• Call Us
  • +251465512106

Daguwa/ዳጉዋ/

ዳጉዋ /Daguwa/

ዳጉዋ/ደቦ በአንድ መንደር የሚኖሩና ተቀራራቢ የሆኑ በቁጥር 10 እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች በህብረት የሚሰሩት ሥራ ነው፡፡ ዳጉዋ/ደቦ/ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል የሚሳተፍበት ሲሆን የደቦው አባላት ሥራውን እየሰሩ አንድ ቀን ሙሉ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ዳጉዋ (ደቦ) ተብሎ የሚጠራው በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት ከ10 በላይ ሆኑ ሰዎች በቡድን በቡድን በመሆን በጥቂት ሰዎች ሊሸፈኑ የማይችሉ ሥራዎችን በህብረት ለማከናወን የሚጠቀሙበት ባህላዊ በሥራ የመረዳዳት ስርዓት ነው፡፡ በተለይም የእርሻ ሥራ፣ የአዝመራ፣ የኩትኳቶ፣ የእህል አጨዳ፣ የመወቃትና ሌሎችም በህብረት የሚከናወኑ ተግባራት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዳጉዋ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት ከሌሎቹ ማለትም ከሀሽያ እና ከዛይያ ይለያል፡፡ የዳጉዋ ስርዓት በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት ሆኖ ብዙ ዝግጅት ተደርጎ የሚከናወን ነው፡፡

የአካባቢው ሴቶችም ዳጉዋ ወዳለበት ቤት ተሰባስበው ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት የሚያግዙ ከመሆኑም በተጨማሪ የሰፈር ሴቶች ከየቤታቸው ምግብና መጠጥ በማምጣት ድጋፍ ሚያደርጉበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ በአንድ አካባቢ/ሰፈር የሚገኙ ሴቶች ዳጉዋ ወዳለበት ቤት የምግብና የመጠጥ ድጋፍ የሚያደርጉበት ስርዓት በብሔሩ አጠራር ያጋኑዋ/Yaganuwa/ ይባላል፡፡ ‘ያጋኑዋ’ ያመጣች ሴት ምን ዓይነት ምግብና መጠጥ እንዳመጣች ዳጉዋ ለጠራች ሴት ካሳየች በኋላ ታስረክባለች፡፡ ዳጉዋ የተጠራበት ቤት እናት ያጋኑዋ ተረክባ ‹‹በደስታና በሰርግ ውለታ መላሽ ያርገኝ›› በማለት የመጣላትን ምግብና መጠጥ በደስታና በፈገግታ ትረከባለች፡፡

ዳጉዋ በሚካሄድበት አካባቢ የሚገኙ ሴቶች የሚያመጡት ምግብና መጠጥ በአዘቦት ቀን ህብረተሰቡ የሚመገባቸው ናቸው እንጂ ለሰርግና ለበዓል የሚዘጋጁ ምግቦች አይደሉም፡፡ ምግቦችም ሆኑ መጠጦች በአከባቢው የሚዘወትሩና ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ናቸው፡፡ በዳጉዋ ባህል መሠረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ሰፋፊ ማሳዎችን ማረስ፣ መኖሪያ ቤት ለመሥራት መሰረት መደልደል፣ ዘር መዝራት፣ አረም ማረም እና የመሳሰሉት ተግባራት ናቸው፡፡ በዳጉዋ ስርዓት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በየቡድናቸው በመሆን በአንድ ቀን ውስጥ እጀግ በጣም ሰፊ የሆነውን ሥራ በመሥራት ለባለዳጉዋ ግለሰብ የሚያስረክቡበት ነው፡፡ በዳጉዋ ስርዓት በየቡድኑ ያሉ ሰዎች እየዘፈኑና እየዘመሩ አንዳንድ ጊዜም አንዳቸው አንዳቸውን እየቀለዱና እየተሳለቁ ሥራውን በአጭር ሰዓት ውስጥ ለማጠቃለል ጥረት ያደርጋሉ፡፡

ለዳጉዋ ስርዓት የሚወጣው ወጪ እንደሀሽያ እና ዛይያ ቀላል ሳይሆን እንደተሰበሰበው ህዝብ ብዛት በጣም ከፍ ልል ይችላል፡፡ ምክንያቱም በአንድ አካባቢ ካሉ የሰፈር ሰዎች በተጨማሪ ከሌሎች አካባቢዎችም የሚመጡ እንግዳ ሰዎች ስላሉ የሚቀርቡ ምግቦችና መጠጦች የአዘቦት ጊዜ ምግቦች ቢሆኑም እንኳ የተመረጡ ናቸው፡፡ ዳጉዋ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓቱ የሚከናወነው የእርሻ ሥራ ከሆነ በእርሻ መሣሪያ ከሚቆፍሩ ሰዎች በተጨማሪ እንደየሁኔታው ከ10 በላይ በሆኑ ጥማድ በሬዎች ሊያርሱ ይችላሉ፡፡ በዳጉዋ ስርዓት ምግብ የሚበላው በምሳ ሰዓት ብቻ ሲሆን እንደየግለሰቡ ፍላጎት የጠማው ሰው ካለ በመሀልም ከተዘጋጀው መጠጥ ሊቀርብላቸው ይችላል፡፡

በሀሽያ፣ በዛይያ እና በዳጉዋ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት የማረስ፣ የመኮትኮት፣ የመዝራት እና ምርት የማሰባሰብ ሥራዎች ሊከናወኑ የሚችሉ ሲሆን የጎጆ ቤትም ሆነ የቆርቆሮ ቤት ለመሥራት መሠረት የመደልደልና ግድግዳ የመፍለጥ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በስርዓቱ ሥራውን መምረጥ የለም፡፡ ማንኛውም ዓይነት ሥራ በጋባዡ ግለሰብ ፍላጎት መሠረት ሳይመረጥ ይከናወናል፡፡ ሥራው ከቀኑ እስከ 11 ሰዓት ድረስ በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል ሲሆን ከ11 ሰዓት በኋላ ከሩቅ አካባቢዎች የመጡ ግለሰቦች የሚሄዱ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች እንደየሥራው ሁኔታ እስከ 12 ሰዓት ድረስ እየሰሩ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ 

በአጠቃላይ የወላይታ ብሔር ቤት ለመሥራት፣ መቃብር ለመቆፈር፣ ምሰሶ ለመጎተት፣ ለመኖሪያ ቤት ግድግዳ ለመፍለጥ፣ የመኖሪያ ቤት የሚሠራበት ቦታ /መሠረት/ ለመደልደል እና በአንድና በተወሰኑ ጥቂት ሰዎች ጉልበት ሊከናወኑ የማይችሉ ተግባራትን ማከናወን ሲፈለግ የመረዳዳትና አብሮ ተባብሮ የመሥራት ባህል ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፡፡ ይህ በሥራ የመረዳዳት ባህል በህዝቡ ውስጥ ረጅም ዘመን የቆየ የህዝቡን የአንድነት፣ የአብሮነትና የመቻቻል ባህል የሚያጎለብት ነው፡፡ ይህ በእርሻና መሰል ተግባራት ላይ የሚከናወነው በሥራ የመረዳዳት ባህል በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