አምልኮ የሰው ልጅ ከራሱ በላይ ነው ብሎ ለሚያምንበት ክብርን፣ ስለትን፣ ምስጋና፣ ልመናን ወዘተ የሚያቀርብበት የሕይወት ስርዓት (life style) ነው፡፡ ይህን ስርዓት ብዙ ሀገራት ከነባር ባህላቸው ጋር አያይዘው እንደሚከውኑ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ለምሳሌ በዘመናችን ከፍተኛ ስልጣኔ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቻይና ከዘመናዊ ታሪኳ (modern history) በፊት “አኔሚዝም”፣ ሻመኒዝም” እና ሌሎች ባህላዊ የአምልኮ ስነ-ሥርዓቶችን ስትከተል እንደነበረ Wikipedia the free encyclopedia ይገልጻል፡፡
የክርስትና እምነት (ሃይማኖት) ከመስፋፋቱ በፊት የወላይታ ሕዝብም ከቻይና ባልተናነሰ መልኩ ባህላዊ አምልኮ ሲያካሂድ እንደነበረ ይታመናል፡፡ በሕይወት ፍስፍና፣ በማህበራዊ የሕይወት መስተጋብር፣ በስነ-ምግባር እና በራስ መተማመን ጠንካራና ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው በማመን የወላይታ ሕዝቦች ባህላዊ አምልኮ ሲያመልክ ነበር፡፡
እንዲህ እንደ አሁኑ ዘመን በርካታ ቁጥር የሌላቸው የሃይማኖት ድርጅቶች ከመምጣቻቸው በፊት የወላይታ ሕዝብ የተጠናከረና የተደራጀ ባህላዊ የአምልኮ ሰረዓት ነበረው፡፡
ይህን አሰገራሚ የሆነ መንፈሳዊ ስርዓት በተመለከተ የወላይታ ባህላዊ አምልኮ መልክ ምን ይመስል ነበር? የአምልኮው አፈጻጸምስ? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሀተታ የያዘ ፅሑፍ በዚህ እትም ልናቀርብ እንሞክራለን፡፡
የወላይታ ብሔር ብዙ የጎሣ ስብጥሮችን በውስጡ የያዘ ሲሆን እነዚህ ጎሳዎች የየራሳቸው ባህላዊ አማልክት (Mayzza xoossati) እንደነበሯቸው የተለያዩ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ቡቡላ የሚያመልከው ሙሉጉሻ፣ ወሼሻ የሚያመልከው እንግላላ፣ ወምግራ የሚያመልከው ጋማና፣ አጋርሷ የሚያመልከው ዳይዳንታ፣ ዛምቦቼ የሚያመልከው ሀዉዙላ፣ አይፈርሷ የሚያመልከው ኪቶሳ… ወዘተ እንደነበሩ እድሜ ጠገብ ሽማግሌዎችና የፅሑፍ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ነባር ባህላዊ አምላክ ያልነበታቸው የጎሣ አባላት ከላይ ከተጠቀሱት አንዱን መርጠው ከነባሩ ባህላዊ አምልኮ ቄስ ጋር በመስማማት ያመልኩ እንደነበርም ይወሳል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ምንም እንኳን ነባር ባህላዊ አምላክ ያልነበራቸው የጎሣ አባላት ቢኖሩም እርስ በርስ በመስማማት ለአምልኮ ምቹና ሰፊ በሆነ ሜዳ ብዙ ቅርንጫፍ ማውጣት የሚችል ዛፍ ተክለው በዚያ ዛፍ ስም የሚያመልኩም እንደነበሩ ይነገራል፡፡
ብዙ ጊዜ የተለመደ ባይሆንም እነዚህን ከላይ የተገለጹ ሁለት አማራጮችንም መቀላቀል ያልወደደ አንድ አባወራ የአባቴ አምላክ እያለ በግሉ የተለያዩ ነገሮችን ያመልክ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አማልክት ይገኛሉ ተብሉ የሚገመተው በተራራዎች፣ በወንዞች፣ በመካነ መቃብሮች፣ በታላላቅ ደኖች፣ በጫካዎች፣ በደብሮች፣ በዋሻዎችና በቤት ምሶሶ ነበረ፡፡
እነዚህ አማልክት ወላይታዎች የሚያመልኩበት ዋና ምክንያት ከአደጋ እንከላከሏቸውና ሀሳባቸውን እንዲያሳካላቸው ነበር፡፡ ሕዝቡ ልመናቸውና ስለታቸውን የሚያመልኩትን ባህላዊ አምላክ (mayzza xoossaa) በመጥራት “አንተ ለእኔ ይህንን ይህንን ካሳካህልኝ ይህንን እሰጣለሁ” ብለው ስለት የሚቀያቀርቡለትን እንስሳ ወይም ግዑዝ ስም እየጠሩ ይሳሉለታል፡፡ በብዛት ኮርማ በሬ፣ በግና ፍየል ነበረ የሚሳሉለት፡፡ ልመናቸው ከሰመረ ወደ ተሳሉበት ባህላዊ አምላክ ወኪል (ባህላዊ ቄስ) ዘንድ ሄዶ ስለታቸውን ያደርሳሉ፡፡ መሻቱ ያልተሳካለት ቢኖር ለባህላዊ ቄሱ “አልተሳካልኝም” ብሎ ሲነግረው ባህላዊ ቄሱ “የአባቴ አምላክ እንደ ሐጢያት አይቁጠርብህ፣ ቅር አይበልብህ (Nessi gometoppo…)፣ ሌላ አምላክ ያሳካልህ” ብሎ ቀደም ሲል የተሳለውን ስለት ምሮት ያሰናብተዋል፡፡
ወላይታዎች ባህዊ አማልክትን የሚያመልኩት በባህላዊ አምልኮ መሪ አመካኝነት ነበር፡፡ ባሕላዊ ቄስ የሚሾመው በሕዝብ በዓላትም የባህላዊ አምልኮ ባለቤት በሆኑ ጎሳ አባላት ነበር፡፡ የባህላዊ አምላክ (mayzza xoossaa)መሪ ወይም ባህላዊ ቄስ ሆኖ የሚሾም ግለሰብ ነባሩ ባህላዊ አምልኮ በነበረበት አከባቢ ከሌሎች ቀደም ብሎ የመስፈር፣ ጫካውን መንትሮ የእርሻ ማሳ ያስፋፉ እና በሌሎች ሰዎች ዘንድ ጥሮ ስም (ተቀባይነት) ያለው ሲሆን ነው፡፡
ይህ “ቄስ” ባህላዊ አምልኮ ለሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ እኩል የማሰብ እና በእነሱ ስም ፀሎትና ምስጋና ለአምላኩ የማድረስ ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ ባህላዊ ቄሱ ከሞተ የሟቹ ቤተ-ዘመድ (Dabboy) በመሰብሰብ የሟቹን በኩር ልጅ በባህላዊ ቄስነት ይሰይሙታል፡፡ ተተኪው ከሹመት በፊት እንዲገረዝና ባለትዳር እንዲሆን ባህሉ ያዝዛል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን የአባቱ ሹመት እሱን የሚመለከተው በመሆኑ በስነምግባር ምስጉን ሆኖ ከቤተዘመድ ሁሉ ምስክርነት ያገኘ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
በባህላዊ አምልኮ ሥርዓት መሰረት ባህላዊ ቄስ በቄስነት ከተሰየመበት ጊዜ ጀምሮ ከቀይና ከጥቁር ማግ የተሰራ ካባ (maddaa) ይለብሳል፣ ጥምጣም በራሱ ይጠመጥማል፡፡ የብር አምባር (sagaayuwaa)፣ ካዎቲያ (kawottiyaa) እና “ትሪያ” (Tiriyaa) የሚባል ከብር የሚሰራ የጣት ቀለበት ያጠልቃል፡፡
ባህላዊ ቄስ በባህላዊ አምላክ እና በአምላኪው ሕብረተሰብ መካከል እደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን የአምላኪው ግለሰብ መሻት እንዲሳካለት ባህላዊ አምላኩን (mayzza xoossaa)ውን ረቡዕ፣ ዓርብ፣ እሁድና ሰኞ የአምላክ መሻት (Xoossaa Qammaa) እንደሚማጸንና የባህላዊ ፀሎት እና ተያያዥ አምልኳዊ ሥራዎች (Eeqaa) እንደሚፈጽም አባቶች ያስረዳሉ፡፤ በእነዚህ ቀናት አማልክት ይገኞሉ ተብሎ የሚገመተው በተራራ፣ በጫካ፣ በዋሻ፣ በቤት ምሶሶ አከባቢ ስለሆነ ለባህላዊ አማልክት ልመናና ስለት ይደረጋል፡፡ በተጠፈቀሱ ቀናት ድንገተና አደጋና ለሕይወት የሚያሰጉ ገጠመኞች ወይም በሽታዎች ሲደርሱ ለባህላዊ አምላክ ስለት ይቀርባል፡፡ መሻቱ እንዲሳካለት የሚፈልግ ግለሰብ አማልክት ይገኛሉ ተብሎ ከላይ ወደተጠቀሱ ቦታዎች ዞሮ በመስገድ አድነን፣ አውጣኝ፣ ማረኝ፣ ወዘተ በማለትና ከተሳካለት ለአምላኩ የሚያቀርብለትን ስለት በስም እየገለጸ ይማጠናል፡፡
የወላይታ ባህላዊ አማልክት ዝክር በአብዛኛው በዓመት አንድ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን እለቱ የ”ሻሻጋ” ዕለት (shaashshiga gallasaa) በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ቀን በባህሉ የደስታና የምስጋና ቀን ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በእለቱ በባህላዊ ቄስ (Eeqiyaaga) ደጃፍ ላ ኮረማ በሬ ታርዶና ቦርዴ ተጠምቆ በባህላዊ ቄሱ አማካይነት ለባህላዊ አምላኩ የምስጋና መስዋዕት (yarshshuwaa) ይቀርብለታል፡፡
የምስጋና መስዋዕት (yarshshuwaa) ስነ-ሥርዓት ጊዜ ምዕመናኑ ለአምላካቸው ክብር ቄሳቸውን አጅበው በታላቅ ክብርና ተመስጦ ፊታቸውን መሪው ወደ አሳያቸው አቅታጫዎች በማዞርና በመስገድ ሂደቱን ፍፁም መንፈሳነት በተሞላበት ስሜት ያከናወናሉ፡፡ በመጨረሻም ባህላዊ ቄሱ ምዕመናኑ በተዘጋጀው ቦታ ተቀምጠው የተዘጋጁ ባህላዊ ምግብና መጠጥ እንዲበሉና እንዲጠጡ መርቆ (ባርኮ) ያስጀምራል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ተዘውትሮ ለግብዣ የሚቀርበው ምግብ የተጠበሰና ጥሬ ስጋ ሲሆን መጠጡም ቦርዴ ነው፡፡ ለአመጋገባቸው ከአምልኳቸው ጋር አያይዞ ትርጉም ስለሚሰጡ ጥብስ በቅድሚያ ከቄሱ እጅ በመውሰድ ሁሉም ከተቀመሱ በኋላ ጥሬ ስጋውን በደንብ ይበሉታል፡፡
“ቦርዴ” ደግሞ በመላው ወላይታ ዘንድ በተለያዩ የግብዣ ቦታዎች ሲቀርብ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መጠጥ ሲሆን ምዕመናኑም “ሳያለያየን፣ ሳይጠፋን ለዚህ ታላቅ የምስጋና ቀን ያደረሰን አምላካችን (Nu Xoossay) ይመሰገን”፡፡ እያሉ አንድ ቅል ለሁለት በመያዝ በጋራ (በብሔሩ ቋንቋ “ዳግድ” ይጠጣሉ፡፡
በመዝጊያ ስነ-ስርዓት ቄሱ ለምዕመናን የተጀመረው አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የጥጋብና የደስታ እንዲሆንላቸው ቡራኬ በመስጠት ይሸኛል፡፡ አጠቃላይ ስርዓቱም በዚህ ይፈጸማል፡፡
ማጠቃለያ
የወላይታ ባህላዊ አምልኮ በሕዝቡ ሁለንተናዊ ሕይወት፣ የሥራ ሰዓት እና በደን አጠባበቅ ዙሪያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አዎንታዊ እንድምታ የነበረው መሆኑን ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ ሰፋ ያለ ጥናት ለማድረግ የሚፈልጉ ምሁራን ካሉ እጅግ በጣም ይበረታታሉ፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza