የሀሺያ፣ ዛይያ እና ደጉዋ ባህል በወላይታ
በታደለ ፎላ
ባህል ሲባል በአንድ ማህበረሰብ አካባቢ የተገደበ ሆኖ የአንድ አካባቢ ህብረተሰብ ማንነት መገለጫ ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ማህበረሰቡም ይህንን ባህል ነው በማለት በሙሉ ልብ አምኖ የተቀበለበት የማህበረሰቡ ቅርስ ነው፡፡ ባህል ከተጠቃሚው ማህበረሰብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሆኖ በዕለት ተዕለት ኑሮና ተግባሩ አብሮ የሚዘወተር የዚያ ማህበረሰብ አባል እንደቅርስ እና ሀብት አድርጎ የሚቆጥርበት ነው፡፡ ባህል በአንድ አካባቢ ማህበረሰብ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በዕለት ተዕለት ክንዋኔ የሚገለጽ፣ የዚያ አካባቢን እንጂ ዓለምን በአንድ ጊዜ ማሳየት የማይችልና በአንድ አካባቢ ተግባራት የተገደበ ነው፡፡ ባህል የአንድን ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤን የሚገልጽና የማህበረሰቡን ምናብን የመግለጽ ባህርይ ያለው ነው፡፡ ባህል የአንድ ማህበረሰብ የባህላዊ አለባበስ፣ የአስተዳደር ስርዓት፣ የጋብቻ፣ የአመጋገብ፣ የግርዛት፣ በሥራ የመረዳዳት፣ የሰርግና የመሳሰሉት ተግባራትን አጠቃልሎ የያዘ የማህበረሰቡን ማንነት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የማሳየትና የማንጸባረቅ ኃይል ያለው ነው፡፡
የወላይታ ብሔርም ረጅም ዘመናት በኖረበት በዞኑ አካባቢዎች በወቅቱ የነበሩ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረጉ ማህበራዊ ስርዓት ፈጥረው ይተዳደሩ እንደነበር የብሔሩ አፈ-ታሪክና የተለያዩ ድርሳናት ያትታሉ፡፡
የወላይታ ብሔር የዛሬውን የወላይታ ምድር ቋሚ ካርታ በመያዝ መኖሪያቸው አድርገው መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የሚተዳደርበትን ያልተጻፈ ባህላዊ መተዳደሪያ ሕግ አውጥተው ለሕጉ ተገዢ በመሆን ይኖሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ ባህላዊ የወላይታ መተዳደሪያ ሕግ በብሔሩ አባባል ሴራ / Seeraa/ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሴራ /Seeraa/ በውስጡ በርካታ ንዑስ መተዳደሪያ ደንቦችን አጠቃልሎ የያዘ ሆኖ ከትንሽ ወንጀል አንስቶ እስከ ትልቅ የነፍስ ግድያ ወንጀል ድረስ ያለውን የሚዳኝበት ስርዓት ነው፡፡ ሌላው በወላይታ ብሔር ዘንድ ቤት ለመሥራት፣ መቃብር ለመቆፈር፣ ምሰሶ ለመጎተት፣ ለመኖሪያ ቤት ግድግዳ ለመፍለጥ፣ የመኖሪያ ቤት የሚሠራበት ቦታ መሠረት ለመደልደል፣ በአጠቃላይ በሥራ ለመረዳዳት እና ሌሎች በአንድና በተወሰኑ ጥቂት ሰዎች ጉልበት ሊከናወኑ የማይችሉና የበርካታ ሰዎችን ትብብር የሚፈልጉ ተግባራትን ማከናወን ሲፈለግ ሁሉም ሰው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያደርጉበት መተዳደሪያ ደንብ ሴራ /Seeraa/ አስፈልጓቸዋል፡፡ በመሆኑም ጥንታዊ ወላይታዎች የራሳቸውን ማህበራዊ ስርዓት ሴራ /Norms/ ፈጥረው በዛው ይተዳደሩ እንደነበር የብሔሩ አፈ-ታሪክና ድርሳናት ያብራራሉ፡፡
ወላይታዎች ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንብ ሴራ /Seeraa/ ጋር አብረው ያወጡት በሥራ ወቅት የመረዳዳትና አብሮ ተባብሮ የመሥራት ባህል አላቸው፡፡ የወላይታ ብሔር ከአንድ ሰው አቅም በላይ የሆኑ የተለያዩ ዓይነት ሥራዎችን በህብረት የማከናወን ባህል አለው፡፡ እነዚህም በሥራ የመረዳዳት ባህል በወላይታ ብሔር ዘንድ በሶስት ሊከፈል ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ሀሽያ፣ ሁለተኛው ዛይያ የሚባል ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ ዳጉዋ የሚባለው ነው፡፡
ይህ በወላይታ በሥራ የመረዳዳት ባህል ከ2 እስከ 5 የሚደርሱ በአንድ መንደር እና በአንድ አካባቢ የሚኖሩና እርስ በርስ የሚተዋወቁ አርሶ አደሮችም ሆኑ ወጣቶች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምረው ቢያንስ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት/ግማሽ/ ቀን ድረስ የእርሻ ሥራን በጋራ ተጋግዘው የሚሠሩበት በሥራ የመረዳዳት ባህል ነው፡፡ ሀሽያ ተብሎ በሚጠራው በወላይታ በሥራ የመረዳዳት ባህል ውስጥ ጠንከር ያለ መተዳደሪያ ደንብ /Norm/ የለም፡፡ ነገር ግን በሀሽያ የሚረዳዱ አርሶ አደሮች ጧት ከመኝታ እንደተነሱ እርስ በርስ ተጠራርተው የሀሽያ ሥራ ወዳለበት አርሶ አደር ማሣ በመሄድ ከቀኑ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ሥራ በመሥራት ይለያያሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች እስከ ግማሽ ቀን ከሰሩ በኋላ ወደ ገበያ፣ ወደ ለቅሶ አለበለዚያም ወደ ራሳቸው ግል ሥራ ሊሰማሩ ይችላሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜ በሀሽያ በመረዳዳት ሥራ የሚሰሩ ግለሰቦች እስከ 3 ሰዓት፣ ወይንም 4 ሰዓት አንዳንዴ ደግሞ እስከ ግማሽ ቀን ድረስ ሊተጋገዙ ይችላሉ፡፡ ሀሽያ በሥራ የመረዳዳት ባህል እንደግለሰቦች በጎ ፈቃድና ውሳኔ መሠረት የሚከናወን ነው፡፡ በሀሽያ በሥራ የመረዳዳት ባህል በአንድነት እየሠሩ ካሉ ግለሰቦች መካከል አንዱ በተረኛው ሥራ ላይ ካልተገኘ ቅጣት አይጣልበትም፡፡ ምክንያቱም በቀረው ግለሰሰብ ላይ የሚጣል ቅጣት ባይኖርም ያልተሳተፈውን ተራው ሲደርስበት ግለሰቡ ሳይመጣ ይቀራል፡፡ በሀሽያ የመረዳዳት ስርዓት ሁሉም አባላት ተነጋግረው በተስማሙበት መሠረት ይሠራሉ ማለት ነው፡፡ ሀሽያ በሥራ የመረዳዳት ባህል ውስጥ አባላቱ እስከ ምሣ ሰዓት በሥራ ላይ የማይቆዩ ከሆነ ምሳ አይዘጋጅላቸውም፡፡ ይሁን እንጂ በቁርስ ይቀርብላቸዋል፡፡ ምሳቸውን ግን ወደየቤታቸው ሄደው ይበሉና በዛው ወደግል ሥራቸው ይሄዳሉ፡፡ ቀን ሙሉ በሥራ ላይ የሚውሉ ከሆነ ቁርስም ሆነ ምሣ ይዘጋጅላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ሀሽያ ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ሰዎች ቁጥር የሚሠሩት በሙሉ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሥራ ባህል ነው፡፡
ዛይያ የሚባለው ከ5 እስከ 10 የሚደርሱ ሰዎች አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በመሆን በሥራ የሚረዳዳበት ስርዓት ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ተራ በተራ የግላቸውን ሥራ በጋራ ሰርተው የሚበለጽጉበት ህብረት ነው፡፡ ዛይያ በወላይታ ብሔር ዘንድ የተለመደና እስካሁንም ያለ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት ሲሆን ከአንድ ሰው አቅም በላይ የሆነውንና ስፋት ያለውን ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በሥራ የሚረዳዱ ሰዎች ተሰባስበው ተረኛው አርሶ አደር ያቀደውን ሥራ ሰርተው የሚነሱበት ስርዓት ነው፡፡ የዛይያ ስርዓት እንደሀሽያ ስርዓት በአንድ መንደር የሚኖሩ እና በአንድ ሀሳብ ሊስማሙ የሚችሉ ግለሰቦች ተስማምተውና ተግባብተው ከዕለተ ሰንበት ውጪ ባሉት ቀናት ከጧቱ 12 ሰዓት አከባቢ በመነሳት ሥራው ወዳለበት አርሶ አደር ማሣ ሄደው በሥራ ተጋግዘው የሚለያዩበት ነው፡፡
