክተውለት ፈረሱ ላይ በመሆንና ጦር በመያዝ የሟቹን ጀግንነት ይዘክራሉ፡፡

      ሟች ባህላዊ ዳኛ ወይም ሹም ከሆነ በዳኝነቱ ጊዜ ወይም በሹመቱ ጊዜ ያገኛቸውን ካባዎች ልጆቹ አልያም ወንድሞቹ አሊያም የቅርብ ዘመዶቹ ይደርባሉ፡፡ በወቅቱ የአለባበስ ሥርዓቶች ሟቹን ከመዘከር ጎን ለጎን ለለቅሶ ስርዓቱ ጉልህ ድምቀት ይሰጣሉ፡፡

የባህላዊ ለቅሶ አውድ የሙዚቃ መሳሪያዎች

      ለወላይታ የለቅሶ ስነ ስርዓት “ባሊያ” ወይም ቀብር ቀን የሚደረጉ buttuluwaa እና zilassaa ማጀቢያ የምትና የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህም

 1. ካምባ፣ ካራቢያ (addiyanne inddiya) ትልቁና ትንሹ ከበሮዎች የሚባሉ ሲሆን እነዚህ በቅንጅት ይመታሉ፡፡
 2. “ጫቻ ዛይያ”፡- በትንፋሽ ከሚጫወቱት መሣሪያዎች መካከል የተለመደ ሲሆን እነሱም “ማራ፣ ጊዷ እና ሄስያ” በመባል ይታወቃሉ፡፡
 3. ዲንኪያ፡- በትንፋሽ የሚነፋ የሙዚቃ መሣሪያ ሲሆን አጨዋወቱም ሟች  ወንድ ከሆነ እስከ አራት ቀን ሴት ከሆነች ደግሞ እስከ ሦስት ቀን ይዘልቃል፡፡ እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች ለለቅሶ ውበት እንዲኖረው ወሳኝ ሚና ያላቸው ሲሆን አጨዋወታቸው በራሳቸው ባለሙያ ይፈጸማል፡፡ የሙዚቃ መሳሪያዎቹ ዜማ ለማያውቅ ሰው የደስታ አውድ ጣዕም ይምሰል እንጂ ለሚያውቅ ግን ልዩ የሐዘን ስሜት ይፈጥራል፡፡
 4. ደርቢያ (Darbbiya)

በወላይታ ብሔር በባህላዊ ወግና ስርዓት የሚደረገው የለቅሶ ስርዓቶች በጊዜ ሂደት እየከሰሙ ስለመጡ በጽሑፍና በምስል ተቀርጸው ቢቀመጡ ቀጣዩ ትውልድ የራሱን ባህልና ቅርስ እንደይረሳ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል እንላለን፡፡