የህዝበ ውሳኔ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ ያስተላለፉት መልዕክት
ወላይታ ሶዶ፣ ጥር 29/2015 (ወ/ዞ/መ/ኮጉ/ መምሪያ)
የተከበራችሁ፦
ሠላም ወዳድ የወላይታ ህዝቦች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ሴቶች እና ወጣቶች ፣ አመራር አካላት፣
የፀጥታና ሰላም ተቋማት፣የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች፣የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማት፣ ሲቪክ አደረጃጀቶች ፣
ክቡራትና ክቡራን፦
ከሁሉ አስቀድሜ የህዝቦቻችንን የአደረጃጀት ጥያቄ ተከትሎ ተጠቃሚነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ታልሞ በየደረጃው በሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች ይሁንታ በማግኘት የተፈፀመው ታሪካዊው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ህዝበ ውሳኔ ምርጫ በወላይታ ዞን በሰላም መጠናቀቁን በዞናችን አስተዳደርና በራሴ ስም አበስራለሁ።
እንኳን ደስ አላችሁ!!እንኳን ደስ አለን!!!
በዚህ አጋጣሚ ምርጫው በዞናችን ባሉ በ1ሺህ 1መቶ አሥራ ሁለቱም ጣቢያዎች በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመጠናቀቁ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ እየገለጽኩ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ላደረጉ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን በወላይታ ዞን አስተዳደርና በራሴ ስም ላቀርብ እወዳለሁ።
በተለይም ለምርጫው መሳካት ለደከሙ ለፌደራልና ለክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ለዞን፣ለወረዳና ከተማ እንዲሁም በየደረጃው ላሉ አመራሮች ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ከምርጫው ጋር በተያያዘም የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ሌት ተቀን ለደከሙ ለደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፣ለዞናችን ፓሊስና ሚሊሻ እንዲሁም ለአጠቃላይ የጸጥታ መዋቅር አባላት፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለኃይማኖት መሪዎች፣ መንግስት ሠራተኞች፣ ለሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች፣ ለነጋዴ ማህበረሰብ፣ ለሚዲያ ተቋማት፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ለመላው የዞናችን ህዝቦች በራሴና በዞኑ አስተዳደር ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ምርጫ ህዝቡ ፍላጎቶቹን በሰላማዊ መንገድ የሚገልፅበት፣ የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበትና የሀሳብ ልዕልና የሚከበርበት፣ የታጋሽነትና የመደማመጥ፣ የመከባበርና የመቻቻል ባህል የሚንፀባረቅበት የዴሞክራሲ መገለጫና ህዝቡ በቀጥታ የሚሳተፍበት መሆኑን ባረጋገጠ መልኩ ህዝቡ አሉባልታዎችን ወደ ጎን በመተው ከሌሊቱ 9:00 ሰዓት ጀምሮ በመውጣት መብቱን አስከብሯል፤ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ሰጥቷል።
የምርጫውን የመጨረሻ ውጤት በሚመለከት የምርጫ ቦርዱ በራሱ አሠራር መሠረት የሚገልጸው በመሆኑ በትዕግሥት ልንጠባበቅ ይገባል።
በበሌ የምርጫ ማዕከል፣ ሶርቶ ቀበሌ፣ ሶርቶ አንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ የተፈጠረው ስህተት በቦርዱ አሠራር መሠረት የተስተካከለና የዚሁ ጣቢያም ምርጫ በሰላማዊ መንገድ የተጠናቀቀ ሲሆን አጥፊ የቀበሌ አመራር አካላት በተቀመጠው አሠራር መሠረት ተጠያቂ ይሆናሉ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪክና በባህል፣ በስነ-ልቦና፣ በመልክአ ምድራዊ አሠፋፈርና በሌሎች የጋራ ዕሴቶቻችን ሊበጠስ በማይችል መልኩ የተሳሰሩ ህዝቦች ሀገር ናት። እናም ከማንነት በተጓዳኝ የጋራ ዕሴቶቻችንን በማጎልበት ለጋራ ሀገር ግንባታ ሂደት ስኬታማነት በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቅብናል፤ አንድነትና አብሮነት ትልቅ አቅም ነውና።
ሀገራችን እያጋጠሟት ያሉትን ፈተናዎች በአሸናፊነት እየተወጣች ሲሆን አሁንም የኃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሀገራችን ፈተናዎችና የአብሮነትና የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ጠላቶች በመሆናቸው በጽናት ልንታገላቸው ይገባል።
በሌላ በኩል በተዛባ እይታ የራስን አግዝፎ የሌላን ማንኳሰስ፣ የራስን ክቦ የሌላውን የማጠልሸት አባዜ የተጠናወታቸው፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ የሚዘሩ፣ ከአብሮነት ይልቅ ጫፍ የወጣ ግለኝነትና ከእውነታ ይልቅ ስሜተኝነትን የሚሰብኩ የፅንፈኝነትና የአክራሪነት አስተሳሰቦችና ተግባራት ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችንና ለጋራ ልማታችን ፀር በመሆናቸው ልናወግዛቸው ይገባል።
የዞኑ መንግስት ሌብነት ለልማታችን ፀር በመሆኑ ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ዜጎች ከእኩይ ምግባር መታቀብ ብቻ ሳይሆን የድርጊቱ ተዋናይና ተባባሪዎቻቸውን በማጋለጥ የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅብናል።
አምላክ ለሀገራችን የቸረውን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ጸጋዎቻችንን ለህዝቦቻችን የላቀ ተጠቃሚነት ማዋል የምንችለው በጎጥ፣ በሀይማኖት፣ በጎሣ ፣ በቋንቋና በብሄር በመከፋፈል ሳይሆን ዕውቀታችንና ክሂሎታችንን፣ አመለካከታችንና ጥበባችንን፣ ጉልበታችንና ቀልባችንን በማሰባሰብ ጠንክረን ስንሠራ ብቻ መሆኑ ሊሰመር ይገባል።
የምናልመውን የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ሰላማችንን ማስቀጠል ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ሠላም ወዳዱ መላው የዞናችን ነዋሪ ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ከፀጥታ መዋቅሮቻችን ጋር በመቀናጀት ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ የድርሻችንን በተነሳሽነት እንድንወጣ በዞናችን አስተዳደርና በራሴ ስም ጥሪ ላቀርብ እፈልጋለሁ።
የሀገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት፣ የህዝቦቻችን አንድነትና መስተጋብር እንዲሸረሸር ብሎም ሀገር እንድንፈርስ ሌት ተቀን ከሚባዝኑ የውጭ እና ከእነርሱ በሚወረወር ፍርፋሪ ከሚንቀሳቀሱ ሀሰተኛ ሚዲያዎች ለሚለቀቁ አሉባልታዎች ጆሮአችንን ልንሰጥ አይገባም።
የምርጫው ሥራ በሰላም እንዲጠቀቅ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በተነሳሽነት ለተወጡ አካላት በድጋሚ ልባዊ ምስጋናዬን እየገለፅኩ አርአያነት ያለው ጥረታችሁ በድህረ ምርጫ ተግባሮቻችን፣ በቅርቡ በሚበሰረው የዘንድሮ ሥነ አካላዊ የበጋ ተፋሰስ ልማት፣ የገቢ አሰባሰብ፣ የመስኖ እና የቀጣይ የበልግ እርሻ ልማት እንዲሁም በሌሎች የመንግስት አገልግሎቶቻችን ህዝባችንን ለማርካት በላቀ ተነሳሽነት እንድንንቀሳቀስ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ! አመሠግናለሁ።
አቶ አክሊሉ ለማ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza