በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ እስከ 17ኛው መቶ ክ/ዘመን መንግስት የነበራቸውም ያልነበራቸውም አከባቢዎች በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ይመሩ አንደነበር ይታወቃል፡፡ ከባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትም በሽምግልና የሚፈጸመው ዳኝነትና የእርቅ ሥርዓት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
በወላይታ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የተጀመረበት እርግጠኛ ጊዜ በውል ባይታወቅም እጅግ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ ይህ ማህበራዊ ክዋኔ የወላይታን ግዛት ባስተዳደሩ ሶስት ስርወ መንግስታት በሙሉ ይተገበር እንደነበር የተለያዩ ተውፊታዊና ጽሑፋዊ የታሪክ መረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡ በቀዳሚው የአሩጂያ ስርወ መንግስት በማህበረሰቡ ውስጥ ይከናወን የነበረው የዳኝነት ሥርዓት በሽማግሌ የሚሰጥ የፍርድ አሰጣጥ እንደነበር የታሪክ አዋቂዎች ያወሳሉ፡፡ በ12ኛው ክ/ዘመን ወላይታን የማስተዳደር በትረ ስልጣን ከተረከበው የወላይታ ማላ ስርወ መንግስት ዘመን ጀምሮ ከዚያ በመቀጠል በ1430 ዓ.ም አከባቢ የፖለቲካ ስልጣኑን እስከተረከበው የትግሬ ስረወ መንግስት ማብቂያ ድረስ ህብረተሰቡ ይተዳደርበት የነበረው ያልተጻፈ ነገር ግን የደረጀ መዋቅራዊ አፈጻጸም በነበረው ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ነው፡፡ በሽማግሌ የሚፈጸመው የሙግት ፍርድ እና ብያኔም በተጠናከረ መልኩ ይከናወን ነበር፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በወላይታ ብሔር ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በሁለት መልክ ይከናወናል፡፡
ይህ ስርዓት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ እየተተገበረ ያለና በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በህብረተሰቡ መካከል የሚፈጠሩ የፍትሐብሔር ችግሮችን ፍርድ ቤት ከመሄዳቸውም በፊት ይሁን ከሄዱ በኋላም በሽማግሌ ደረጃ ይዘው የሚፈቱበት ነው፡፡
የወላይታ ብሔር በሕብረተሰቡ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ትንኮሳዎች፣ በስነልቦናና በአካል ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ከዚያም ከፍ ሲል ነፍስን እስከማጥፋት የሚደርሱ ወንጀሎችን በሽማግሌ ደረጃ የመዳኘት ነባር አኩሪ ባህል ነው፡፡
በዚህ ደረጃ የሚዳኙ ጉዳዮች
እነዚህና የመሳሰሉ ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈጸሙ ከሕብረተሱ መካከል የተመረጡ ሽማግሌዎች የጥፋተኛውን ጉዳይ በጥልቀት በብዙ ማስረጀዎች ካረጋገጡ በኋላ በባህሉ መሠረት የብይን ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ለአብነት ያክል የሚከተሉትን እናቀርባለን፡፡
ሀ. የደመኛ እርቅ ካሣ ሥርዓት (Cuucaa Cachcha)
በሕብረተሰቡ መካከል ነፍስ የማጥፋት ድርጊት በሚከሰትበት ጊዜ ጉዳዩ ከግለሰቦች አልፎ ጎሳዊ ይዘት ይይዛል፡፡ በዚህን ጊዜ በገዳይ ወገን እና በሟች ወገን መካከል በጠላትነት መፈላለግ ስሚፈጠር ነገሩ ወደ በቀልና ደም መቃባት እንዳይሰፋ በሀገር ሽማግሌዎች ወዲያው ይያዛል፡፡
የገዳይ ጎሳ ሽማግሌዎች “እኛ አጥፍተናል በድለናል ይቅርታ ይደረገልን ለጥፋታችንም ተገቢ ካሣ እንከፍላለን (wogi)” በማለት ከገዳዩም ከሟቹም ጎሳ ውጭ የሆኑ እውቅ ሽማግሌዎችን ወደ ሟች ቤተሰብ ይልካሉ፡፡
ከብዙ ማግባባት በኋላ የሟች ቤተሰብ ለእርቁ ፈቃደኛ ሆነው ሲገኙ ከሁለቱም ጎሣ ውጪ የሆኑ በሀገር አከባቢው የታወቁና የታፈሩ ሰባት ሽማግሌዎች ለዳኝነት ይሰየማሉ፡፡ እነዚህ አስታራቂ ሽማግሌዎች የዳኝነቱን ሥርዓት በባህሉ የእርቅ አፈጻጸም ሥርዓትና ወግ መሠረት በሚከተለው መልኩ ያስፈጽማሉ፡፡
በዚህ እርቅ ስርዓት ላይ ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ሰዎች ይታደማሉ፡፡ የገዳዩን እህቶችና የሟች እህቶች ወክለው በእርጅና ምክንያት መውለድ ያቆሙ አረጋዊያን እናቶች ይቀርባሉ፡፡ የእነዚህ አረጋዊያን እናቶች ምሳሌታዊ ትርጓሜ “ከዛሬ ወዲህ ጠላትነትና ደመኝነት ይቁም፤ ይምከን” ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከገዳይ ወገን በኩል መውለድ ያቆመች ላም እና በግ እንዲቀርቡ ይደረግና የጎሳው መንፈስ አዋቂ ያርዳቸዋል፡፡ የእንስሳቱን ደም እየጠቀሰ ሁለቱንም ወገኞች ይቀባል፡፡ ትርጓሜው “ የተቀባነው ደም ይድረቅ ይቁም” ነው፡፡ የታረደውን ከብት ስጋ ግን ሁለቱም ወገኖች አይበሉም፡፡ በብሔሩ ማካ ከሚባለው ጎሳ አንዱ ተጠርቶ ይወሰድና ለአከባቢው የሸክላ ሥራ ባለሙያዎች ያከፋፍላል፡፡
ዋናው እርቀ ሰላም ማውረጃ ሥርዓት በአስታራቂ ሽማግሌዎች አማካይነት የገዳዩ ወገኖች ኮርማ በሬ እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ ይህን በሬ የጎሣው መንፈስ አዋቂ የሆነ ያርደውና ከየብልቱ አይነት ትንሽ ትንሽ ቆርጦ ለጎሳው አማልክት መስዋዕት ያቀርባል፡፡ ከመስዋዕቱ በኋላ የቀረው ሥጋ በሙሉ በቦታው በሥርዓቱ ላይ ለታደመው ህዝብ ይቀርባል፡፡ አስታራቂ ሽማግሌዎች የገዳዩንና የሟቹን ቤተሰብ በአንድነት በማስቀመጥ ከሥጋው ከአንድ ገበታ እንዲበሉ ከተዘጋጀውም ባህላዊ መጠጥ (ፋርሶ) በጋራ እንዲጠጡ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ሥርዓት በኋላ በደመኛነት መፈላለግ ቀርቶ ጤናማ ማህበራዊ ሕይወት ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
የደመኛ ካሣ (ጉማ) በገንዘብ ሲተመን
ይህ የሚከናወነው በአጋጣሚ ገዳዩና ሟቹ ከአንድ ጎሣ ወይም በጋብቻ በተሣሠሩ አማች ቤተሰብ መካከል ሲሆን ነው፡፡ በዚህ መልኩ እርቅ ሲከናወን ከፍተኛ መጠን ያለው የደም ካሣ ገንዘብ (Cuucaa Caditidi) በመክፈል ይፈፀማል፡፤ አንዳንድ ጊዜ በአስታራቂ ሽማግሌዎች የተወሰነው የደም ካሣ ገንዘብ መጠን ከገዳዩ አቅም በላይ ከሆነ እጆቹንና እግሮቹን በሰንሰለት በማሰር በየአደባባዩ በየገቤው ቦታ በመዞር ለምኖ የተጠየቀውን ይከፍላል፡፡ ይህ ካልሆነ እርሙ ለልጅ ልጅ ይቆያል፡፡ (palay kyenan agikko) ተብሎ ይታመናል፡፡
የደመኛ ካሣ ገንዘብ ለመክፈል አቅም በጣም ያጠረው ገዳይ የቅርብ ዘመዶቹን ወይም አማቹን ዋስ ጠርቶ ጊዜ ሊሰጠው ይችላል፡፡ የተወሰነው ጉማ ገንዘብ ተከፍሎ ሲያልቅ በሬ ይገዛና ተበዳዩ ቤተሰብ እንዲያርደው ተደርጎ መብልና መጠጥ ተዘጋጅቶ በጋራ በልተው ጠጥተው የሥርዓቱ ፍጻሜ ይሆናል፡፡
ለ. በሌቦችና ዘራፊዎች ላይ የሚሰጥ የፍርድ ውሳኔ
በዘረፋና ሌብነት ተግባር በመሰማራት ህብረተሰቡን ያስመረሩ በሚየዙበት ጊዜ በመጀመሪ በሀገር ሽማግሌዎች ይገሰጻሉ፡፤ ባለመታረም አሁንም በድርጊታቸው ከቀጠሉ በሕዝብ ትብብር እንዲያዙ ይደረግና ወደ አከባቢ ሽማግሌዎች ይቀርባሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም ዝረዝር ጥፋታቸው ካዳመጡ በኋላ ለዚህ ተግባር በተዘጋጀ ቤት ውስጥ እጅና እግራቸው ከእንጨት ግንድ ጋር ጠርቆ በማሰር ለተወሰነ ጊዜያት እንዲሰቃዩ ይበይናሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ቅጣት በብሔሩ “ዱጤታ” ይባላል፡፤ የእነርሱን ስቃይ አይቶ ሌላው እንዲማር የሚል እንድምታ እንዳለው አዛውንቶች ይናገራሉ፡፡
ሐ. በሐሰት ክስ የሚያመጡ ወይም የሚመሰክሩ ሲያጋጥሙ
አንዳንድ ጊዜ በሐሰት በመክሰስ ንጹሁን ሰው ለመጉዳት የሚፈልጉ አንዳንዴም በሌላው ላይ በሐሰት ምስክር ሆነው የሚቀርጉ ሲያጋጥሙ የሀገር ሽማግሌዎች ወደ ፍርድ ውሳኔ ከመሄዳቸው በፊት በሀገሩ ባህል መሠረት በሚቀጥለው ሥርዓት ያጣራሉ፡፡
በቀጠሮው ዕለት ለዳኝነት የተሰየሙ የሀገር ሽማግሌዎች በጉባኤው ፊት ይቀመጣሉ፡፡ በሁሉም ፊት ተነባብሮ የተቀመጠ ጦር መሬት ላይ ይዘረጋል፡፡ በመቀጠልም በሐሰት ክስ ወይም ምስክር የተከሰሰው ሰው በእጁ ጦር ዘቅዝቶ ይይዝና ዓይኑን በጨርቅ ሸፍኖ መሬት ላይ የተዘረጋውን ጦር እየተራመደ እንዲህ ብሎ ይምላል፡፡
Yeline diccoppo - የወለድኩት አይደግ
Haarin go’’oppo- ያፈራሁት አይሁንልኝ
Maayiin hooppo- ለብሼ አይሙቀኝ
Keexxin wottoppo- ቤቴን አልኑርበት… ወዘተ
እንዲህ እየማለ ጦሩን ተራምዶ ካለፈ ግፉ ጡር ሁሉ በራሱ ይሆናል፡፡ በድፍረት ምሎ ካለፈ ሽማግሌዎቹ በክሱ ነጻ ያደርጉታል፡፡
በአጠቃላይ በሽምግልና በዳይና ተበዳይን በመዳኘት እርቀ ሰላም ማውረድ ፍትህ መስጠት በወላይታ አከባቢ እጅግ የተለመደና የሚከበር ባህላዊ ሥርዓቱ ነው፡፡
ይኸኛው ዓይነት ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ከ12ኛ ክ/ዘመን ከወላይታ ማላ ሥርወ መንግስት ጀምሮ እስከ ትግሬ ሥርወ መንግስት ንጉስ ጦና ጋጋ ድረስ የዘለቀ ነበር፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱ ያልተጻፈ ይሁን እንጂ ለዘመናዊ የፍትህ ሥርዓት በቀረበ መልኩ ተዋረዳዊ መስመር የተከተለ የውሳኔ ሂደት ይይዛል፡፡
በህብረተሰቡ መካከል ከበድ ያለ ቅጣት ሊያስበይኑ የሚችሉ ከባድ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ ይኸኛው የዳኝነት ዓይነት ይተገበራል፡፡
የወንጀሉን አፈጻጸም የሚመረምሩት በቅድሚያ ከተለያዩ ጎሣዎች የተውጣጡ 51 (ሃምሳ አንድ) የሸንጎ አባላት ሲኖሩ ከእነርሱ ለጥቀው የሚያጣሩ 12 (አስራ ሁለት) የንጉሥ አማካሪዎች አሉ፡፡ በእነዚህ የንጉስ አማካሪዎች የተጣራው ጥፋት በሞት ፍርድ የሚያስቀጣ ሆኖ ከተገኘ ለንጉስ ይቀርባል፡፡ ንጉሱም ዝርዝር አፈጻጸሙን ካዳመጠ ወዲህ በሞት የሚያስቀጣ ሆኖ ካገኘው “አናክ” ብሎ የብር ቀለበቱን ካነሣ ፍርዱ ይጸድቃል፡፡
ከበድ ያሉ እስከሞት ሊያደርሱ የሚችሎ ወንጆሎች
የሞት ፍርድ አፈጻጸም ሥርዓት
የተፈጸመውን ከበድ ያለ ወንጀል በቅድሚያ ከሕዝቡ የተለያዩ ጎሣዎች የተውጣጡ 51 የህዝብ ሸንጎ አባላት ይመረምራሉ፡፡ ጥፋቱ ከእነርሱ ደረጃ ላቅ ብሎ የከበደ ከሆነ ለ12 የንጉሡ አማካሪዎች ይቀርባል፡፡ የንጉሡ አማካሪዎች ጥፋቱን በጥልቀት መርምረው የሞት ፍርድ እንደሚገባው ካረጋገጡ ከዝርዝር መረጃ ጋር የፍርድ ውሳኔ ለንጉሡ ይቀርባል፡፡ ንጉሡም ነገሩን ከተገነዘበ በኋላ (ኦናክ) ብሎ በብር ቀለበቱ የውሳኔውን መጽደቅ ያረጋግጣል፡፡
በወላይታ የቀድሞ ታሪክ የሞት ቅጣት በሚከተሉት መንገዶች ይከናወናል፡፤ እነርሱም፡-
በሲፋ የሚፈጸም የሞት ቅጣት (መሰየፍ)
አንድ ከባድ ወንጀል ፈጽሞ የተያዘ ሰው በቅድሚ ወደ 51 የሸንጎ አባላት ጉባኤ ፊት ይቀርብና ጥፋቱ ይጣራል፡፤ የጥፋቱ ዝርዝር ጋር ሪፖርቱ ለንጉሡ አማካሪዎች (12 ሲደርስ እነርሱም በደረጃቸው በጥልቀት ያገናዘቡና በርግጥም የሞት ቅጣት የሚያሰጥ ከባድ ወንጀል ሆኖ ሲያገኙት ለንጉሥ ያቀርባሉ ንጉሡም ካየው በኋላ ካመነበት “ኦናክ!” ብሎ በብር ቀለበቱ ሲያጸድቅ የሞት ቅጣት አፈጻጸም በባህሉ መሠረት ይሆናል፡፡
የጥፋተኛው ድርጊት ለህዝብ በአደባባይ ከተነገረ በኋላ በኦፋ ወረዳ ውስጥ የሞት ውሳኔ የተላለፈባቸው ወደሚሰየፉበት ሆሎዜ ገደል ይኬዳል፡፡ በሆሎዜ ገድል አናት ላይ እንዲሰይፉት ለሸክላ ባለሙያ (“ሲፋ ጪናሻ”) ይሰጣል፡፡ እርሱም በትልቅ ስል ሰይፍ አንገቱን ቆርጦ ገደል ውስጥ ይጥለዋል፡፡ የሟች ዘመዶች ከገደሉ በታች ጠብቀው ከአንገት በታች ያለውን ሰውነቱን ያነሱና ከአንገቱ በላይ የተቆረጠውን ክፍል ከንጉሡ ዘንድ ይቅርታ ለምነው አስፈቅደው በመውሰድ ይቀብሩታል፡፡
በ”ጣጫ” የሞት ቅጣት የተበየነበት ሥርዓት አፈጻጸም
የሞት ቅጣት የተወሰነበት ሰው መሬት ተቆፍሮ ከአንገት በታች በሕይወቱ እያለ ይቀበርና በጭንቅላቱ ላይ ፈረሶች ይነዳሉ፡፡ በፈረሶች ግልቢያ ኮቴ ጭንቅላቱ ተጨፍልቆ ሲሞት እዚያው ጉድጓድ ቀብሩ ይከናወናል እንጂ ለቤተሰብ አይሰጥም፡፡
በ”ይንፑዋ” የሚፈጸም የሞት ቅጣት
ወንጀለኛው እጅግ ዘግናኝ የሆነ ጥፋት በሰው ላይ አድርሶ ከሆነ ለምሳሌ ከነቤተሰቡ ከብትና ቤቱ በላዩ ማቃጠል፣ በዘረፋና ሌብት ወንጀል ህዝብ ያስመረረ፣ የሰው ሚስት የደፈረ… ወዘተ በ “ይንፑዋ” የሞት ቅጣት ይፈጸምበታል፡፡ አፈጻጸም በጣም ወፍራም ዱላ ሆኖ የታችኛው ጫፍ የተድቦለቦለ ይያዝና ጥፋተኛውን አጋድሞ መላ ሰውነቱን በመንቀጥቀጥ አንገቱን ሰባብሮ ሥጋውን ማድቀቅ ነው፡፡ ይህ የደረሰበት ወንጀለኛ በብዙ ስቃይ ሲያጣጥር ቆይቶ እዚያው ነፍሱ ይወጣል፡፡
በመቆንጠጫ በ”ቃጵያ” እንዲሞት ማድረግ
በዚህ መልኩ የሞት ቅጣት የሚበየንባቸው ሰዎች በመንግስት ደረጃ ተጠያቂነትን ሊያስከትል በሚችል የሀገርና የህዝብ ደህንነት ላይ ወንጀል ሲፈጸም ነው፡፡ ወንጀለኛው ተይዞ መሬት ላይ ይዘረርና በራስጌውና ግርጌው ትልቅ ድንጋይና ችካል ተተክሎ ከሰውነቱ ጋር ይጠፈራል፡፡ በመቀጠልም ከወፍራም እንጨት በተሠራ ረዥም ጠንካራ መቆንጠጫ (Qaphiyaa) እንዲጣበቅ በማድረግ በአፍ በአፍንጫው ደም በሌላውም መውጫ ብዙ ነገር እንዲያመልጠው እየተደረገ እየጠበቀ እየጠበቀ ሄዶ በአሰቃቂ ሁኔታ የህይወቱ ፍጻሜ ይሆናል፡፡
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት የሞት ቅጣት ፍርድ የሚፈፀሚባቸውን ባህላዊ አፈጻጸም ነው፡፡ ከእነዚህ በተለየ መልኩ ከበድ ያለ ወንጀል ፈጽመው ፍርዱ የሚቀልላቸው ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ጥፋተኞች ከአከባቢው ወደ ሩቅ ሀገር እንዲሰደዱ ሲወሰን ቤተሰቡን ብቻ ይዞ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ሀብት ንብረቱን ንጉሡ ይወርሳል፡፡ ዳግመኛ ወደ ትውልድ ቀዬው አይመለከትም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በስደት የሚለለው ግለሰብ “ፈጽሞ መውጣት አልችልም አርጅቻለሁ፡፡” ብሎ ቢከራከር በትላልቅ ዱላ እየገፉ አንገላተው ይገድሉታል፡፡ ሀብቱን ልጆቹ ይወርሳሉ፡፡
ለሞት የሚያበቁ ጥፋቶች የቅጣት ዓይነቶች
የጥፋተኛው ወንጀል ክስ ለንጉሡ አማካሪዎች (ዞሬ ሞጮና) ቀርቦ ለሞት የሚያበቃ ሆኖ ባያገኙት ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለታችኛው መዋቅር (የሸንጎ መማክርት አባላት) ያወርዳሉ፡፡ በእነዚህ የሸንጎ አባላት የሚተላለፉ ቅጣቶች መካከል
በአጠቃላይ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በወላይታ ከረዥም ዘመናት በፊት ጀምሮ ያለ ማህበራዊ ክዋኔ ነው፡፡ ይህ ባህላዊ ሥርዓት በሁለት መልኩ ሲከናወን መቆየቱንም ከላይ በቀረበው ጽሑፍ በዝርዝር ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ባህላዊ ዳኝነቱ ባለፉት ዘመናት የነበረ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዚህ ዘመን ለምንተዳደርበት ዘመናዊው የፍትሕ ሥርዓት የራሱን አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የመዋቅር ተዋረዱን ይዞ እስከ ንጉሡ ድረስ የሚዘልቀው የብይን ሥርዓት እስከ ትግሬ ሥርወ መንግስት የመጨረሻው ንጉሥ ካዎ ጦና ጋጋ ድረስ ሲተገበር ቆይቶ አብሮ የከሰመ ሲሆን የሽማግሌ ባህላዊ ዳኝነት ግን እስከአሁን ድረስ በስፋት የሚሰራበት ስርዓት ነው፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza