በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሕዝበ- ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ተጀመረ
አርባ ምንጭ ጥር 29 ቀን 2015 (ኢዜአ)..በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሕዝበ- ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ውሳኔ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና አስተባባሪ ወይዘሪት መቅደስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት የድምጽ አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ዛሬ ከማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው በ31 ማዕከላት ሥር በሚገኙ 3 ሺህ 771 ምርጫ ጣቢያዎች ነው።
ህዝብ ውሳኔ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች መሆኑን ጠቁመዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም ቦርዱ ባለፉት አራት ቀናት ለድምፅ አሰጣጥ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ሙሉ ለሙሉ አሰራጭቷል ብለዋል።
በየደረጃው የተሰማሩ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎችና የጸጥታ አካላት የምርጫውን ስነ-ስርዓት ለማስፈጸም በተቀናጀ ሁኔታ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ እየተካሄደባቸው ከሚገኙ ዞኖች መካከል ኢዜአ ቅኝት ባደረገበት ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ዶይሳ አሸም ሁለት ምርጫ ጣቢያ ድምፅ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ታዛቢዎች በተገኙበት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ የድምፅ መስጫ ሳጥን ባዶ መሆኑ ከተረጋገጠ እና የሚስጥር ቁልፍ ከተሰጠው በኋላ በቃለ ጉባኤ ተፈራርመዋል።
በተመዘገቡት መራጮች ልክ የድምፅ መስጫ ወረቀት መዘጋጀቱንም መረዳት የተቻለ ሲሆን በምርጫ ጣቢያዉ መራጮችም ከ12:00 ሰዓት ቀደም ብሎ በድምፅ መስጫ ጣቢያዉ ተገኝተው ሰዓቱ እንደደረሰም ድምፅ መስጠት ሥነ ሥርዓት መጀመሩን አረጋግጧል።
በምርጫ ጣቢያው 600 ሰዎች የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የምርጫ ጣቢያው ምርጫ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፅዮን ኦሎሎ ገልፀዋል።
በሕዝበ ውሳኔው ላይ 5 ሺህ 274 የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች እንደሚሰማሩ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል መግለጹ ይታወሳል።
ቦርዱ በክልሉ ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከ3 ሚሊየን በላይ መራጮች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውም እንዲሁ ቦርዱ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza