• Call Us
  • +251465512106

ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት

የወላይታ ብሔር ባህላዊ የጋብቻ ሥርዓት

 

ጋብቻ እንደዘመኑና አንደብሔሩ የተለያየ ትርጉምና አፈጻጸም እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡ ጋብቻ በሁለት ተቃራኒ ፆታዎች መካከል የሚደረግ የህይወት ትስስር እና ቤተሰብን ለመመስረት የሚካሄድ ውህደት ነው፡፡ ጋብቻ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የነበረ ዛሬም ድረስ ያለ ነገር ነው፡፡ የጋብቻ አፈጻጸሙ ግን እንደዘመኑ፣ እንደሕብረተሰቡ ባህል እና የሃይማኖት ሥርዓት ይለያያል፡፡

እንዲህ እንደአሁኑ ጊዜ የጋብቻ አፈጻጸም ወደ ዘመናዊነት ከማድላቱ በፊት በነባሩ የወላይታ ባህል መሠረት የሚከናወኑ የጋብቻ ዓይነቶችን እንደሚከተለው አሳጥረን እናቀርባለን፡፡

የጋብቻ ዓይነቶች ወደ አምስት ያህል ሲሆኑ እነርሱም­፡-

  1. በቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ "ፓራ ቡላቻ"
  2. በተጋቢዎች ፈቃድ ብቻ የሚፈጸም ጋብቻ
  3. የጠለፋ ጋብቻ "ዳፋ" dafaa
  4. በአገናኝ ድለላ የሚፈጸም ጋብቻ "ላባ" labaa
  5. የውርስ ጋብቻ "ላታኔ ሚሼቾ"
  1. በቤተሰብ ስምምነት የሚፈጸም ጋብቻ

ይህ ዓይነቱ ጋብቻ በወላይታ ሕብረተሰብ ዘንድ ህጋዊ እና ዘላቂነት አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ የጋብቻው ስምምነት በሁለቱ ተጋቢዎች ቤተሰብ በኩል ይፈጸማል፡፡

የወንዱ ልጅ ወላጆች ልጃቸው ለአቅመ አዳም መድረሱን ካረጋገጡ በኋላ ሚስት የምትሆንለትን ልጃገረድ ማፈላለግ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ሂደት የጎሳዎች የዘር ሐረግ ቆጠራ በጥንቃቄ ትኩረት ይደረግበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የልጅቱ ሙያ፣ ውበትና ጠባይ እንደመስፈርት የሚወሰድ ሲሆን የቤተሰቦቿ የኑሮ ደረጃም ከግንዛቤ ውስጥ ይገባል፡፡

መመዘኛዎቹን የምታሟላ ልጃገረድ ከተገኘች የልጁ አባት ከራሱ ጋር ወደ አራት የሚሆኑ ሰዎችን ይዞ ለሽምግልና ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ይሄዳሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ ሲሄዱ ከመንገድ እርጥብ ቅጠል ቀንጥሰው ይይዛሉ፡፡ ወደ ቤተሰቦቿ በራፍ እንደደረሱ በያዙት ቅጠል የእግራቸውን አቧራ መታ መታ በማድረግና ጎሮሮአቸውን እንደመሳል እያደረጉ ይቀመጣሉ፡፡ ቤተሰቡን ጠርተው ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ መታየታቸውን አረጋግጠው ይመለሳሉ፡፡ በአሥራ አምስተኛው ቀንም በተመሳሳይ መልክ መጥተው ይቀመጣል፡፡ ቤተሰቡ ወግ አጥባቂ ካልሆኑ ወደቤት አስገብተው የመጡበትን ይጠይቋቸዋል፡፡ ወግ አጥባቂዎች ከሆኑ ግን የልጅቱ አባት ሆን ብሎ ከቤት ይጠፋል፤ አልያም ቤት ውስጥ እያለ ዝም ይላቸዋል፡፡ ሽማግሌዎቹ ተስፋ ባለመቁረጥ አራት አምስት ጊዜ ይመላለሳሉ፡፡ የልጅቱ አባት የጠያቂውን ቤተሰብ ማንነት ካጣራ በኋላ የማይፈልጉት ዓይነት ከሆነ እስከመጨረሻው ወደቤት አይጋብዛቸውም፡፡ 3 የእምቢታ ምልክት መሆኑ ስለሚታወቅ ሽምግልናው ይቆማል፡፡

ቤተሰቡ ጋብቻውን የሚፈቅዱ ከሆነ ሽማግሌዎቹ ወደቤት እንዲገቡ ያደርጉና የመጡበትን ይጠይቋቸዋል፡፡ እነሱም “ወይፈናችንን በጊደራችሁ ልንለውጥ መጣን፡፡'' ይላሉ፡፡ የልጅቱ አባት “ለልዋጭ የደረሰች ጊደር የለንም፡፡'' ብለው ይመልሷቸውና ስለሁኔታው ከቤተዘመድ ጋር ሲመካከር ይቆያል፡፡ ሽማግሌዎቹ በአሥራ አምስተኛው ቀን ሲመጡ ቡና ይቀርብላቸዋል፡፡ ከቡና መልስ በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ ለቃል ማሠሪያ ቀን ቀጠሮ ሰጥተው በዕለቱ ሊያመጡ የሚገባቸውን አዘው ይሸኟቸዋል፡፡

በቀጠሮው ዕለት የልጅቱ ቤተሰብ ማለፊያ የሆነ ባህላዊ ምግብና መጠጥ አዘጋጅተው ከቅርብ ቤተዘመድ ጎረቤት ጋር በመሆን ይጠብቋቸዋል፡፡ የልጁ ቤተዘመድ ከሽማግሌዎቹ ጋር ተጨምረው ይመጡና የርስበርስ ትውውቅና ግብዣ ይደረጋል፡፡ በግብዣው ወቅት የልጁ አባትና የልጅቱ አባት ጎን ለጎን ተጠጋግተው በመቀመጥ ከአንድ ቅል ውስጥ ያለውን መጠጥ በአንድ ትንፋሽ በመጠጣት ዝምድናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ የአጠጣጥ ሥርዓት “ዳጉዋ'' (dagguwa) ይባላል፡፡ በመቀጠል ከሽማግሌዎች አንጋፋው ተነስቶ የማጫ ምልክት እንዲሆን በልጅቱ እጅ የብር አምባር (sagaayuwaa) ያስርላታል፡፡ ይህ ሥነ ሥርዓት የዝምድና ልውውጥ (qommo lame) ይባላል፡፡ በስነ ሥርዓቱ ማሳረጊያ ላይ ከልጅቱ ቤተሰብ ጋር የሠርጉን ቀጠሮ፣ ለቤተሰብና ለልጅቱ የሚያስፈልገውን የጥሎሽ ዓይነትና መጠን ተነጋግረው ይሰነባበታሉ፡፡

የሠርግ ቅድመ ዝግጅት

ቅድመ ዝግጅቱ በሁለቱም ቤተሰቦች በኩል ነው፡፡ ሁለቱም ቤተሰብ ለሠርጉ ዕለት የሚሆን ግብዣና የስጦታ ዕቃዎች እያሰናዱ ይቆያሉ፡፡

በሠርግ ዝግጅቱ ወቅት ቤተዘመድ ጎረቤት ሁሉ ይተባበራል፡፡ ደጋሹ ቤተሰብ አስፈላጊውን ሁሉ ለማሟላት የበኩሉን ጥረት ያደርጋል፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ ከቤተዘመድ፣ ከቅርብ ጎረቤት እና የውለታ እጅ ባለባቸው ወዳጆቻቸው የሚፈልጉትን ነገር ለሠርጉ ዕለት (cachchaa) ማዘዝ በባህሉ የተለመደ ነው፡፡ እናት ለሴት ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ ቡሉኮ፣ ጋቢ፣ ነጠላ፣ እስር ቅቤ፣ አይብ… ይዘው ለሠርጉ እንዲተባበሩዋት ትነግራለች፡፡

የልጁ ቤተሰብ ከሠርጉ ዝግጅት ውጭ ለሙሽሪትና ቤተሰቧ የሚሰጥ ጥሎሽ (koytaa) የሚከተሉትን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህም

  • ቅልብ በሬ ለአባቷ
  • ጦር “ayyoo tooraa'' ለአባቷ ወይም ለታላቅ ወንድሟ፣
  • እንስራ ሙሉ ቅቤ “naqqo oysaa''፣
  • የአማት እቅፍ ሙሉ ቅቤ “bollottee idimaa oysaa'' ለእናቷ የሚሰጥ ሆኖ በግምት ከአንድ ክንድ ርዝመት በሚበልጥ መጠን በኮባ ቅጠል ሞላ ተደርጎ የሚታሰር ቅቤ፣
  • ለቤተዘመድ የሚታሰብ ቅቤ “wotti-gatuwa oysaa'' መጠኑ መለስተኛ የሆነ ለጋ ቅቤ ሆኖ በሠርጉ ላይ የተሰበሰቡት የልጅቷ ቤተዘመድ ሴቶች የሚቀቡት
  • ለሙሽሪት ቡሉኮ፣ ጋቢ፣ ነጠላ፣ የጆሮና የአንገት ጌጥ፣

ከሠርጉ ዕለት ሁለት ወይም ሦስት ቀን ቀደም ብሎ የአከባቢው ነዋሪ ተሰብስቦ በደጋሹ በራፍ ዳስ ይጣላል፡፡ በመብሉና በመጠጡ ዝግጅት ሴቶች ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ ወንዶች እንጨት በመፍለጥ፣ ዳስ በመጣልና በተለያዩ ስራዎች ይሠማራሉ፡፡ ወደ ዋዜማው ቀናት ሩቅ ያሉ ቤተዘመድ አስፈላጊውን መሰናዶ ሁሉ አጠናቀው ድግሱ ቤት ይገባሉ፡፡ ቅርብ ያሉ ጎረቤት ውለው እያደሩ መሰናዶ ሁሉ አጠናቀው ድግስ ቤት ይገባሉ፡፡ ቅርብ ያሉ ጎረቤት ውለው እያደሩ ዝግጅቱን ያጧጡፋሉ፡፡

የሠርጉ ዕለት

በሠርጉ ዕለት የሙሽራው አጃቢዎች በቀጠሮው ሰዓት ይሰበሰቡና በአባቱ ቤት በሚገባ ይጋበዛሉ፡፡ ከዚያም ሙሽሪትን ለማምጣት በየፈረሶቻቸው ላይ ሆነው እየዘፈኑ ሆታ እያቀለጡ ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ሙሽራው “ሀዲያ'' (hadiya) የተባለውን ጌጠኛ የባህል ሱሪ ታጥቆ ከወገቡ በላይ “አሳራ'' የሚባለውን ጥብቆ አላባሽ በመልበስ ነጭ መለስተኛ ጋቢ ደርቦ በእጁ ጦር ይይዛል፡፡ በጉዞ ላይ “ሃያሾ ላሌ'' ተብሎ የሚታወቀውን ተወዳጅ የሠርግ ዘፈን ይዘፍናሉ፡፡

            “Tukkiyaa giddoora po’iya aginiyoo

            Hayya sholaalee ekkana boos

            Xeessa baggaara asho biillamiyoo

            Hayya sholaalee ekkana boos

            Gediyaa xeelliyoode muyla hallittyoo”

የዘፈኑ ይዘት “እንደጨረቃ የደመቀችዋን ውብ፣ ወገበ ቀጭኗን፣ ተረከዘ ልስልሷን… ልጃገረድ ልናመጣት እየሄድን ነው፡፡'' የሚል ሀሳብ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ lashshimo agokko, hay lachchiyawu, la yuya yuya aboliya yuya, boolade boolade yuya… የመሳሰሉ ልዩ ልዩ የሠርግ ዘፈኖች አሉ፡፡

ሽማግሌዎች ከሙሽራና አጃቢዎች ቀድመው ለልጅቱ ቤተሰቦች ጥሎሽ (koytaa) ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ያመጡትን ጥሎሽ ማስረከብ ይችሉ ዘንድ በአክብሮት ጠይቀው ይፈቀድላቸውና የልጅቱ ቤተሰብና የቅርብ ቤተዘመድ በመደዳ በተቀመጡበት ጥሎሹን እየቆጠሩ ያስረክባሉ፡፡ በአጋጣሚ የጎደለ ነገር ካለ ቤተሰቡ ይቆጣል፡፡ ካመረሩ ሌላ ጊዜ ለማሟላት ዋስ ጠርተው ምህረት ጠይቀው ይታረቃሉ፡፡ የርክክቡ ሥነ ሥርዓት ሲያበቃ ለነሱ ተብሎ የተሰራ ልዩ ባህላዊ ምግብ ቀርቦላቸው ይስተናገዱና ከሠርጉ ታዳሚዎች ጋር ይቀላቀላሉ፡፡

በሌላ በኩል ሙሽራው ከአጃቢዎቹ ጋር እየደረሰ መሆኑን ለመግለጽ አራት ፈረሰኞች ይመረጡና በግልቢያ ልጅቱ ቤት በራፍ አከባቢ ደርሰው ምልክት በመስጠት ይመለሳሉ፡፡

ከሙሽራዋ ቤት ለሠርገኞች አቀባበል ቀደም ሲል የተነገራቸው ሁለት ፈረሰኞች ይወጡና በመንገድ ላይ ግርግርና እንቅፋት እንዳይፈጠር ግራና ቀኙን በማስከፈት ነጻ ያደርጋሉ፡፡ የወንድ ወገኖች ሙሽራውን መሃል ላይ በተሸላለመ ልዩ ፈረስ ላይ አስቀምጠው በሽምጥ ግልቢያ ይገቡና እየተመላለሱ የፈረስ ጉግስ ያሳያሉ፡፡ በሙሽራው በኩል ሂደቱን ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችና ዘፋኞች በጭፈራና በዘፈን ሲያደምቁ የሴቷ ወገን በበኩሉ ደግሞ በቤቱ ግቢ (shuuriyaa) በባህላዊ ጭፈራና ዘፈን አከባቢውን ያደምቃል፤ ሆታ እልልታው ይቀልጣል፡፡

በጨዋታው ከቆዩ በኋላ እንዲገቡ ይፈቀድቸዋል፡፡ በእንግዳ ተቀባዮች መሪነት አስተናጋጆች የሥራ ክፍፍል ተደርጎላቸው የግብዣው ሥነ ሥርዓት ይጀምራል፡፡ “ቶሎሱዋ አሾ'' (Tolsso ashuwaa) የሚባለው ምርጥ የቁርጥ ሥጋ፣ “ሙቹዋ'' (muchchuwaa)፣ ከአይብ፣ ከሥጋና ከበቅቤ የሚሰራ “ሎጎሙዋ''(loggomuwaa)፣ ምርጥ የቆጮ ቂጣ (goodeettaa unccaa)፣ የበቆሎ ቂጣ፣ በቅቤ እና በልዩ ልዩ ቅመማ ቅመም የተዘጋጀ “ዳታ በርበሬ'' ወዘተ በገፍ ይቀርብላቸዋል፡፡

በነባሩ ባህል ለሠርግ ዕለት የሚዘጋጁ የመጠጥ ዓይነቶች የጌሾ ጠላ/parssuwa፣ የማር ብርዝና ጠጅ ናቸው፡፡ ከጊዜ በኋላ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ከተስፋፋ በኋላ “ኪኖቶ'' የተሰኙ ለስላሳ መጠጦች እየተዘወተሩ መጥተዋል፡፤

በመጨረሻም ሴት ሙሽራ ካለችበት ክፍል እንደተሸፋፈነች በጓደኞቿ ታጅባ በአንድ ሽማግሌ መሪነት ወደ ዳሱ ስትገባ ሙሽራውና አጃቢዎችም ተነስተው ይቆማሉ፡፡ የሙሽራው አባት ልጅቱን ይይዝና ሙሽራውን “አምኜህ ጮርቃዋን ልጄን ሰጥቼሃለሁ፡፡ እንደ እኔው ያዛት ተንከባከባት'' ይሉታል፡፡ ሙሽራው “ምንም ነገር ሳይጎድልባት እንደርስዎ ልንከባከባትና ላከብራት ቃል እገባለሁ፡፡'' በማለት ጎንበስ ይልና መቀበሉን ያረጋግጣል፡፡ በመቀጠልም ሙሽራው ከሙሽሪት ጋር የቤተዘመዶቿን እግር ስመው ሲጨርሱ ቀድሞ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀው አዛይ ሚዜ “ba’o jaalaa” ሙሽሪትን አዝሎ ወደ ውጭ ይወጣል፡፡ አዛዩ ሚዜ በመጀመሪያ ሙሽሪትን ባዝራ ፈረስ ላይ ካስቀመጣት በኋላ ያወርዳትና በበቅሎ ላይ እንድትቀመጥ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ በቅሎ ላይ ከወጣች እንደ በቅሎ መሃን ትሆናለች ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡

ሠርገኞቹ ወደ ልጁ ቤት እየተጓዙ “ይሄው ይዘናት መጣን”/ekkidi yoos!/ የሚባለውን የሠርግ ዘፈን እያቀለጡ ነው፡፡ በመንገድ ላይ ያለው የጭፈራ ትርዒትና የዘፈን ሆታ እልልታ ልብን ይመስጣል፡፡ ቤት እንደደረሱ የልጁ እናት፣ አክስቶች፣ የአጎት ሚስቶች

(Baltteetaa) መሬት ላይ በተነጠፈ ቁርበት ላይ በተርታ መደዳውን እግራቸውን ዘርግተው ይቀመጣሉ፡፡ አዛዩ ሚዜ ሙሽሪትን ከበቅሎ ተሸክሟት እንደወረደ በባልቴቶቹ እቅፍ ላይ ያስቀምጣታል፡፡ እነሱም ተራ በተራ እንትፍ እያሉ “ውለጂ ክበጂ! ሀብታም ሁኚ!” (yela, deexxa, dureta) በማለት ይመርቋታል፡፡ ከሙሽራው አባት ይጀምርና ሁሉም ቤተዘመድ የጎጆ መውጫ ስጦታና ሽልማት ያበረክትላቸዋል፡፡ ስጦታው እንደየሰው ቢለያይም መሬት፣ ከብት፣ አልባሣት ወዘተ ያጠቃልላል፡፡

ከዚያም ሙሽሪት በሚዜዎች አማካይነት ወደ ጫጉላ ቤትዋ ትገባለች፡፡ ለዕለቱ መኝታ በባህሉ መሰረት ሙሽሪትን የምታዘገጃጃት የሙሽራው ወንድም ሚስት፣ ወይም የአጎቱ ሚስት (menaatte) ስትሆን አገልግሎቷ በነባሩ ባህል እስከ 3 ጠገራ ብር ይበረከትላታል፡፡ menaatte የማዘገጃጀቱን ስራ ጨርሳ ስትወጣ ሙሽራው ይገባል፡፡ መቼም ወግ አይቀርምና ሙሽሪት በቀላሉ እጅ አትሰጥም፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ እንደተደፈረች ትጮሃለች፡፡ ሙሽራውም ምሽራቿ (mishshiraachchaa) ብሎ ደስታውን ሲያበስር ከውጭ ሆነው የሚጠባበቁ ጓደኞቹና ዘመዶቹ በደስታ እልልታ ያቀልጣሉ፡፡ ሙሽራውም ኮራ ባለ መንፈስ ወደ ውጭ ሲወጣ “እንኳን ደስ ያለህ!” እያሉ ይመርቁታል፡፡ የልጁ እናት በደስታ እየተፍነከነከች ለጫጉላ ቤት ሙሽሮች ብቻ ተለይቶ የሚሠራ “erettaa” የተባለ ምግብ ይዘጋጅና ተራ በተራ በማንኪያ (mooqiya) ታጎርሣቸዋለች፡፡

በሦስተኛው ቀን ማለዳ ሙሽሮች ከ3-5 ከሚደርሱ ወንድ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ወደ ልጂቱ ቤተሰብ ቤት ይሄዳሉ፡፡ እዚያም ቀኑን ሙሉ በቤተሰቦቿና ዘመዶቿ ጋር ሲበሉ ሲጠጡ ውለው የሚመለሱ ሲሆን ሥርዓቱ ትውውቅ (ogee erissuwa) ይባላል፡፡

በዚህ ዕለት ከልጂቱ ወገን ለጎጆ መውጫ የሚሆን ስጦታ ይሰጣል፡፡  እንደቤተዘመዷ አቅም ከብት፣ ላም፣ አልባሣት… የማጀት ቁሳቁስ ድረስ ያጠቃልላል፡፡ በጥንት ጊዜ ከቤት አገልጋይ ሴት ሳይቀር ይሰጣት ነበር፡፡ ይህ ሥርዓት ሲፈጸም ሙሽራ ከቤተሰቧ ጋር መቀላቀሉ ይፋ ይሆናል፡፡ ሆኖም እስከ ዕድሜ ልኩ ወላጆቿን በአንቱታ ብቻ እያከበረ ስማቸውን በግላጭ ሳይጠራ ይኖራል፡፡

የልጁ አባት የልጁን ሚስት በበኩሉ መልስ ይጠራል (ayfiya gattees)፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መርቋት ካልፈቀደ በቀር አማቾቿን እንድታይ ባህሉ አይፈቀድም፡፡ በአጋጣሚ ቢገናኙ እንኳን ፈጥና በመሸሽ መደበቅ ይኖርባታል፡፡ ከዚህ ጣጣ ለመገላገል አባትዬው በመኖሪያ ቤቱ ምግብና መጠጥ አዘጋጅቶ ሙሽራውንና ሙሽሪቷን ከሚደርሱ ጓደኞቻቸው ጋር ጠርቶ የሚጋብዛቸው የቅርብ ቤተዘመድና ጎረቤት በግብዣው ቦታ ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ የልጁ አባት በወጉ መሰረት ትኩስ ወተት በሙሽሮቹ እግር በማርከፍከፍ ላይ “ውለዱ፣ ክበዱ፣ ክበሩ” ብሎ ይመርቃቸዋል፡፡ ሙሽሮቹ ከተስተናገዱ በኋላ ይሸኛሉ፡፡ በነጋታው ሙሽሮች ለብቻቸው ይጠሩና ከልጁ አባት ፊት ለፊት ተቀምጠው የልጅቷ አማች  “ከአሁን ወዲያ እኔ አባትሽ አንቺም ልጄ ሆነሻልና አትፍሪኝ ቅረቢኝ አትሽሽኝ ወጉን ምሬሻለሁ፡፡” ይሉዋታል፤ የሚቀርብላቸውን ድግስ ተጋብዘው ይሄዱና ከዚያን ዕለት ጀምሮ ከቤተሰቡ ጋር በይፋ ትቀላቀላለች፡፡ እንደባልዋ ሁሉ እሷም ዕድሜ ልኳን አማቾቿን በአንቱታ ብቻ እንጂ ስማቸውን በነጠላ ፈጽሞ አትጠራም፡፡

2. በተጋቢዎች ፈቃድ ብቻ የሚፈጸም ጋብቻ

እንዲህ ዓይነቱ ጋብቻ ሁለቱ ተጋቢዎች በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተው ይተዋወቁና ተፈቃቅረው ለመጋባት በመወሰን የሚፈጽሙት ነው፡፡

መቼም በሰው ዘንድ አጋጣሚ አይጠፋም፡፡ አንዳንዱ ለበጎ ሲውል አንዳንዱ ለክፉ ይደርጋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ጊዜ ግን ሁለት የማይተዋወቁ ሰዎችን ያግባባና እስከ ኑሮ ጥምረት ያደርሳቸዋል፡፡ በተገናኙበት አጋጣሚ ከተስማሙ በኋላ ቃል ይገባባሉ፡፡ በሂደትም ወንዱ ልጅ በቅርብ ለሚያውቃት ብልህና አግባቢ ሴት ምስጢሩን ያካፍልና ሄደው እንዲመካከሩ ያመቻቻል፡፡ ልጅቷም ቀድማ የተስማማችበት ስለሆነ ባለማንገራገር ለጥሎሽ የምትፈልገውን ነገር ዓይነትና መጠን ትናገራለች፡፡ የሚገባው ልጅ በሴትዮዋ በኩል የጠየቀችው እንዲደርሳት ያደርጋል፡፡ በድሮ ጊዜ ጥሎሹ በጠገራ ብር ተመን ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን ከጥሬ ገንዘብ በተጨማሪ ወርቅ፣ ሰዓት፣ ሙሉ ልብስ፣ ጫማ ይገዛላታል፡፡

ልጅቷ የጋብቻዋን ቀነ ቀጠሮ በምስጢር ይዛ የራሷን መሰናዶ በጥንቃቄ ማድረግ ትጀምራለች፡፡ ሁኔታው ከተመቻቸ ቡሉኮ ወይም ጋቢ፣ ነጠላና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን በስውር ማሰራት ትችላለች፡፡ ካልተመቻት ግን ከወላጆቿ ቤት እነዚህን ቁሳቁሶች ደብቃ ይዛ ትወጣለች፡፡ በቀጠሮው ዕለት በሣር አጨዳ ወይም በሌላ ሥራ አስታክካ በአግባቢዋ ሴት አማካይት እጮኛዋ ቤት ትገባለች፡፡

በመቀጠል የሙሽሪትንና የሙሽራውን ቤተዘመዶች ትስስር ቀጣይ ሂደት በሽማግሌዎች አማላጅነት (gaannaa) የሚያልቅ ይሆናል፡፡

3. የጠለፋ ጋብቻ (dafaa)

ይህ ጋብቻ ወንዱ ልጅ ለጋብቻ የፈለጋትን ልጃገረድ የልጅቷም ሆነ የቤተሰቦቿ  ስምምነት በሌለበት በግዴታ የሚፈጸም የጋብቻ ዓይነት ነው፡፡

የጠለፋ ጋብቻ መንስኤዎች፡-

  1. ልጅቷ ወዳው ሳለ ቤተሰቦቿ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ከቀሩ፣
  2. ወንድ ልጅ ወዷት በልጅቱ በኩል እምቢታ ካለ፣
  3. የልጅቷ ቤተሰቦች የሠርጉን ጊዜ በጣም ካራዘሙት፣
  4. ልጅቷን ሌላ ሰው ሊያገባት ነው ተብሎ ከተሠጋ እና
  5. የልጅቷ ቤተሰብ ከወንዱ ልጅ አቅም በላይ የሆነ ጥሎሽ ሲጠየቅ

ጠለፋ አብዛኛውን ጊዜ የሚከናወነው በገበያ ቀናት ሲሆን በሌሎች አጋጣሚዎች አመቺ ሁኔታ ከተገኘ አይታለፍም፡፡ ጠለፋው በታቀደ ቀን ልጁና ጓደኞቹ የልጅቱ መምጫና ጊዜ መረጃ በመሰብሰብና በመገመት ጥሻ ውስጥ ያደፍጣሉ፡፡ ልጅቱ ከአጠገባቸው ስትደርስ በልጁ መሪነት በጉልበትና በዱላ በመታገዝ ጓደኞቹ ተሸክመዋት ይሮጣሉ፡፡ ጠላፊውና ተባባሪዎቹ በሰላም ወደልጁ ሠፈር ከደረሱ ወደጫጉላ ቤት ያስገቡዋታል፡፡ ምክንያቱም ሳትደፈር ከቆየች አምልጣ የመሄድ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይታመናልና፡፡

ጠለፋው በተፈጻመ ሦስተኛው ቀን ሽማግሌዎች (gaannaa) ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ይላካል፡፡ ሽማግሌዎች በአባቷ በራፍ ከደረሱ በኋላ ጎንበስ እንደማለት ብለው “ተሳስተናል፣ አጥፍተናል፤ ልጃችሁን የእገሌ ልጅ አግብቷል፡፡” ይላሉ፡፡ ያው የተለመደው አተካራ ባይቀርም ወደ መጨረሻ ላይ እርቅ ይደረግና በሂደት ነገሩ በሰላም ይጠናቀቃል፡፡

 

4. Labaa (ልጅቷን በማግባባት የሚፈጸም) ጋብቻ

ይህ ዓይነቱ ጋብቻ በአብዛኛው የሚፈጸመው በህጋዊ መንገድ በሀገር ሽማግሌ አስጠይቀው፣ የሚጠይቁትን ጥሎሽ አሟልተው ደግሰው ለማግባት አቅም በሚያንሳቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡

ወንዱ ልጅ ልቡ የፈቀዳትን ልጃገረድ ከመረጠ በኋላ በቅርብ በሚያውቃት ሴት ወይም አንዳንዴ ወንድ አማካይነት ያስጠይቃታል፡፡ ለአገናኝነት ተግባር የሚመረጡ ሰዎች ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ተልዕኮ በማስፈጸም የታወቁ፣ በአከባቢው የሚወደዱና የሚከበሩ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ አገናኝዋ ሴት የተጠቆመችዋን ልጅ ከገበያ መሃል ፈንጠር ያለ ቦታ ትወስዳትና የልጁን ቁመና፣ ውበት፣ ሀብት፣ ዘር አጋንና በመንገር ታግባባታለች፡፡

በ “labaa” ወቅት ልጁ የሌላውን ውበት ሀብት ቁመና እንዳለው አድርጎ ማሳመን የተለመደ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ አንዳንዴ ልጁን ለማሳየት እንኳን የሆነ እንከን ወይም መልከ ጥፉ ከሆነ ለጊዜው ሌላ ቆንጆ ወንድ መርጦ በማሳየት ማግባባትም የተለመደ ነው፡፡

በመቀጠል ለእሽታዋ ቀጥላ የሚያስፈልጋትን ዘርዝራ በሴትዮዋ አማካይነት ትገልጽና ልጁ በጥሎሽ መልክ ያሟላላታል፡፡ ጥሎሹን ከተቀበለች በኋላ ራስዋን አዘገጃጅታ ወደልጁ ቤት የምትሄድበትን ቀነ ቀጠሮ ትሰጣለች፡፡ እስከ ዕለቱ ድረስ በልጁ ቤተሰብ ዘንድ መጠነኛ ድግስ ይዘጋጃል፡፡ በቀጠሮው ዕለት ልጅቱ አልባሳቷን አስቀድማ በድብቅ አውጥታ በሥራ አስታክካ ከቤት በመውጣት ወደ አግባቢዋ ሴት ዘንድ ትሄዳለች፡፡ አግባቢዋ ሴት በድብቅ ልጅቱን ወደ ልጁ ቤት ታደርሳለች፡፡

የልጁ ቤተሰቦች ለልጅቷ ቤተሰቦች ሽማግሌዎችን ልከው ዕርቁ ይፈጸማል፡፡ ሙሽራውና ሙሽሪት ከተፈቃቀዱ ትዳሩ ይዘልቃል፡፡

 

5. የውርስ ጋብቻ Laataanne Mishechchuwaa

የውርስ ጋብቻ ከዚህ በፊት የተመሰረተ የጋብቻ ዝምድና እንዳይቋረጥ ሲባል የሚደረግ ጋብቻ ነው፡፡

ላታ (laataa) ታላቅ ወንድም ለሞተ ታናሽ ወንድም የታላቁን ሚስት የሚያገባበት ሥርዓት ነው፡፡ የጋብቻው ዓላማ የሟች ወንድም ልጆች አሳዳጊ እንዳያጡና በባዳ እጅ እንዳይሰቃዩ ከሚል እምነት የተነሳ ነው፡፡

“ሚሸቾ” (mishechchuwa) ማለት “ማስተዛዘን” ማለት ሲሆን ሴት ልጃቸውን ድረውለት ቤተሰብ መስርታ በመኖር ላይ ሳለች በአጋጣሚ ከሞተች የሟችቱን ታናሽ እህት በምትክ ለሚስትነት የሚሰጡበት ሥርዓት ነው፡፡ ዓላማውም የተወለዱት ልጆች በእንጀራ እናት እንዳይጎዱና ከዚህ ቀደም የተጀመረው የጋብቻ ዝምድና እንዳይቋረጥ ታስቦ ነው፡፡

ጋብቻ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በየትኛውም ማህበረሰብ ዘንድ ያለ ማህበራዊ የሕይወት ሲሆን ትርጉሙና አፈጻጸሙ ከዘመን ወደ ዘመን ከሥፍራ ወደ ሥፍራ የተለያየ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ በተለይም የጊዜያትና ዘመናት ሂደት የሚፈጥራቸው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ጋብቻን ጨምሮ በብዙ የሕይወት መስተጋብሮች ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡

እናም የነባሩን የወላይታ ብሔር የጋብቻ ሥርዓት በዛሬው ትውልድ ዘንድ እንደነበረ ማግኘት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ በርካታ ለውጦች ይስተዋላሉና፡፡ ባህል “dynamic” ነው፡፡

ሆኖም የትናንቱን ማንነት እና ትውልድ ያለፈበትን የዕድገት ጎዳና በተለያየ የኑሮ መስተጋብሮች አኳያ ለቀጣዩ ትውልድ በታሪክ ቅርስነት ማስቀመጡ ተገቢ ነው፡፡