• Call Us
  • +251465512106

ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ

     ሙዚቃ የአንድ ሀገር ሕዝብ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ባህሉን፣ መልካም ገጽታውንና የሕይወት ፍልስፍናውን በቀላሉ የሚያስተዋውቅበት ዓይነተኛ መሣሪያ ከመሆኑም በላይ የዓለም ሕዝብ ቋንቋ እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ የወላይታ ብሔር ባህላዊ ሙዚቃም ይህንን በእጅጉ ያስተጋባል፡፡ የብሔሩ ባህላዊ ሙዚቃ (cultural music) ሙሉ ሙዚቃ ነው እንዲባል አራት ዋና ዋና ነገሮችን ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ እነዚህም የሙዚቃ ግጥም፣ ዜማ፣ ድምጽና የሙዚቃ መሣሪያ ናቸው፡፡ እነዚህነ ለሙዚቃው የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ በዚህ ዙር መጽሔት መተንተን ስለማይቻል ለዛሬው በባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡

      በወላይታ ውስጥ ሕብረተሰቡ የሚጠቀምባቸው በርካታ የሙዚቃ መሣሪያዎች አሉ፡፡ እነሱም በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች የሚመደቡ ሲሆን ዓይነቶቻቸውም፡-

  1. የምት፣
  2. የትንፋሽ እና
  3. የግርፍ ሙዚቃ መሣሪያዎች በመባል ይታወቃሉ፡፡
  1. የምት ሙዚቃ መሣሪያ ዓይነቶች

እነዚህ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ዓይነቶች በእጅ ወይም በአጭር ብትር እየተቀኙ ድምጽ የሚሰጡ ሲሆን በአሠራራቸው፣ ለአገልግሎት በሚውሉበት አውድ እና ከአሰላለፋቸው አንፃር እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡

ዳርቢያ (Darbbiya)

      በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው ይህ የምት ሙዚቃ መሣሪያ በትልቅ ጋን ቅርጽ ከጭቃ የሚሰራ ሲሆን በለሰለሰ ቆዳ ወይም ምቹ በሆነ ጨርቅ ውጥር ተደርጎ በጋኑ አፍ በኩል ይታሠራል፡፡ ቁመቱ አንድ ሜትር ያህል የሆነው ይህ መሣሪያ በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ከመቀመጫቸው ሳይነሱ የሚጫወቱት ሲሆን ይመቱታል፡፡ ለአገልግሎት የሚውለው በአዋቂ ሰው የለቅሶ ስነስርዓት ላይ ብቻ ነው፡፡

ናግሪታ

ናግሪታ የሚሰራው ከዋንዛ እንጨት ውስጡ ተቦርቡሮ ነው፡፡ ጠንከር ያለና ከፍተኛ ድምጽ እንዲሰጥ ሲባል ከበሬ ግንባር ቆዳ በሁለቱም በኩል ተወጥሮ በባለሙያ ይሰራል፡፡ የመሳሪያው ቁመት 1.20 ሜትር ሲሆን ስፋቱ ከላይ ½ ሜትር ሲሆን ከታች ደግሞ ¼  ስኩዌር ሜትር ነው በቅርጹ ከላይ ሰፋ ብሎ ከታች ደግሞ ሾጠጥ ይላል፡፡

ናግሪታ ከዚህ ቀደም በባህላዊ አምልኮ ስርዓት ወቅት እና በንጉሱ ትዕዛዝ ለሚከናወኑ የተለያዩ ተግባራት ማሳወጃ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ በወላይታ ውስጥ ከሚገኙ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የ"ቃልቻ" ጎሣ ባህላዊ አምልኮ ሥርዓት በሚፈጸምበት ወቅት እና በወላይታ ዘመን መለወጫ ግፋታ በዓል ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በአግልግሎት ላይ ይውል ነበረ፡፡

በንጉሡ ዘንድ የሚተላለፍ ሕዝባዊ መልዕክት ሲኖር እንደማሳወጃ ስለሚቆጠር ሕዝቡ በንቃት ይከታተለው ነበር፡፡ ለምሳሌ­፡- በንጉሡ አደባባይ (garuwaa) ናግሪታ ሶስት ጊዜ በተከታታይ ከተጎሠመ ከንጉሡ ቤት ሰው እንደሞተ መግለጫ በመሆኑ ሕዝብ ሁሉ ከያለበት ስፍራ ወጥቶ እንዲያለቅስና የሐዘን ስነ-ሥርዓቱን እንዲፈጽም ማወጃ ነበር፡፡ በንጉሱ አደባባይ ናግሪታ አራት ጊዜ በተከታታይ ከተጎሰመ የሹመት ስርዓት፣ የድል ብሥራት፣ የሠርግና የክብር በዓላት ማብሰሪያ በመሆኑ ሕዝቡ ወደአደባባይ በመሰብሰብ የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑ ይደረግ ነበር፡፡ በንጉሡ አደባባይ (garuwaa) ናግሪታ አምስት ጊዜ በተከታታይ ከተጎሰመ የውጊያ ጥሪ መሆኑን ሕዝቡ ይረዳና በአፋጣኝ ወደአደባባይ በመሰብሰብ ለውጊያ ይዘጋጃል፡፡

ናግሪታ ከሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎች ጋር ሳይቀናጅ ለብቻው ይመታል፡፡ ጎሳሚውን የሚያጅቡ ቢያንስ አራት ሰዎች በእያንዳንዱ ክንውን ላይ ይኖራሉ፡፡ በደስታ ጊዜ በጭፈራ ታጅቦ፣ በሐዘን ጊዜ የሐዘን እንጉርጉሮ እና በጦርነት ጊዜ ፉከራና ሽለላ የሚያሰሙ አጃቢዎች ከናግሪታ ጎሳሚው ጋር አብረው ይሰለፋሉ፡፡

ካምባ

     ይህ የወላይታ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ቁመቱ አንድ ነጥብ አምስት ሜትር ከሆነ የዋንዛ ግንድ ውስጡ ተቦርቡሮ ከደረቀ በኋላ በሁለቱም በኩል በኮርማ በሬ ቆዳ ይሸፈናል፡፡ ጠንከር ብሎ እንዲወጠር በጠፍር ይታሰርና በኮርማ በሬ ቆዳ ይሸፈናል፡፡ ጠንካራና ጥሩ ቃና ያለው ድምጽ እንዲያሰማ በአንድ በኩል ክብ ቀዳዳ መሐሉ ላይ ይበጃል፡፡

      ሕብረተሰቡ ይህን የሙዚቃ መሣሪያ የሚጠቀመው በትላልቅ መንግስታዊና ሕዝባዊ ክብረ በዓላት ላይ እና በአዋቂ ሰዎች ለቅሶ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው፡፡ ካምባ ሁልጊዜ ከጫቻ ዛዬ፣ ከትንሷ ከበሮ (indde karaabe) እና ከኡልዱዱዋ ጋራ የሚቀናጅ ሲሆን የሚጫወቱት ግለሰቦች መሣሪያውን ለመሸከም አቅም ያላቸው ወንዶች ብቻ ናቸው፡፡

ካራቢያ (Karaabiyaa)

      ይህ የሙዚቃ መሣሪያ መለስተኛ የሸክላ ድስት አፉ በቆዳ ተወጥሮ ይጠፈርና ይታሰራል፡፡ የድምጹ አወጣጥ እንደ ካምባ ሆኖ መጠኑ ዝቅ ይላል፡፡

      ካራቢያ ከመጠኑና ከሚሰጠው ድምጽ አንጻር በሁለት ዓይነት ስያሜ አለው፡፡ ተለቅ ያለው "አዴ ካራቤ" ተብሎ ሌላኛው መጠኑ አነስ ያለው "እንዴ  ካራቤ"  የሚል ስያሜ አለው፡፡ ሁለቱም የሙዚቃ ስልተ ምት በጠበቀ መልክ ተቀናጅተው በሚጫወቱበት ጊዜ ስሜትን የሚኮረኩር ማራኪ ጣዕመ ዜማን ይፈጥራሉ፡፡

      ካራቢያ በወላይታ ዘመን መለወጫ  "ግፋታ" በዓል፣ በሠርግና ግርዘት ሥርዓት ወቅትና ሕዝባዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት በሚከበሩበት አውድ ላይ ከሌሎች ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ተቀናጅተው ዝግጅቱን ያደምቃል፡፡

የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ ዓይነቶች

      የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች እየተነፉ የተለያየ ዜማ የሚሰጡ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ዓይነቶች ሲሆኑ ከሚሰሩበት ቁሳቁስ፣ ቅርጾቻው እና ለአገልግሎት ከሚውሉበት አውድ አንጻር ይለያያሉ፡፡ የወላይታ ሕዝብ በባህሉ የሚጠቀምባቸው የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዲንኪያ

     ይህ የትንፋሽ መሣሪያ በርዝመቱ እስካሁን በዓለም ተወዳዳሪ እንዳልተገኘለት ይነገራል፡፡ መሣሪያው የሚሰራው ከ3-4 ሜትር ርዝመት ካለው ቀርከሃ እና ከአጋዘን ቀንድ ነው፡፡

      ከመጠንና ከድምጽ አወጣጥ ደረጃ አንጻር በውስጡ ስድስት የድንኬ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነሱም፡-

  1. ዞሃ (zoohaa)
  2. ላምያ (lamiyaa)
  3. ሄስያ (Heesiyaa)
  4. ኩብያ (kubbiyaa)
  5. ማራ (maraa) እና
  6. ጫቻ (Cachchaa)

እነዚህ ስድስቱን ከአንድ ካምባ (kambbaa) ጋር አቀናጅተው ሲጫወቱት የሚሰማው የሙዚቃ ቅንብር ስሜትን የመመሰጥ ኃይል አለው፡፡

ዲንኪያ ተራ ማሕበራዊ አውዶች ላይ አይቀርብም፡፡ ከዓይነቶቹ በተለይ ዞሃ (zoohaa) የሚባለው ነገስታት ከፍተኛ የሹመት ሥነ-ሥርዓት በሚፈጸሙበት ወቅት፣ በታላላቅ ሕዝባዊና መንግስታዊ ክብረ በዓላት ላይ እና ታዋቂ ሰዎች የለቅሶ ሥነ-ሥርዓት ይነፋል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያውን ለመሸከምም ሆነ ለመንፋት አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ፈርጠም ያሉ ጎልማሶች ይመረጣሉ፡፡

ጫቻ ዛዬ (Cacha zayye)

ይህ ሙዚቃ መሣሪያ በሙዚቃ ባህሪው በጣም ተወዳጅና ታዋቂ የሚያደርግ ቅኝት አለው፡፡ የሙዚቃ መሣሪያው የሚሰራው  "እርወይሻ" (ሰንበለጥ ውስጥ የሚበቅል ለስላሣ እንጨት መሰል ሆኖ ውስጡ እንደሸምበቆ እጽዋት ከዋናው)፣ ከማሽላ አገዳ፣ ከሲጢነታ ልፋጭነት ባህሪ ካለው የስጋ ዓይነት እና ከዋንዛ እንጨት ይሰራል፡፡

      ጫቻ ዛዬ ስልጡን በሆኑ ተጨዋቾች እየተቀናበረ ሲቀርብ እንኳን የብሔሩን ተወላጅ ይቅርና ስለሙዚቃውና ስለወላይታ ባህል የማያውቅ ሁሉ ሳይቀር በተቀመጡበት ከማወዛወዝ አስነስቶ የሚያስጨፍር ድንቅና ማራኪ ጣዕም አለው፡፡ ይህ የሙዚቃ መሣሪያ በሠርግ፣ በግርዘት፣ በባህላዊ ክብረ በዓል ወቅት ይነፋል፡፡ ስምንቱን የሙዚቃ ቅኝት (octatonic rhythm) ለመቃኘት ጉልህ ሚና የሚጫወተው ይህ መሣሪያ ከካምባ እና ከካራቢያ በመቀናጀት በአብዛኛው ይቀርባል፡፡

      የጫቻ ዛዬ አይነቶች(ዘሮች) ከመጠናቸውና ከሚያሰሙት የዜማ ስልት አንጻር በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡

እነሱም፡

  1. ዞሃ (zoohaa)
  2. ማራ (maraa)
  3. ግዷ(gidduwaa)

በጫቻ ዛዬ የአነፋፍ ስልት መሰረት የሚከተሉት ስድስት ዓይነት የሙዚቃ ቅኝት መስራት እንደሚቻል ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

  1. ቶቲያ (tootiyaa)
  2. ሄቸቺያ (hechchiyaa)
  3. ስልዷ (sildduwaa)
  4. ኮይሻቷ (koyishattuwaa)
  5. ጎሻ (Gooshaa)
  6. ድርባ (Dirbbaa)

 

እምቢልታ

ይህ ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ ርዝመቱ 75 ሳ.ሜ ከሆነ ጠንካራ ሸምበቆ የሚዘጋጅ ሲሆን በላዩ ላይ "ሲጢነታ" (የልፋጭነትና የተለጣጭነት ባህሪ ያለው ሥጋ) በመደረብ ለመንፋት በሚያመች መልኩ በአንድ በኩል በማሳጠርና በሌላው በኩል ረዘም እንዲል በማድረግ ይሰራል፡፡ ሶስት እምቢልታዎች አንድ ላይ ይዋቀራሉ፤ እነዚህም "አይዮ"፣ "ማራ" እና "ግዶ" በመባል በቅድመ ተከተላቸው ይሰለፋሉ፡፡

እምቢልታ በሕብረተሰቡ ዘንድ በድሮ ጊዜ በዋናነት ንጉሡ ለሕዝቡ ግብዣ በሚደርግበት ዕለትና በሠርግ፣ በግርዘትና በታላላቅ ክብረ በዓላት ስነ-ሥርዓት ላይ ይነፋል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያውንና ለመንፋት አቅምና ጥበብ ያላቸው ሶስት ወንዶች በውዝዋዜ አጅበው ያቀርቡታል/ ይጫወቱታል፡፡

ማልካታ (Malkkataa)

ማልካታ ከባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች አንዱ ሲሆን አሠራሩ የቀርከሃ ዛፍ በየቅርጹ ተከፍሎና ተቆርጦ በሸምበቆ ወይም እር ወይሻ የሚባል ዛፍ እላዩ ላይ ከተደረበበት በሰጢነታ (የስጋ ዓይነት) ደርቦ በወፍቾ በማሰር ነው፡፡ ይህ የሙዚቃ መሳሪያ አዋጅ፣ ከፍተኛ ስብሰባ፣ ከንጉስ ዘንድ ጥብቅ ማስታወቂያ ሲኖር፣ ለሕብረት ሥራዎች ቅስቀሳ ሲያስፈልግ እና ታዋቂ የአደን ፈረሰኞች በቀን ቀጠሮአቸው መገናኘት ሲያስፈልጋቸው ወዘተ ይነፋል፡፡

የሙዚቃ መሣሪያውን ከሌሎች ሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ሳይቀናጅ ብቻውን ለመንፋት አቅምና ጥበብ ባለው ወንድ ይቀርባል፡፡

ኡልዱዱዋ (ulduuduwaa)

ከባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች አንዱ የሆነው "ኡልዱዱዋ" አንድ ክንድ ርዝመት ካለው ቀርከሃና ከበሬ ቀንድ ተጣምሮ ይሰራል፡፡ ቀርከሃው ይበሳና በተፈጠረው ቀዳዳ በኩል ሲነፋ በጫፍ ላይ በተሰካው ቀንድ በኩል እጅግ ማራኪ ድምጽ ያወጣል፡፡ "ኡልዱዱዋ" ከ "ካምባ"  "ካራቢያ" እና ጫቻ ዛዬ ጋር በመቀናጀት በሠርግ፣ በግርዘት፣ በታላላቅ ክብረ በዓላትና ለአዋጅ መቀስቀሻም ይነፋል፡፡ ይህ መሣሪያ ለመንፋት ረዘም ያለ ትንፋሽ ስለሚጠይቅ አቅምና ልምድ ያላቸው ወንዶች ይነፋሉ፡፡

ፑላሊያ (Pulaaliyaa)

ይህ የትንፋሽ ባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ የሚሰራው ከ20-30 ሳ.ሜ በሚደርስ ሸምበቆ ነው፡፡ ሸምበቆው በአራት አንጓ ይቆረጥና ሁለቱ አንጓዎች በሙሉ ርዝመታቸው ሲሆኑ የቀሩት ሁለቱ የጫፍና ጫፍ አንጓዎች በግማሽ ተቆርጠው ይቀረጻሉ፡፡ በእያንዳንዱ አንጓዎች ሁለት ሁለት ቀዳዳዎች ይበሳሉ፡፡

ይህን የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱት ወንዶች ሲሆኑ በእጅ ጣቶቻቸው የፑላሌውን የጎን ቀዳዳዎች በየተራ በመዝጋትና በመክፈት በአንድ ጫፍ በመንፋት ይጫወታሉ፡፡ የወላይታ ሕዝብ ይሀን የሙዚቃ መሣሪያ ለትዝታ፣ ለምስጋና፣ ለመዝናኛ እና ለአምልኮ ዜማዎች ይገለገልበታል፡፡ ከሁሉም በበለጠ ከብት የሚጠብቁ ለጋ ልጆች ያዘወትሩታል፡፡ ከብቶቻቸውን መስክ ላይ አሰማርተው የኑሮ ስንክሳራቸውን ያሰላስሉበታል፡፡ ደስታቸውንና ሐዘናቸውን ያንጎራጉሩበታል፡፡ ከብቶቻቸውን ያሞካሹበታል፡፡ በዚህ አውድ ላይ የሚዘወተሩ በርካታ ስነቃላትንና እንጉርጉሮዎችን በፑላሊው ያጅባሉ፡፡

                                                            

ፐሮሲያ (poorisiyaa)

    ፐሮሲያ ከ "ጩራሬ" እና "ፖራሴ" ከሚባሉ የዛፍ ዓይነቶች የሚሰራ ሲሆን ቁመቱ 1.5 ሜትር ይሆናል፡፡ እነዚህ ዛፎች ውስጣቸው ክፍት በመሆኑ ለሙዚቃ መሣሪያነት ሊያገለግሎ በሚችሉበት ቁመት ተቆርጦ ሲነፋ ምንም ዓይነት መሰናክል ሳይኖር ትንፋሽ ያወጣሉ፡፡

    ይህ የሙዚቃ መሣሪያ ከየትኛውም ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ለአያያዝና አጨዋወት ምቹ ነው፡፡ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች መሳሪያውን ወደፊት ቀጥ አድርገው ይይዝቱና ጠበብ ባለው ጫፍ በኩል በስልት ሲነፉት የሚጥም ድምጽ ያወጣል፡፡

     ይህ መሣሪያ በአብዛኛው ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ተዘውትሮ ባይቀናጅም አልፎ አልፎ ቅኝቱን በጠበቀ መልኩ ከካምባ እና ካራቤ ጋር አሳጅበው መጫወትም ይቻላል፡፡

መሣሪያው አገልግሎት ላይ የሚቀርበው ምሽት ሰዓት የሰፈር ሰዎች በአንድ ቦታ ተሰባስበው በሚጫወቱበት በብሔሩ ቋንቋ ዱቡሻ (Dubbushaa) አውድ ላይ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ እንደ ጃርት፣ ቀበሮ፣ ከርከሮና የመሳሰሉት አራዊት ጨለማን ተገን አድርገው እህላቸውን ሊያበላሹ ሲመጡ ፖርሲያን በማስጮህ ከሩቅ በርግገው እንዲሸሹ በማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡ በወላይታ ዘመን መለወጫ ግፋታ በዓል ጊዜ "ጉሊያ" (guuliyaa) ሲቀጣጠል፣ በግርዘት እና ሌሎችም ክብረበዓላት ወቅት አውዱን ለማድመቅ ይገለገሉበታል፡፡

 

3. የግርፍ ሙዚቃ መሣሪያዎች

     እነዚህ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በጅማት ወይም በሌላ ተመሳሳይ ጥንካሬ ባላቸው ነገሮች የተወጠሩ ሲሆኑ በእጅ ወይም ለመከርከር በተዘጋጀ (በተቀረጸ) እንጨት ሲገረፉ ማራኪ ድምጽ የሚሰጡ ናቸው፡፡

 እነዚህ የሙዚቃ መሣሪያዎች በአንጻሩ ተዘወታሪነታቸው አነስተና ሲሆን ዓይነታቸውም እንደሚከተለው ተዘርዝሯል፡፡

ዲታ (diittaa)

      ይህ የግርፍ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ከኤሊ ቆዳ፣ ከእንጨትና ከከብት ጭራ ይሰራል፡፡ መሳሪያው አጨዋወቱን በተካኑ ወንድ ወይም ሴት ሊቀርብ የሚችል ሲሆን ስልቱን እየተከተሉ የሚደንሱ ተጫዋቾች ይሳተፉበታል፡፡ ዲታ ለቀረርቶ፣ ለሽለላ፣ ለፉከራ፣ ለትዝታና ለመድረክ ማድመቂያነት በአብዛኛው የሚቀርብ ሲሆን በግርዘት፣ በሠርግ እና በሌሎችም የባህላዊ ስነ-ጥበብ ዝግጅት ላይ ይጫወቱታል፡፡ ይህ መሣሪያ ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ሳይቀናጅ ብቻውን ይቀርባል፡፡

ማጠቃለያ

      የወላይታ ብሔር ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች እጅግ በጣም ተወዳጅና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንደነበሩ የተለያዩ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ ከትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች አንዱ የሆነው ዲንኬ በዓለም እጅግ ረጅም (the longest musical instrument in the world) በመባል ተገልጿል፡፡ ሌላው ደግሞ የወላይታ ጫቻ ዛዬን ከደቡብ አፍሪካው ቫቩዜላ ጋር በንጽጽር ብናጣጥም የድምጹን ቃና ተመራጭነት ለአድማጩ መተው ነው፡፡

      ከዚህም በላይ የወላይታ የሙዚቃ መሳሪያ ከ ኮይሻቷ አንስቶ እስከ ዬዳ ስምንት ዓይነት የዘፈን ዜማ ቅኝቶች(ሪትም) አሏቸው፡፡ የአውሮፓው ግን ከጃዝ አንስቶ እስከ ክላሲካል አራት የዘፈን ዜማ ቅኝቶች ብቻ ናቸው፡፡

      ስለዚህ ከእነዚህ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የወላይታ ሕዝብ በሙዚቃው ጥበብ ዘርፍ ከቱሪስቶች ከሚገኘው ገቢ አንጻር የኢኮኖሚ ዋልታ ሊባሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም እነዚህ መሣሪያዎች በአግባቡ ለሕዝቡ ሁለንተናዊ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ ባህላዊነታቸውን ባልለቀቀ መልክ ማልማትና ከፍተኛ የማስተዋወቅ ስራ መስራት ከመላው የብሔሩ ተወላጆችና ከብሔሩ አጋር ግለሰቦች ይጠበቃል፡፡