ለዛይያ የሚመጡ መንደርተኞች ለሥራ ሲመጡ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ይዘው ነው የሚመጡት፡፡ የዛይያ አባላት ለሥራ ሲመጡ ተረኛ የሆነው አርሶ አደር ቁርስና ምሣ በራሱ ቤት አዘጋጅቶ የሚጠብቅ ሲሆን ምንም ዓይነት ለየት ያለ መጠጥ አይዘጋጅም፡፡ ተረኛው አርሶ አደር ቁርስም ሆነ ምሣ ቤት ያፈራውን በማዘጋጀት ለሚሰሩ ሰዎች ያቀርባል እንጂ ለየት ያለ ዝግጅት አይኖርም፡፡ ቁርስንም ሆነ ምሳ የሚያዘጋጁት የቤቱ ሰዎች ናቸው እንጂ ከጎራቤት ለእገዛ የሚመጣ ሰው አይኖርም፡፡ ምናልባት ምግብ የሚታዘጋጀው የአርሶ አደሩ ባለቤት ለመውለድ የተቃረበችና አራስ ከሆነች ከጎራቤት አንድ ወይም ሁለት ሴቶች ሊያግዟት ይችላል፡፡ ዛይያ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት ላይ ከእርሻ ሥራ ውጪ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ትልቅ የሆነውን የወላይታ ጎጆ ቤት ለመሥራት የሚፈልግ ግለሰብ በዛይያ የቤቱን መሠረት በመደልደል ማዘጋጀት ይችላል፡፡ ሌሎች የእርከን ሥራዎችም ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ በእርሻ ጊዜ ዘር በዛይያ አማካይነት ሊዘራ ይችላል፡፡ የኩትኳቶና የአረም ሥራዎችም በዛይያ ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡
ዛይያ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት አባላት በአንድ ቀን በሁለት ሰዎች ማሳ ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም በአዝመራው ወቅት የዘር ጊዜ እንዳያልፍ ለማድረግ ከጧት እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ድረስ በአንድ ሰው ማሣ ዘር ዘርተው ከቆዩ በኋላ ከሰዓት ደግሞ በሁለተኛው አርሶ አደር ማሳ ዘር እየዘሩ ይውላሉ፡፡ በወላይታ ብሔር አባባል ‹‹ Badhdheesay sheeshshawu uttidaashin aadhdhees›› ይባላል፡፡ ይህም ከአዝመራ ወቅት ለሽንት እንኳን መውጣት አያስፈልግም እንደማለት ነው፡፡ የአዝመራ ወቅት እንዳያልፍ ለማድረግ በዛይያ የተደራጁ አርሶ አደሮች በአንድ ቀን በሁለት ሰዎች ማሣ ዘር ዘርተው ሊውሉ ይችላሉ፡፡
ዳጉዋ/ደቦ በአንድ መንደር የሚኖሩና ተቀራራቢ የሆኑ በቁጥር 10 እና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች በህብረት የሚሰሩት ሥራ ነው፡፡ ዳጉዋ/ደቦ/ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል የሚሳተፍበት ሲሆን የደቦው አባላት ሥራውን እየሰሩ አንድ ቀን ሙሉ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ዳጉዋ (ደቦ) ተብሎ የሚጠራው በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት ከ10 በላይ ሆኑ ሰዎች በቡድን በቡድን በመሆን በጥቂት ሰዎች ሊሸፈኑ የማይችሉ ሥራዎችን በህብረት ለማከናወን የሚጠቀሙበት ባህላዊ በሥራ የመረዳዳት ስርዓት ነው፡፡ በተለይም የእርሻ ሥራ፣ የአዝመራ፣ የኩትኳቶ፣ የእህል አጨዳ፣ የመወቃትና ሌሎችም በህብረት የሚከናወኑ ተግባራት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዳጉዋ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት ከሌሎቹ ማለትም ከሀሽያ እና ከዛይያ ይለያል፡፡ የዳጉዋ ስርዓት በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት ሆኖ ብዙ ዝግጅት ተደርጎ የሚከናወን ነው፡፡
የአካባቢው ሴቶችም ዳጉዋ ወዳለበት ቤት ተሰባስበው ምግብና መጠጥ በማዘጋጀት የሚያግዙ ከመሆኑም በተጨማሪ የሰፈር ሴቶች ከየቤታቸው ምግብና መጠጥ በማምጣት ድጋፍ ሚያደርጉበት ስርዓት ነው፡፡ ይህ በአንድ አካባቢ/ሰፈር የሚገኙ ሴቶች ዳጉዋ ወዳለበት ቤት የምግብና የመጠጥ ድጋፍ የሚያደርጉበት ስርዓት በብሔሩ አጠራር ያጋኑዋ/Yaganuwa/ ይባላል፡፡ ‘ያጋኑዋ’ ያመጣች ሴት ምን ዓይነት ምግብና መጠጥ እንዳመጣች ዳጉዋ ለጠራች ሴት ካሳየች በኋላ ታስረክባለች፡፡ ዳጉዋ የተጠራበት ቤት እናት ያጋኑዋ ተረክባ ‹‹በደስታና በሰርግ ውለታ መላሽ ያርገኝ›› በማለት የመጣላትን ምግብና መጠጥ በደስታና በፈገግታ ትረከባለች፡፡
ዳጉዋ በሚካሄድበት አካባቢ የሚገኙ ሴቶች የሚያመጡት ምግብና መጠጥ በአዘቦት ቀን ህብረተሰቡ የሚመገባቸው ናቸው እንጂ ለሰርግና ለበዓል የሚዘጋጁ ምግቦች አይደሉም፡፡ ምግቦችም ሆኑ መጠጦች በአከባቢው የሚዘወትሩና ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ናቸው፡፡ በዳጉዋ ባህል መሠረት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ሰፋፊ ማሳዎችን ማረስ፣ መኖሪያ ቤት ለመሥራት መሰረት መደልደል፣ ዘር መዝራት፣ አረም ማረም እና የመሳሰሉት ተግባራት ናቸው፡፡ በዳጉዋ ስርዓት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በየቡድናቸው በመሆን በአንድ ቀን ውስጥ እጀግ በጣም ሰፊ የሆነውን ሥራ በመሥራት ለባለዳጉዋ ግለሰብ የሚያስረክቡበት ነው፡፡ በዳጉዋ ስርዓት በየቡድኑ ያሉ ሰዎች እየዘፈኑና እየዘመሩ አንዳንድ ጊዜም አንዳቸው አንዳቸውን እየቀለዱና እየተሳለቁ ሥራውን በአጭር ሰዓት ውስጥ ለማጠቃለል ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ለዳጉዋ ስርዓት የሚወጣው ወጪ እንደሀሽያ እና ዛይያ ቀላል ሳይሆን እንደተሰበሰበው ህዝብ ብዛት በጣም ከፍ ልል ይችላል፡፡ ምክንያቱም በአንድ አካባቢ ካሉ የሰፈር ሰዎች በተጨማሪ ከሌሎች አካባቢዎችም የሚመጡ እንግዳ ሰዎች ስላሉ የሚቀርቡ ምግቦችና መጠጦች የአዘቦት ጊዜ ምግቦች ቢሆኑም እንኳ የተመረጡ ናቸው፡፡ ዳጉዋ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓቱ የሚከናወነው የእርሻ ሥራ ከሆነ በእርሻ መሣሪያ ከሚቆፍሩ ሰዎች በተጨማሪ እንደየሁኔታው ከ10 በላይ በሆኑ ጥማድ በሬዎች ሊያርሱ ይችላሉ፡፡ በዳጉዋ ስርዓት ምግብ የሚበላው በምሳ ሰዓት ብቻ ሲሆን እንደየግለሰቡ ፍላጎት የጠማው ሰው ካለ በመሀልም ከተዘጋጀው መጠጥ ሊቀርብላቸው ይችላል፡፡
በሀሽያ፣ በዛይያ እና በዳጉዋ በሥራ የመረዳዳት ባህላዊ ስርዓት የማረስ፣ የመኮትኮት፣ የመዝራት እና ምርት የማሰባሰብ ሥራዎች ሊከናወኑ የሚችሉ ሲሆን የጎጆ ቤትም ሆነ የቆርቆሮ ቤት ለመሥራት መሠረት የመደልደልና ግድግዳ የመፍለጥ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡ በስርዓቱ ሥራውን መምረጥ የለም፡፡ ማንኛውም ዓይነት ሥራ በጋባዡ ግለሰብ ፍላጎት መሠረት ሳይመረጥ ይከናወናል፡፡ ሥራው ከቀኑ እስከ 11 ሰዓት ድረስ በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል ሲሆን ከ11 ሰዓት በኋላ ከሩቅ አካባቢዎች የመጡ ግለሰቦች የሚሄዱ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች እንደየሥራው ሁኔታ እስከ 12 ሰዓት ድረስ እየሰሩ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡
በአጠቃላይ የወላይታ ብሔር ቤት ለመሥራት፣ መቃብር ለመቆፈር፣ ምሰሶ ለመጎተት፣ ለመኖሪያ ቤት ግድግዳ ለመፍለጥ፣ የመኖሪያ ቤት የሚሠራበት ቦታ /መሠረት/ ለመደልደል እና በአንድና በተወሰኑ ጥቂት ሰዎች ጉልበት ሊከናወኑ የማይችሉ ተግባራትን ማከናወን ሲፈለግ የመረዳዳትና አብሮ ተባብሮ የመሥራት ባህል ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው፡፡ ይህ በሥራ የመረዳዳት ባህል በህዝቡ ውስጥ ረጅም ዘመን የቆየ የህዝቡን የአንድነት፣ የአብሮነትና የመቻቻል ባህል የሚያጎለብት ነው፡፡ ይህ በእርሻና መሰል ተግባራት ላይ የሚከናወነው በሥራ የመረዳዳት ባህል በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza