• Call Us
  • +251465512106

የአደን ታሪካዊ አጀማመር ​​​​​​​    

አደን ወይም “ሻንካ” በወላይታ ብሔር በጥንታዊያን ዘንድ ከመኖር ህልውና ጋር በጥብቅ የሚያያዝ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ምክንያቱም ለእለቱ ጉርስና ለአካል ልብስ አድርገው የሚጠቀሟቸው ነገሮች ሁሉ ከአደን ውጤት ጋር በጥብቅ የተያያዙ ስነበር ነው፡፡

      በተጨማሪም አደን በድሮ ጊዜ ለተለያዩ አደጋዎች መካከል ይደረግ ለነበረው ተከታታይና ተደጋጋሚ ጦርነት ዝግጅት ልምድ መቅሰሚ መልካም መድረክ ይቆጠር ነበር፡፡ ሌላው አራዊትን ገድለው የሚያገኙትን ነገሮች ለምሳሌ የዝሆን ጥርስ፣ የተለያዩ የአራዊት ቆዳዎችንና ሌጦዎችን በመሸጥ ኑሮአቸውን ለመደጎምም ለሚደረገው ግብግብ አደን ዓይነትና መንገድ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡

      በሌላ አንጻር አንዳንድ የዱር እንስሳት በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ለመቀነስና ለመከላከል አደን ይካሄድ እንደነበርም ታሪክ አዋቂዎች ያስታውሳሉ፡፡

  1. አደን (ሻንካ) አደረጃጀቱና ስምሪቱ

በወላይታ ባህላዊ የአደን ሥርዓት ወቅት አዳኞች በአደን መሪ (ጋዳዎ) አማካኝነት የሚመሩ ሲሆን ጥሪውም የሚተላለፈው በብዛት በአገር ገዥው ነጉሥ ጥሪ ከሚሰበሰቡባቸው አከባቢዎች ወይም ትልቅ ገበያ በሚኖርበት ዕለት ወደቦታው በመሄድ በባህላዊ ጥሪ ማስተላለፊያ መሣሪያ (ኡሉዱዱዋ) በመታገዝ በ “ጋዳዋው” ትዕዛዝ መሰረት ነው፡፡

በዚህ ሥርዓት ተሳታፊ የሚሆኑት ከወጣ እስከ ጎልማሳ የዕድሜ ክልል ያላቸው ወንዶች ሲሆኑ፣ እነርሱም በስምሪት ወቅት እግረኞችና ፈረሰኞች ተብለው በሁለት ጎራ ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ ይህም ሲባል ፈረስ ያለው  ፈረሱን ጭኖ ሲሄድ እግረኞች ደግሞ በእግራቸው ይከታሏቸዋል፡፡

አዳኞቹም ባህላዊ ልብስ (ሀዲያ) የተባለውን ለብሰው በልዩ ልዩ የነበርና የአንበሳ ቆዳ ደርበው፤ እንደዚሁም ከዱር እንስሳት ቆዳ የሚዘጋጀውን ኮፊያ (ኡኪያ) በጭንቅላታቸው ደፍተው ከተገኘም ከቆዳ የተዘጋጀ ባህላዊ ጫማና ጋምባሌ በማድረግ የአደን ዜማ እያዜሙ በአደን መሪው (ጋዳዋ) መሪነት አደኑ ወደሚካኔድበት ጫካ ያመራሉ፡፡ የአደን ዜማው በብሔሩ ቋንቋ “ባሊያ” በመባል ይታወቃል፡፡ የአደን ዜማ (ባሊያ) የሚከተለውን ይመስላል፡፡

         ሶንዴ ፊሪጦ ሳጋዳን ሶንዶ 2x

         ኤ ሶንዴ ፊሪጦ ሶንዶ ፊሪጦ ሳጋዳን ሶን 2x

         ጎቻ ሎካዩ አጅንቻ ጎቻ

               ቦሎ… ሆ… ሆ… ሀያና

               ላሌ ቦሌ ሀያና 2x

         ቁሊያራ ኢይያጌ ጋጭኖ ጋ

               ሀያና

         ጋዲያ ናግያጌ ቡዳዋ አዴ

               ሀያና

         ቶራ ዛሪያጌ ጋርማሞ ሜዜ

               ሀያና

         ኡሎይ ቆፒዮጌ ኡንደና ወደ

               ሀያና

         ዳንጋርሳ አቻይ ሚርቀታ ዛሌ

               ሀያና

         ዛታ ዮቲያጌ ወላይታ ዛሬ

               ሀያና

         ዛኳ ፓርሷ ናችሳ ኤሴ

               ሀያና … እያሉ ያዘማሉ፡፡

   ይሄ ዜማ በአውጭና (መሪ) ተቀባይ ቅብብል የሚዜም ሞቅ ያለ ዜማ ነው፡፡ ዜማውም እጅግ መሳጭ ስለሆነ ሩጫ የተቀላቀለበት እርምጃ በማድረግ በጣም ሩቅ የሆነውንም መንገድ በቀላሉ ተጉዘው ወደ ቦታው ይደርሳሉ፡፡ ለአደን መሰማሪያ ቀን ቅዳሜ ብቻ እንደነበር አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ እግረኞችም ሆነ ፈረሰኞች አዳኞች የሚይዟቸው መሣሪያዎች ዝም ተብለው ለታዩ ተመሳሳይ በሚስሉም የቅርጽ ልዩነት አላቸው፡፡ እግረኞች ጦሮች እና ጋሻዎች ከስፋትና ከብዛት አንጻር ግዙፍ እና በርከት ያሉ ናቸው፡፡ የዚህም ምክንያት እግረኞች ከፈረሰኞች በበለጠ ለሚተናኳሏቸው አውሬዎች የተጋለጡ ስለሚሆኑ ራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል እንዲያስችላቸወ ታስቦ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አዳኞች ወደ ጫካው አቅራቢያ ሲደርሱ በአደን መሪው (ጋዳዋ) ምርቃትና ጻሎት ይደረግና ወደ ጫካው ውስጥ ይዘልቃሉ፡፡ አደን መሪው (ጋዳዋ) “ወራይ ሹጎ” በለስ ይቅናችሁ ገድላችሁ ተመለሱ”፣ “ወላኗፐ አትተ” የፈረስ እግር ከሚሰብር ጉድጓድ ያድናችሁ፣ “ይአይ እንተና ደሞፖ እንተ ዶኣ ደሚተ” እናንተ አውሬ አግኙ እንጂ እናንተን አውሬ አያግኛችሁ፣ “እንተ ኣዋ እንተ ኣየ ጦሳይ እንተና ማዶ” የእናት የአባታችሁ አምላክ ይርዳችሁ… ወዘተ ብሎ ከመረቋቸው በኋላ የሚገደሉ እና የማይገደሉ አውሬዎችን ለይቶ ይገልጽላቸዋል፡፡ ከአደን መሪው ፈቃድ ውጭ አውሬ ገድሎ የተመለሰ ሰው ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ከሚገደሉት አንበሣ፣ ነብር፣ አጋዘን፣ ከርከሮ ወዘተ… ከማይገደሉት ደግሞ ዝንጀሮ፣ ቀበሮ፣ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ አግረኞች ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ፈረሰኞች ደግሞ ከውስጥ አምልጠው የሚወጡትን አውሬዎችን በፈረስ አባረው ይገድላሉ፡፡

አደን መሪው (ገዳዋ) በአደን ሂደት ወቅት በህይወታቸው ላይ አደጋ የሚያደርስ አላስፈላጊ እሽቅድድም እንዳይኖር በጦር አወራወር ጊዜ እንዳጠናቀቄ፣ ተግተው በአደን ግዳይ ፈጽመው ዝነኛ እንዲሆኑና እሱንም ባለዝና እንዲያደርጉት ይመክራቸዋል፡፡ አመራር ይሰጣቸዋል፡፡ እየተከታተለም የሚሰንፈውን አዳኝ ይዘልፈዋል፡፡ በአርጩሜ ይገርፈዋል፡፤ በአዳኞች መካከል በግዳይ ይገባኛል ዙሪያ የሚነሱ ክርክሮችን በመመልከት እልባት ይሰጣል፡፡

በባህሉ አውሬውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያደማ ወይም ያቆሰለ አዳኝ ግዳይ ይሰጠዋል፡፡ የግዳይ ይገባኛል ክርክር በምስክሮች ወይም በባህላዊ መሀላ (ቶራሙራሙሩዋ) ተደርጎ ይፈጸማል፡፡ በባህሉ በሀሰት መማል መቅሰፍት (ጎሚያ) ያስከትላል ተብሎ ስለሚታመን ሳይከራከሩ እንደሚቀበሉ ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

የአደን መሪው (ጋዳዋ) አዳኞን መከታተልና በመካከላቸው የአደን መሪው (ጋዳዋው) ፈቃድና ማዕረግ ያገኘው ቀደም ብሎ ቢያንስ አንድ መቶ እና ከዚያ በላይ አራዊትን በመግደል ስለሆነ አራዊትን ወግቶ መግደል አይፈቀድለትም፡፡ ከዚህ ከመሪነት እሱ የሚያገኘው ትሩፋት ቢኖር “ጋዳዋ ኦናኮና ኦናካ ሻንካን ጋሟ ዎራዳ፣ ማህያ ወራዳ…” እያሉ አዳኞች ሲፎክሩና ሲሸልሉ የሚያገኘው ዝና ክብር አለ፡፡ ውስጥ ውስጥን ሊታይ ግን ሰዎች የመምራትና የማብቃት ችሎታ በማዳበር ለትልቅ አመራርነት ሚና መሰረት መጣያ ጭምር እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡

ወንዶች ለአደን ሲሰማሩ ሚስቶቻቸው ለባሎቻቸው ስንቅ የሚሆን ሳይበላሽ ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚችሉ ምግቦችን ለምሳሌ በቅቤ የታሸ ገብስ (ባንጋ ቡራቷ)፣ ሙልሙል ቆጮ (ኡንጫ ኮምፑዋ) ያዘጋጃሉ፡፡ አክለውም ለፈረሳቸው መኖ የሚሆኑ ጥራጥሬዎችን በማዘጋጀት ይሸኛሉ፡፡ እየጠበቁ፣ ህጻናትን እየተንከባከቡ ማህበራዊ ሃላፊነቶችንም በአግባቡ እየተወጡ የባሎቻቸውን መመለስ ይጠብቃሉ፡፡ ይኸንን የምትወጣ ሴት በማህበረሰቡም ሆነ በባሏ ጥሩ ተቀባነት ታገኛለች፡፡ በሞተችም ጊዜ ከሌሎች ሴቶች በተለየ ሁኔታ

         ባንጋ ቡራቱዋ ሽንቂያሮ

         ኦላዩ ኦዶልቻ ኮሪያሮ

ትርጓሜውም ለባሏ ስንቅ ለፈረሱ መኖ አዘጋጅታ በመሸኘት ግዳይ ጥሎ እንዲመለስ የምታደርግ ጠንካራ ሴት እንደማለት ነው፡፡

በዚሁ መልክ ግለሰቡም ሲሞት ደግሞ

         ነርቢው ዳንጋርሳ ዛሊያ ናኦው

         ግማራው ስለና ካጪያ ናኣው

እየተባለ በተለየ ሽለላና ፉከራ ታጅቦ ይለቀስለታል ማለት ነው፡፡ ሴትቱ ባሏ በለስ ቀንቶት ገድሎ ከተመለሰ ከደጃፍ ቆማ ፈረሱንና በጦር ጫፍ ላይ ተሰክቶ የተንጠለጠለውን የአውሬ ቆዳ (እጀንቻ) በልዩ ደስታ ትቀበላለች፡፡ እሱም ይፎክራል ይሸልላል፡፡ ጎሬበቶቹም ይሄንን ሲሰሙ ወደቤቱ በመምጣት እንኳን ደስ አለህ፡፡ እንኳን ከ “ሞንቻ” ነት ወደ “ወራቲያ” ነት አደረሰህ ይሉታል፡፡ ይሄ ሁኔታ እንግዲህ በሌሎችም ዘንድ መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡

3. የአደን ገድል ሽልማት

አደን በድሮ ጊዜ በሁለት መልኩ ይካሄድ እንደነበር ይነገራል፡፡ ነገስታት በሀገር ደረጃ በማሳወጅ የሚካሄድ አደን እና በአደን መሪው (ገዳዋ) መሪነት የሚደረግ አደን ነበር፡፡ ታዲያ በሁለቱም አደን መስክ በመሰማራት በለስ ቀንቷቸው ገድለው ለተመለሱት ግለሰቦች የተለያዩ ሽልማቶች ይበረከትሏቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡

የነገስታት አደን (ግፋታ ሻንካ) የሚባለው በየአመቱ አንደ በመስቀል ጊዜ ብቻ የሚደረግ የአደን አይነት ሲሆን፣ የዚህም ዓላማ ሀገርን ከጠላት መጠበቅ የሚችል ዜጋ ለማፍራት እንደመለማመጃ ተደርጎ የሚወሰድ አደን ነው፡፡ በዚህ አደን የሚሳተፉት አዳኞች አንበሳና ነብር ገድለው እንዲመለሱ በታዘዙት መሠረት አድነው ገድለው ሲመለሱ ቀጥታ ወደ ንጉስ ቤት ያመራሉ፡፡ ገዳዩ ወደ ንጉሱ ቤት ከደረሰ ሞቅ ያለ አቀባበል ይደረግለታል፡፡ ከዚያም ከንጉሱ አርሶ የሚጠቀምበት ሰፊ መሬት ይበረከትለታል፡፡ ይሄም በብሔሩ ቋንቋ “ካውዋ ዳጌታ” ይባላል፡፡ ካዎይ ዳግዮጋ ተብሎ በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ የሆነ ክብርና ዝናም ይጎናፀፋል፡፡ በመቀጠል ወደ ቤተሰቡ በት በማምራት ከአባት ከብቶችን፣ በሬ፣ ወይፈን፣ ከእናት- ላም፣ ግደር… ያገባ ከሆነ ከሚስት አቅም የፈቀደውን ስጦታ (ወይቷ) ያገኛል፡፡ ሚስት በተጨማሪነት የገብስና አጃ ዱቄት በቅቤ ብቻ የተሰራ ሙቅ (ኤሬታ) ተወዳጅ ምግብ ሰርታ ታበላዋለች፡፡ ከአደን መልስ አጅበውት ለመጡት ጀሌዎቹ ጭምር ከቤተዘመድ ለመስቀል የተዘጋጀው ምግብና መጠጥ ይቀርብላቸዋል፡፡ የአደን መሪ (ጋዳዋ) አማካይነት በሚወጣው አደን ተሳትፎ ገድሎ የተመለሰ አዳኝ ደግሞ እየፎከረና እያቅራራ የግዳይ ምልክት (አጅንቻ ላራ) በጦሩ ጫፍ አንጠልጥሎ ወደ አደን መሪው ጋ ሲደርስ ጓደኞቹ ተሰባስበው በማጀብ ስለመግደል (ሞንቻ) ወደ ገዳይ (ወራቲያ) ደረጃ አሸጋገረህ እያሉ ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የደስታ መግለጫና የሽግግር መግለጫ የሆነውን በጎሽ ዋንጫ የሚቀዳ መሪዎች ጀግኖችን የሚያስጎነጩትን የማር ወለላ  (ቡዳ ኤሳ) አደን መሪው ያስጎነጨዋል፡፡ ከወላጆቹ እና ያገባ ከሆነ ከሚስቱ የሚበረከቱ ስጦታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ማለት ነው፡፡

ማጠቃለያ

የአደን ልምምድ የሚጀምረው ልጆች በሰፈር ቢራቢሮዎችንና የተለያዩ በራሪ ነፍሳትን አባረው እየያዙ፣ እየታገሉ፣ ዝላይ እየዘለሉ ወዘተ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ ራሳቸውን ከሚያበቁበት ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ለአካል ብቃት የሚሆን ስፖርታዊ እንቅስቃሴም ሰለሚኖር ለአካል ጥንካሬም ይጠቅማቸዋል፡፡

   አደን በማህበረሰቡ ዘንድ በየወቅቱ በጊዜ ሂደት የሚከሰቱ ዘረፈ ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ሲባል ይካሄድ እንደነበረ ከፍ ብሎ ተገልጸል፡፡ የማህበር ብሔሩን ትውውቅና ትስስር ከማጠናከር ጎን ለጎን ገሬሳ (ቀረርቶ)፣ ጨቋዋ (ፉከራ)፣ ዘፈን (የታ፣ባሊያ) ወዘተ… የመሳሰሉ የአደን ሂደት ስነቃላት፣ እንዲሁም ባህላዊ ዕደጥበባት ጦር፣ ጋሻ የመሳሰሉትን የማህበረሰቡ እሴቶች ዕውቀት ለትውልድ ቀጣይ እንዲሆን የራሱን ድርሻ ያበረክት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም አደን የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ እንደሚሰት የጥንት አዳኝ የነበሩ ግለሰቦች ያወሳሉ፡፡

ለአደን የማይሄድ ወይም ተሳትፎ ያልገደለ በባህሉ ጀግንነት የራቀው ሰነፍ፣ የጓዳ ሰው (ጉሺያ ሞንቻ) ተብሎ ይነቀፋል፡፡

በሌላ በኩል አዳኞች በትንሹ ለአንድ ወር ያህል በአደን ሰበብ ያለ ስራ ስለሚቆዩ የእርሻ ስራቸውን ስለሚሻማ የእርሻ ምርት ገቢያቸው አነስተኛ እንደሚሆንና ቤተሰቦቻቸው ለረሃብ ይጋለጡ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሕገ ወጥ የሆነ አደን ለወላይታ ዓይነተኛ የቱሪስት መስህብ ለሆኑ በርካታ የዱር እንስሳት ቁጥር መመናመን ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ስለሆነም ሕገወጥ አደን በመቆጣጠርና እጅግ የተመናመነውን የዞኑን የደን ሽፋን በተቀናጀ መንገድ በማሟላት በደኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት በመከላከል ፓርኮችንና ቦታዎችን ለይቶ በማጥናት፣ በማልማት መሰረት ልማቶችን በመዘርጋት የዱር እንስሳት ሀብት ልማትን ለማፋጠን በተጓዳኝነት የቱሪዝም ገቢያችንን ለማሳደግ እንዲቻል የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ሊቀጥል ይገባል፡፡

የዱር እንስሳት ሀብታችን እየለማ በሄደ መጠን ያበቃለትን ሕገወጥ ባህላዊ አደን ተንሰራፍቶ በዱር እንስሳት ሀብታችን ላይ እልቂት እንዳያደርስ ከወዲሁ ሊታሰብ ይገባል፡፡