የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ልማት በማበረታታት ለማስፋፋት መንግስት ልዩ ልዩ አዋጃች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን በማዉጣት ወደ ትግበራ ከተገባ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ ከዚህም የተነሳ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ በመምጣቱ ከዘርፉ የሚጠበቀዉን ተኪ የሌለዉን ሚና ከመጫወት አኳያ በሀገራችን፣ በክልላችንም ሆነ በዞናችን አበራታች እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት የወላይታ ዞን አስተዳደርም በዞኑ እየተካሄደ ባለዉ የልማት እንቅስቃሴ ዉስጥ የግሉ ኢንቨስትመንት እየተጫወተ የሚገኘዉንና ሊጫወት የሚችለዉን ተኪ የሌለዉን ሚና በመገንዘብ፣ ልማቱን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ዞኑን ለኢንቨስትመንት ምቹ አከባቢ እንዲሆን ለማድረግ ከምን ጊዜዉም በበለጠ እጅግ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የወላይታ ዞን ለግሉ ኢንቨስትመንት መስፋፋት ወሳኝ ሚና መጫወት ከሚችሉት መሠረተ ልማቶች አኳያ ሲታይ ከሌሎች በክልላችን ከሚገኙ ዞኖች በአንፃራዊ ሁኔታ የተሻለ አቅርቦት ያለዉ ከመሆንም በተጨማሪ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጡም በክልላችን እምብርት ላይ የሚገኝ የመሆኑን ያህል ልማታዊ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሠማርተዉ ተጠቃሚ ሆነዋል ባይባልም የማይናቅ ቁጥር ያላቸዉ ባለሃብቶች ተሠማርተዉ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገታችን የየድርሻቸዉን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
በዞኑ ዉስጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2009 ዓ/ም መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ባለዉ መረጃ መሠረት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሠማራት 273 ባለሃብቶች ፈቃድ ተሰቶላቸዉ በማልማት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የፕሮጀክቶቹን ብዛት በየዘርፋቸዉ፣ ያስመዘገቡት ካፒታል በየዘርፉ ይፈጠራል ተብሎ የታቀደና የተፈጠረ ለዜጎቻችን የሥራ ዕድል እንዲሁም ፕሮጀክቶች የሚገኝበት የአፈፃፀም መረጃ እንደሚከተለዉ እንመለከታለን፡፡
በማልማት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ብዛት በየክፈለ- ኢኮኖሚ ያስመዘገቡት ካፒታል በየዘርፉ፣
ከላይ ለመመልከት እንደሚቻለዉ በአጠቃላይ 273 ፕሮጀክቶች በዝርዝር በተጠቀሱት ዘርፎች ለመሠማራት በድምሩ ብር 1.34 ቢሊዮን ካፒታል በማስመዝገብ የኢንቨስትመንት ፊቃድ ተሰጥቷቸዉ በማልማት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በዝርዝር ስንመለከትም በካፒታል ድርሻ ሆቴልና ቱሪዝም 37.68% ሆኖ ከፍተኛዉን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ በመቀጠልም ግብርና 21.14%፣ ኢንዱስትሪ 12.83%፣ ማህበራዊ ዘርፍ 12.21%፣ ሪልስቴት 9.4% እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎት 6.9% እንደየቅደም ተከተላቸዉ ድርሻ የያዙ ናቸዉ፡፡
አጠቃላይ 273 ፕሮጀክቶችን በሁለት ለመክፈል የተሞከረ ሲሆን ከአጠቃላዩ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት /አገልግሎት/ መስጠት የጀመሩት 146 ሲሆኑ፣ በከፊል ማምረት/ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት 65፣ ቅድመ ትግበራ ላይ የሚገኙ 52፣ ፈቃድ አዉጥተዉ ወደ ቀጣይ እንቅስቃሴ ያልገቡ 10 በመሆናቸዉ በድምሩ 273 ወይም 96% ተስፋ ሰጪ የልማት እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙ ናቸዉ፡፡
መንግስት ለግሉ ኢንቨስትመንት መስፋፋት ከሁሉም ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ዘርፉን ከሚያበረታታበትና ከሚደግፍበት ምክንያቶች አንዱና ዋነኛዉ ከዘርፍ ትርጉም ያለዉን የመቀጠር ዕድል አግኝተዉ ዜጎች ኑሯቸዉ ተሻሽሎና ሕይወታቸዉ በተሻለ ደረጃ ተለዉጦ ለማየት ካለዉ ራዕይ ነዉ፡፡
በዚህም ረገድ ከፍ ብሎ በዝርዝር እንደቀረበዉ በዞናችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዉ በተለያየ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ልማታዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት 273 ፕሮጀክቶች በድምሩ 14,848 ዜጎቻችን ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ ዕድል እንዲፈጠሩ ለመመልከት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በጥሩ ጎኑ ስንመለከት አፈጻጸሙ አበረታች ነዉ ብሎ መዉሰድ ይቻላል፡፡ ይህም በግብርና 57.75% የበላይነት እንዲሁም ሆቴልና ቱሪዝም 15.34% ተከታታይነትና የሌሎችንም መጠነኛ ድርሻ የያዘ ነዉ፡፡
እንደአጠቃላይ 273 በአሁኑ ወቅት በልማት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በድምሩ በፕሮፖዛላቸዉ ያቀረቡት ዕቅድ እንደሚያሳየዉ 20,122 ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደነበረ መረጃዎች የሚሳዩ ሲሆን፣ በተጨባጭ የተፈጠረ የሥራ ዕድል ግን 14,484 በመሆኑ ይህም ከመቶ 72% እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የዚህን ዓመት 14,484 የሥራ ዕድል ፈጠራ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተፈጠረዉ 13,575 ጋር ሲነጻጸር 109% እንደሆነ ለማየት የሚቻል ስለሆነ በየዓመቱ መሻሻል እያሳየ የሚሄድ በመሆኑ አበረታች ነዉ ለማለት ይቻላል፡፡
ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ስርጭት አንጻር በዞኑ ከተመዘገቡ 273 ፕሮጀክቶች 142 ያህሉ /52 በመቶ/ በሶዶ ከተማ፤ 23 ፕሮጀክቶች በቦዲቲ ከተማ /8 በመቶ/፤ 17 ፕሮጀክቶች በሁምቦ ወረዳ /6 በመቶ/፤ 14 ፕሮጀክቶች በዳሞት ወይዴ /5 በመቶ/፣ በኦፋ፤ በአረካና በሶዶ ዙሪያ በእያንዳንዳቸዉ 4 በመቶ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች የሚገኙ ሲሆን የፕሮጀክቶቹ ስርጭት በሶዶ ከተማ ዙሪያ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህም መሠረት በአጠቃላይ በዞኑ ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃድ ከተሰጣቸዉ 273 ፕሮጀክቶች ዉስጥ 142 (52%) በሶዶ ከተማ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመቀጠል ቦዲቲ ከተማ 23 ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን፣ ሁምቦ ወረዳ 17 ፕሮጀክቶችን ይዞ በ3ኛ ደረጃ የሚገኝ ሲሆን ሌሎችም ወረዳዎች አነስተኛ ቢሆንም ድርሻ ድርሻቸዉን ይዘዉ ሲገኙ በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ፣ በዳሞት ፑላሳ ወረዳ እና ዳሞት ጋሌ ወረዳ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃድ ያወጡ ባለሃብቶች ብዛት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza