• Call Us
  • +251465512106

ባህላዊ የደመኛ እርቅ ሥርዓት(Cuucaa cachchaa)

 የደመኛ እርቅ ሥርዓት በነባሯ ወላይታ (Cuucaa cachchaa)

የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ከሌሎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት መዋደድና መፋቀር መጣላትና መጋጨትም አይቀሬ ክስተቶች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ የሚከሰት መቃቃርና መበቃቀል ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ይቀጥፍ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ይህ አስከፊ ድርጊት ምህዳሩን አስፍቶና ተባብሶ ዜጋን እንዳይጨርስ የጥንት ወላይታዎች በባህላቸው የሚፈጽሙት ድንቅ የሀገር በቀል እውቀት Cuucaa cachchaa ነበራቸው፡፡

በዚህ ጽሑፍ “ጩጫ ጫቻ” ምንድነው?፣ ይህ ስርዓት ለምን ይፈጸማል?፣ እንዴትስ ይፈጸማል?፣ ለሚሉ ጥያቄዎች ዝርዝር ገለጻዎች ልናቀርብ እንሞክራለን፡፡

በነባሩ ወላይታ “ጩጫ ጫቻ”  ማለት የአንዱ ጎሳ አባል የሌላውን ጎሳ አባል በጥላቻ ወይም ድንገት በተፈጠረ ቅራኔ አጥቅቶ ሲገድል የሟች ቤተዘመድ ገዳዩንና የገዳዩን ቤተሰብ በበቀል ተነሳስቶ እንዲጠቁና ችግሩ ተባብሶ በሁለቱ የጎሳ አባላት መሐል እልቂት እንዳይፈጠር ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች የሚያስማሙበት ወሳኝ የእርቅ ስነ-ሥርዓት ነው፡፡ ገዳዩ ግለሰብ የሰው ሕይወት በእጁ እንዳጠፋ ሲያረጋግጥ በወቅቶ የሚፈጠረው ሁኔታ ለሕግ አካል እጅ ለመስጠት ምቹ ስለማይሆንና ለሕይወቱ በጣም ስለሚሰጋ ወደ ታዋቂ ሽማግሌዎች ቤት በመሄድ “የሰው ሕይወት በእኔ እጅ አልፏል እርቅ በማውረድ ሊደርስበት ካለው የሕይወት እልቂትና አደጋ አድኑኝ (ገላግሉኝ)፡፡” በማለት በብርቱ ይለምናል፡:

ይህን አስደንጋጭ መርዶ የሰሙ ሽማግሌዎች የወጋቸውን ለመፈጸም አንድ ተወካይ ይመርጣሉ፡፡ ተወካዩ ሽማግሌ ወደ ንጉስ ዘንድ በመሄድ በአከባቢው የተፈጸመው ግድያ በጎሣ ግጭት ምክንያት መሆኑን ከገለፀ በኋላ በ”ጩጫ ጫቻ” ስነ-ስርዓት ሁለቱንም ጎሣዎች (የገዳይና የሟች) ለማስታረቅ ፈቃድ ያገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ተወካዩ ሽማግሌ ከሌሎች ስድስት ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ወደ ሟች ቅርብ ዘመድ ቤት ሄዶ “Tumay neessa, ne zariyaassa; cuucaa caddada gumiyaa ma: nuuni giigissana nuussi imaa.” በማለት ይማጸናሉ፡፡ ትርጉሙም ተበዳይ ነህ ፍትህ ለአንተ ለዘርህ ይገባል በደለኛውን ግለሰብ በመሃላ አረጋግጥና የደም ካሣ  ይከፈልህ፣ ሂደቱን እኛ እንጨርሳለን፡፡” እንደማለት ነው፡፡ ሽማግሌዎች በሟች ቅርብ ዘመድ ደጃፍ የእርቅ ምልጃቸውን ለሶስት ቀናት ሳያቋርጡ ያካሂዳሉ፡፡

ከዚህ በኋላ የሟች ቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው በጉዳዩ ከቤተሰብና ከቅርብ ቤተዘመድ ጋር ለመመካከር ቀጠሮ ሰጥቶ ይሸኛቸዋል፡፡ በቀጠሮ ቀን ለሚመጡ ሽማግሌዎች የሟቹ ቅርብ ዘመድ “ከእናንተ ተነጥለን የት እንደርሳለን?” ካሉ በኋላ በሟቹ ይረዱ የነበሩ የቤተሰብ አባላት በሙሉ ከልጅ እስከ አዋቂ ይናገሩና “እንደወጋችሁ አድርጉ” ይላሉ፡፡

ሽማግሌዎቹም “Diidoogaappe daanaage dares) (ከኖርነው ልንኖር ያለነው ይበልጣል)” በማለት ገዳዩ እንደመጥፎ አጋጣሚ ሆኖ የገደለውም ራሱን ጥፋተኛ በማድረግ ይቅርታ ስለሚጠይቅ የካሣ ቅጣቱን ዝቅ አድርጉ ብሎ ይለምናሉ፡፡ በዚህ መሰረት ከሟች ቤተሰብ መስራት ለማይችሉ ሕጻናትና አረጋዊያን እስከ እለተሞታቸው የሚተዳደሩበት ገንዘብ በብሔሩ ቋንቋ “ጉሚያ” (Gumiyaa) ለማስከፈል ያስማማሉ፡፡ ይህንንም በ”ጩጫ ጫቻ” ቀን ለማምጣት ቀጠሮ ቆርጦ ይመለሳሉ፡፡

ከዚያ በኋላ ደመኛውን በእርቁ ስነ-ስርዓት ካልተሳተፈ በበቀል ተነስቶ ችግር ሊፈጥ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩትን ሰው በመሰብሰብ ለእርቁ ፈቃደኛ መሆናቸወን አረጋግጦ ለካሣ (ለጉሚያ) (Gumiyaa) ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልገው በዕለቱ በመግለጽ በእርቁ ቀን ወይም በ”ጩጫ ጫቻ” ቀን ይዞ እንዲቀርቡ ይነገራቸዋል፡፡

በባህሉ መሰረት በጩጫ ጫቻ (Cuucaa cachchaa) ቀን የሚቀርቡ ነገሮች

  1. በግንባሩና ጅራቱ ላይ ነጭ ምልክት ያለው ሆኖ ሙሉ መልኩ ጥቁር ኮርማ በሬ (ለሟቹ)ቿ ቅርብ ዘመድ የሚሰጥ፣
  2. ለሟቹ ቤተሰብ የሚሰጥ ካሣ (የደም ካሣ) (Gumiyaa) እና
  3. ለመሃላ (“ጩጫ ጫቻ) (Cuucaa cachchaa) የሚያገለግሉ ነገሮች ማለትም የወፍጮ ድንጋይ፣ ወሊድ ያቆመች በግ፣ ወሊድ ያቆመች ላም እና ማየት የተሳናት አሮጊት ሴት ናቸው፡፡

እነዚህን ነገሮች የማቅረብ ግዴታ የደም አፍሳሹ ሲሆን አቅሙ የማይፈቅድ ከሆነ ከዘመድ አዝማድ ይለምናል፡፡ በነገሮች መጓደል የእርቅ ስነ-ስርዓት (Cuucaa cachchaa) ከተደናቀፈ መዘዙ ለእነሱም እንደሚተርፍ ጠንቅቆ ስለሚያውቁ አንድም ዘመድ የእርዳታ እጅ የማይዘረጋ አይኖርም፡፡

በመጨረሻ ለሁለቱ የጎሳ አባላት የሚመች ቀን በማስመረጥ ሽማግሌዎች በሟቹ ቤተሰብ ዘንድ የምግብና የመጠጥ ድግስ እንዲዘጋጅና ወጪውም በገንዘብ በማርጮ ተተምኖ በገዳዩ እንደሚሸፈን ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ በዕለቱ ለመስተንግዶ እርድ የሚካሄድ ሲሆን እርዱ ተወካይ አንጋፋ ሽማግሌ ይፈጽማል፡፡

በ”ጩጫ ጫቻ” ስነ-ስርዓት  ሶስቱም ወገኖች ማለትም ሽማግዎች፣ የገዳዩና የገዳዩ ጎሣ አባላት እና የሟች ጎሣ አባላት በሟች ቅርብ ዘመድ ደጅ ሜዳ ቦታ ቦታቸውን ይዘው ተቀምጠው ከገዳዩ ወገን ለጩጫ ጫቻ አስፈላጊ ነገሮች የሚቀርቡ ሲሆን ከሟች ወገን የእለቱ የምግብና የመጠጥ መስተንግዶ ይቀርባሉ፡፡

በመቀጠል ተወካዩ ሽማግሌ አጠቃላይ የእርቁን ሁኔታ በተመለከተ ለሁሉም ገለጻ በማድረግ ወደ ቀጣዩ ተግባር ይመራል፡፡ ገዳዩ፣ የገዳዩ ጎሣ አባላትና ዘመዶቹ የእንሰት ቅጠል ግልድም በመታጠቅ፣ ሁለት ለግብዣ የሚታረዱ የበግ ጠበቶችን በመያዝና ግንባራቸውን ጥላሸት በመቀባት በእንብርክክ (በጉልበታቸው በመዳህ) ወደ ሟች ቅርብ ዘመዶችና ጎሣ አባላት ዘንድ ሲቀርቡ የተበዳዩ ጎሣ አባላት የበዳይ ወገኖችን በሐዘኔታ ይመለከታሉ፡፡

በመቀጠል ሽማግሌዎቹ ለእርቁ ታማኝ የሆኑትን የገዳዩ ጎሣ አባላት ያረጋግጣሉ፡፡  (ከጩጫ ጫቻ) ቀን በኋላ በሁለቱ ጎሣዎች መሃል ሰላም፣ ፍቅር እና መወዳጀት እንዲሰፍን በመመረቅ በጎችን አርዶ በሁለቱም የተመረጠ የሸክላ ጥበብ ሥራ ባለሙያ ወጥቶ ለመሃላ የቀረቡ ነገሮችን እየነካ ሁለቱም ወገኖች ውላችንን አፍርሰን የብቀላ ወንጀል ከሰራን “እንደ እነዚህ ግዑዛን ድዳ ያድርገን፣ ልጅ አይስጠን፡፡” በማለት እንዲደግሙ ያስተባብራል፡፡ እነሱም ቃለ መሐላውን ደጋግመው ቃል ይገባሉ፡፡

በመጨረሻም ሽማግሌዎቹ ለእርቅ (cuucaa cachchaa) የቀረቡ ግለሶቦችን ከሚታረደው ሥራ አንጀት ሁለት ጫፎችን በማስያዝ ከመሃል ቆርጦ “በእናንተ መሃልም የተከሰተው ጥል እንደዚህ ስጋ ተቆርጧል፣ ከአሁን በኋላ ጥላቻ የለም፣ ሰላም ለሁለቱም የጎሣ አባላት ሆኗል፡፤” በማለት የምግብና የመጠጥ ግብዣ እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡ ሰው ሁሉ እንዳሻው ይበላል፤ ይጠጣል፡፡ የሟቹና የገዳዩ ጎሣ አባላትና የቅርብ ዘመዶች የአንድ ቅል ቦርዴ ለሁለት (daguwa) የሚጠጡ ሲሆን ድርጊቱ ሁለቱ ጎሣዎች በትክክል እንዲታረቁና ከልብ ይቅር እንደተባባሉ የሚያሳይ ትልቅ ትርጉም ያለው ሂደት ነው፡፡ በማጠቃለያ ገዳዩ ግለሰብ በሽማግሌዎች አማካይነት ለሟች ቅርብ ዘመድ የደም ካሣ (Gumiyaa) ያስረክባል፤ ከዚህም በኋላ በስነ-ስርዓቱ የተገኙ ሰዎች ሁሉ በገዳዩና በገዳዩ ዘመድ አዝማድ እና በሟች ዘመድ አዝማድ በጋራ ምስጋናና ምርቃት ተችሮላቸው ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

 

ማጠቃለያ

      “ጩጫ ጫቻ” በጥንታዊት ወላይታ ባህል የአንድ ጎሣ አባል ከሌላ ጎሳ አባል ጋር በአንድ መጥፎ አጋጣሚ በተከሰተው የሕይወት መጥፋት ምክንያታ ግጭቱ ሰፍቶ ተጨማሪ የሕይወት እልቂት እንዳይከሰትና የተዋከባ ማህበራዊ ኑሮ እንዳይፈጠር ለማድረግ ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች የሚፈጽሙት ባህላዊ የደመኛ የእርቅ ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት ግጭት ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን የወላይታ ብሔር ከአሩጂያ ዘመነ መንግስት እስከ ትግሪያ ዘመነ መንግስት ድረስ በነበረው ጊዜ በጣም ጠንካራ የመንግስት መዋቅር መስርቶ በገናናነት ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር በተዘዋዋሪ ቢሆንም ዓይነተኛ ሚና እንደተጫወተ መገንዘብ ይቻላል፡፡

      በመሆኑም ሥርዓቱ ለወደፊት ባህላዊነቱን ባልለቀቀ መልኩ ጥናት ተደርጎና ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተግባራዊ ቢሆን ለመልካም አስተዳደርና ወንጀል መከላከል ሂደት ሁነኛ መሳሪያ ይሆናል የሚል ግምት አለን፡፡

      ስለዚህ ይህ ትውልድ በዚህ ባለብዙ ፋይዳ ባህል ላይ ሰፋ ያለ ጥናትና ምርምር አካሂዶ ለአገልግሎት እንዲያበቃ አበክረን እንጠይቃለን፡፡