የግርዘት ሥርዓት በወላይታ ሕብረተሰብ ዘንድ በጥብቅ ከሚከናወኑ ባህላዊ ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት በብሔሩ ዘንድ በጥልቀት የሚከናወነው በሁለት ዓላማዎች ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው ከባህላዊ ዓላማ ጋር የተሳሰረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሃይማኖታዊ ዓላማ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ከባህል አንፃር ግርዛት በሕብረተሰቡ ዘንድ ለወንድ ልጅ ለአቅመ አዳም ደርሶ ራሱን መምራት ወደሚችልበት የዕድሜ እርከን እንደደረሰ የመግለጫ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህ ካልተፈጸመ የመራቢያ አካሉን ንጽሕና መጠበቅ ያልቻለ ፀያፍ ሰው ተደርጎ ስለሚቆጠር እንደውግዝ ይቆጠራል፡፡ ትዳር ለመመስረት ሲታሰብ በየአጋጣሚው እንኳን shaamaa ተብሎ ይዘለፋል፣ ይናቃል፡፡ ያልተገረዘ ሰውን ለማንኳሰስ የሚውሉ ምሣሌያዊ ንግግሮች፣ ተረቶች፣ የዘፈን ቃላዊ ግጥሞች… ወዘተ ይጠቀማሉ፡፡
ለምሣሌ፡- bawu qaxxarettibeenna uray asa ayfiya oyiqees
ትርጓሜው፡- ለራሱ አልተገረዘ፤ ለሌላው ዓይን አባት ሆነ፡፡
ለራሱ አልበቃ፤ ለሌላው ጠበቃ እንደማለት ነው፡፡
በሴት ልጅ ግርዛትም ላይ ሕብረተሰቡ ተመሣሣይ አመለካከት ነበረው፡፡ “ ወደ ኮረዳነት ዋዜማ ካልተገረዘች የቤት ዕቃ ሰባብራ ተጨርሳለች፤ ብታገባም በባሏ ብቻ የማትረጋ ሴሰኛ አመንዝራ ትሆናለች፡፡” ይባል ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከሳይንሱ እውነታ ጋራ የሚጣረስ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ከመሆን አልፎ እንደ ወንጀልም ስለሚቆጠር ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ሰፊ ጥረትና እንቅስቃሴ እየተደረገ በመሆኑ ብዙ ለውጦች እየታየ ነው፡፡
የዚህ ፅሑፍ ትኩረትም ነባሩን ባህላዊ የግርዘት ሥርዓት ክወና ከወንድ ልጅ አንጻር መቃኘት ነው፡፡ የሥርዓቱ ክዋኔ ትንተናም አሁን ባለንበት ዘመን ላይ ከስልጣኔና ትምህርት ጋር ተያይዞ የመጡ ለውጦች ቢጠቃቀስም ይበልጡኑ በነባሩ ባህል ላይ ተንተርሶ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡
በወላይታ ነባር ባህል መሰረት የግርዘት ሥርዓት የሚዘወተርበት ልዩ ወቅት፣ የዕድሜ ክልል እና የክዋኔው ቅድመ ተከተሎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
የግርዛት ሥርዓት የሚዘወተርበት ወቅት
እንደ ሌሎቹ ባህላዊ ክዋኔዎች ሁሉ የግርዛት ሥርዓት በወላይታ ብሔር ዘንድ የሚዘወተርባቸው ወቅቶች አሉ፡፡ ግርዛት በወላይታ ብሔር በዋናነት በብሔሩ የዘመን መለወጫ (ግፋታ ክበረ በዓል) ሰሞን የሚፈጸመው ሲሆን አልፎ አልፎ እህል ከተሰበሰበ በኋላ በህዳርና በታህሳስ ውስጥም ይከናወናል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የአየሩ ሁኔታ አመቺ ከመሆኑ ጎን ለጎን የእርሻ ስራ ፋታ የሚሰጥበት ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ ለብሔሩ ዘመን መለወጫ የሚደረገውን መሰናዶ ዝግጅት ለግርዛት በዓልም አቀናጅቶ ለመጠቀምም ጭምር ነው፡፡
የግርዛት ሥርዓት የሚፈጸምበት የዕድሜ ክልል
በብሔሩ ነባር ባህል ወንድ ልጅ ለአቅመ አዳም በሚደርስበት ዋዜማ በአማካይ ከ16-21 ዓመት ሲሆነው ይገረዝ ነበር፡፡ ሴቷ ወደ ልጃገረድነት መሻገሪያዋ ዕድሜ ላይ በአማካይ ከ14-18 ዓመት ባለው ይገረዙ እንደነበር አበው ያስረዳሉ፡፡ ይህ የዕድሜ ክልል ለምን እንደተመረጠ ሲገልፁ “ልጆች በህጻንነታቸው ከተገረዙ ቅባት ነክ ምግቦችን በፍላጎት ስለማይበሉ ዕድገታቸው ይስተጓጎላል፣ ይቀጭጫሉ ይላሉ፡፡
አሁን አሁን ከተማዎቹና የተማሩ ሰዎች ልጆቻቸውን በሕፃንነት ዕድሜ ላይ ያስገርዛሉ፡፡ ገጠሬውም ቢሆን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ከሚሄዱበት ዕድሜ ቀደም ብለው በአማካይ ከ5-13 ዓመት የዕድሜ ክልል ባለው ጊዜ ማስገረዝ እየለመዱ ይገኛሉ፡፡
የግርዛት ክዋኔ ቅድመ ተከተል
ሀ. ቅድመ- ግርዘት ክዋኔዎች
ባህላዊው የወላይታ የግርዘት ሥርዓት ዝግጅቱና ወጪው ሰፊ በመሆኑ ረዥም ዕቅድ ይያዝለታል፡፡ ምንም እንኳን የዝግጅቱ መጠን በባለቤቱ አቅም የሚወሰን ቢሆንም ማንም የተቻለውን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አይልም፡፡ ለዝግጅቱ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ጊዜ በመውሰድ አስፈላጊውን ሁሉ ማሰባሰብ የተለመደ ነው፡፡
ቤተሰቡ አቅም ያለው ከሆነ ለእርድ በሬ ይቀለባል፡፡ ከማሣ የእህል ምርት ተሰብስቦ ይወቃና ጎተራ ይገባል፡፡ ቅቤና ማር ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ይጠራቀማል፡፡ ቆጮና ቡልኣ የመሳሰሉ የእንሰት ተዋጽኦዎች በጥንቃቄ ተዘጋጅተው ይቀመጣሉ፡፡ ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ ከቤት የሚወሰደውም ከገበያ የሚሸመተውም መሟላቱ ይረጋገጣል፡፡ የበርበሬና ቅመማ ቅመም ዝግጅት ይጠናቀቃል፡፡ የማገዶ እንጨት ተቆርጦ ይፈለጥና እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ የቤት ውስጥ እድሳትም የአጥር ዙሪያ ጥገናም ተያይዞ ይከናወናል፡፡
ለተገራዡ ልጅ የዓይን አባት የሚሆን jaalaa ምርጫ ከወዲሁ ይከናወናል፡፡ ምርጫው በተገራዡ ልጅ ጥቆማ ሊከናወን ቢችልም አብዛኛው ጊዜ በወላጆች በጎ ፈቃድ ይፈጸማል፡፡ በነባሩ ባህል የጎሣ አቻነት መጠበቅና ግለሰቡ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ማረጋገጥ የማይታለፍ መስፈርቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ ዘመድ አዝማድ፣ ወዳጅና ጎረቤት የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ጥሪ ይተላለፍላቸዋል፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም በደስታም ይሁን በሐዘን የውለታ እጅ ያለባቸው በሙሉ ይጠራሉ፡፡ እስከነአባባሉ qaxxaraan bullachchaan zaariisso (በግርዝ በሠርግ ውለታ መላሽ ያድርገን) እንደ ማለት ነው፡፡
ወደ ግርዝ ሥርዓት ዋዜማ ሰሞን ዝግጅቱ ይጧጧፋል፡፡ ወንዶች ዳስ የሚሠራበትን ቦታ በመኖሪያ ግቢው ውስጥ መርጠው ይደለድላሉ፡፡ የአጥሩ ዙሪያ ይጠገናል፤ አፀዱ ይከረከማል፤ አከባቢው ሁሉ ፅዱ እና ውብ ሆኖ እንዲታይ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል፡፡ የማጀት ውስጥ ሥራም ዝግጅት በየፊናው ይጀመራል፤ እህል ይፈጫል፣ ዱቀት ይቦካል፣ ጥንስስ ይጠነሰሳል፡፡
በግርዙ ዋዜማ ዕለት ፕሮግራሙን ለማድመቅ ከወዲሁ ከበሮ ይደለቃል፡፡ ባህላዊ ዘፈኖች ይዘፈናሉ፤ የተገራዡ ጓደኞች ተሰባስበው ይጨፍራሉ፡፡ ቤተሰቡ ያለውን ሲያቀራርቡ የጎደለውን ሲያሟሉ ይውላል፡፡
በሌላ በኩል የተገራዡ ዓይን አባት “ጃላ” በዋዜማው ዕለት ዝግጅቱ በራሱ ቤት ሲያደርግ ይውላል፡፡ በብሔሩ ባህል ጃላ ከ4-8 የሚደርሱ አጃቢዎችን ከጓደኞቹና ዘመዶቹ መርጦ ቀጠሮ ሰጥቶ ያቆያቸዋል፡፡ ፕሮግራሙን እንዲያደምቁለት የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችን ፕሮግራም ይይዝላቸዋል፡፡ ጃላውና ጓደኞቹ ማምሻ ሰዓት አከባቢ ይመጡና በጃላው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ የሚገናኙ ሲሆን “ሙቹዋ” የተባለ ተወዳጁ የወላይታ ምግብ ከምርጥ ቦርዴ (parssuwa) ጋር ቀርቦላቸው ይጋበዛሉ፡፡ በዚህ መሃል ሙዚቀኞቹ ጃላውንና ቤተሰቡን እያሞጋገሱ ይዘፍናሉ፤ ያቅራራሉ፡፡ በቃላዊ ግጥሞችም የግነት ዘይቤ በመጠቀም የጃላውን ባለቤት ያወድሷታል፡፡
Hooho……. ho…………ha!
Hamma nu wogaa… hamaa nu gishsha
Qol’’oppe tookkada hagan wuyige ola
Bi eran eessiyagaa na’ee
Qaran qanxxiyagaa na’ee
Wogay diyoogaa na’ee
Hamma nu wogaa.. hamma nu gishshaa!
ጠቅለል ባለ መልኩ ትርጓሜው “ጥሩ ቤተሰብ ጥሩ ልጅ ይወልዳል፡፡ እንግዳ አክባሪ ከሆነ ቤተሰብ የተገኘሽ ነሽ፡፡ ከሞላው ከተረፈው ቤት የተገኘሽ በመሆንሽ ዛሬም ሳትሰስቺ አብይን አጠጪን..” እያሉ የመስተንግዷቸው መጠን ይበልጥ ከፍ ይደረግላቸዋል፡፡
ከምሽቱ አራትና አምስት ሰዓት ገደማ ሲሆን ጃላውና አጃቢዎቹ ወደግርዙ ቤት ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ወደ ግርዙ ቤት መቃረባቸውን ለማሰማት ሙዚቀኞቹ የሙዚቃ መሳሪያውን ድምጽ በእጅጉ አጉልተው በመልቀቅ ይዘፍናሉ፡፡
ይህንን የሰሙ የግርዙ ቤት አባላት በታላቅ ደስታና በእልልታ በዘፈን እስከ በራፍ ወጥተው አቀባበል ያደርጉላቸዋል፡፡ የጃላውን እና የተገራዡን እጅ ለእጅ አያይዘው በማቆም ጭፈራና ዘፈኑን ያቀልጡታል፡፡ የጭፈራውና የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ቅንብር ድምጽ እንኳን የባህሉን ሰው ሌላውንም ተመልካች ስሜት የመቀስቀስ ጉልበት አለው፡፡
ሲጫወቱ ከቆዩ በኋላ ከቤቱ ለእንግዳ ተቀባይነት በተመደበ ሰው አማካይነት ወደቤት ይገባሉ፡፡ አቀማመጣቸው እንደየማዕረጋቸው ሲሆን ጃላው ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይቀመጣል፡፡
በመቀጠል ላጃላው፣ ለጓደኞቹና ለግርዛቱ እድምተኞ የተዘጋጀው መስተንግዶ ይቀርባል፡፡ ከመስተንግዶው መልስ በሙዚቀኞች አማካይነት የዘፈኑና ጭፈራው ይቀጥላል፡፡ በተለይም ለዚህ የግርዘት ሥርዓት ያበቃቸውን አምላክ የሚያመሰግኑበት ባህላዊ ዝማሬ አለ፡፡
Kaassa gooppa bullachchay xoossaba
Abeeti bullachchaa xossi bessioy be’ees
Ayeera Aawaara
Abeeti bullachchaa xoossi bessiyoy be’ees
Zariyara dabbuwara
Moottaara heeraara
Hagaadan qaxxaraa
ትርጓሜውም “ይኸ ሁሉ የተከናወነው በእግዚአብሔር እንጂ በኛ ብርታት አይደለም፡፡ ወላጆችን፣ ዘመድ አዝማድ ጎረቤት ሁሉ ጠብቆ ለዛሬው ፕሮግራም ያበቃው እርሱ ነው፡፡” እንደ ማለት ነው፡፡
በባህሉ ጃላ የሚሆን ሰው በዘፈቀደ አይመረጥም፡፡ ብርታቱ፣ ሀብቱ፣ ልግስናው፣ ያለው ተቀባይነት.. ወዘተ ተመዝኖ በመሆኑ በቃላዊ ግጥሞች በዕለቱ ሙዚቀኞቹ ያቀነቅኑለታል፤ ይዘፍኑለታል፡፡
ለአብነት ያህል በጥቂቱ እንመልከት
Jaalaa eesso… jaalaa esso
Ayifiya lyiqiya jaalay
Jaalaa malee haraa malle hagee
Tuma jaalaa… jaalaa eesso jaalaa eesso
Qaxxa gonddooro ... jaalaa eesso
Eeshsho mal’iyaa miizzaa leemiso
Jaalaa eesso... jaalaa eesso
ጥቅል ትርጓሜው የጃላውን ትልቅነት ክብሩን ለዝምድና በማንም ዘንድ ተፈላጊ የሆነ ሰው መሆኑን ይገልጻል፡፡
Laalee bole …. Laale bole
Ogiya doonan ogoddaama na’awu
Miixaa doonaa danggarssaawa na’aawu
Mittan woriyaagaa na’awu
Bazaoy baraatiyoogaa na’awu
Bonccoy ashshamiyogaa na’awu
Osiya laareenan danggarssaa goyinaa qanxxiyaga na’awu
Kawuwa yettiyaga na’awu menttaa menttiyaga na’awu
Baalliyan gayiriyaga na’awu la buuccidi oyittiyoga na’awu
Laa koyyidi koddiyoga na’awu laali bole…. laali bole
የቃላዊ ግጥሞቹ ይዘት ጃላው የስመጥር ጀግና ትውልድ ዘር መሆኑን, በዋለበት ውሎ ሁሉ የታፈረ፣ የተከበረና ተፈላጊ ሰው መሆኑን ማሞጋገሻ ሀሣብ የያዙ ናቸው፡፡
ጃላው ይህንን መሰል ሙገሳና ውዳሴ ሰምቶ ዝም አይልም፡፡ ገንዘብ በጉርሻ መልክ ይሰጣቸዋል፡፡
ለ.የግርዛቱ ሥርዓት ክዋኔ ሂደት
ግርዙ የሚካሄደው ሊነጋጋ አከባቢ ወደ 11፡00 አከባቢ በመሆኑ ሰዓቱ ሲደርስ ጓደኞቹ ከሙዚቀኞቹ ጋር ተገራዡን መሃላቸው አድርገው ለየት ያለ የማደፋፈሪያ ዘፈን እየዘፈኑ ያበረታቱታል፡፡ ለጓደኞቹ አብዛኛዎቹ የግርዙን ሂደት ያለፉ ሲሆኑ ያልተገረዙት ቢቀላቀሉም ቀነ ቀጠሯቸውን የሚጠባበቁ ስለሆነ አብረው ይሣተፋሉ፡፡
Ee… ehee… aahe
Yayoppa laa na’awu yayoppa
Laafabaa laa na’awu laafaba
Laafaba laa na’awu mayizaba
Laafaba laa na’awu maa’eba
አንተዬ! ምንም ፍርሃት አይግባህ፤ ጉዳዩ በጣም ቀላል ነው አያስጨንቅህ ጨክነህ አንዴ ብትወጣው ያባት ያያትህን ወግ ባህል የፈጸምክ ኩሩ ልጅ ትሆናለህ እና በርታ! የሚል ትርጉም አለው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ በዘፈንና በጭፈራ አከባቢውን በማድመቅ ላይ ሳሉ ገራዡ በድንገት መሃላቸው ይገባና ተገራዡን የመንጠቅ ያህል ይዞት ለግርዛቱ ወደተዘጋጀው ጓሮ ይወስደዋል፡፡ ጃላውን ሌሎች በዕድሜ ከፍ ያሉ ሰዎች ከተል ብለው ይመጣሉ፡፡ ገራዡ ወፍራም የእንሰት ግንድ አጋድሞ ተገራዡን አመቻችቶ ያስቀምጠዋል፡፡ ጃላው የተገራዡን ልጅ ዓይኖች በፎጣ ሸፈን አድርጎ ሰውነቱን ጠበቅ አድርጎ አቅፎ ይይዘዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ገራዡ ለግርዛት የተዘጋጀውን “ማግላላ” (magilaalaa) የተባለ እጅግ ስልና አጭር ቀጭን ቢላዋና “ማልእያ” የሚባል ከስንጥቅ የሾለ ቀርከሃ የተሠራ መሣሪያ በአጋዥነት በመያዝ ቀልጥፎ ግርዛቱን ይፈፅማል፡፡ በነባሩ ባህል ተገራዡቹ በዕድሜ ከፍ ያሉ በመሆናቸው ግርዙ እንደተጠናቀቀ (Kormaa) ፉከራ ያሰማል፡፡ የኤገሌ ጃላ ኤገሌ በማለት የአባቱንና ቀጥሎ የጃላውን የእድሜ እኩዮች ስም እየጠራ ይፎክራል፡፡ ገራዡ ትኩስ ወተት ይጎነጭና በተገራዡ ልጅ ላይ ያርከፈክፋል፡፡ ይህ የሚደረገው በቁስሉ ህመም ልጁ እንዳይደክም ታስቦ ነው፡፡ ጃላው ለጋ ቅቤ በርከት አድርጎ በልጁ አናት ላይ ያስቀምጣል፡፡ ይህም የልጁ ልብ እንዳይደክም ይረዳዋል ይባላል፡፡
የተገራዡ ልጅ ደም ጠፈፍ እንዳለ ጃላው ደጋግፎት በሌሎች አጃቢነት ልብስ አሸርጦ ቤት ይገባል፡፡ ሥርዓቱ በሰላም መከናወኑን ያዩ ሴቶችና የልጁ እናት እልልታ ያቀልጣሉ፡፡ ጓደኞቹ ዘፈንና ጭፈራውን ደጃፍ ላይ ያጋግላሉ፡፡ ለተገራዡ ልጅ በተዘጋጀው ቦታ በጀርባው ተንጋልሎ ከፍ ያለ ትራስ ይደረግለትና እግሮቹን አንፈራጦ መኝታ ላይ ይተኛል፡፡ ሁሉም እየቀረቡ “Hashshu hashshu! Woga asi be’idoba be’aasa” እሱም “አሜን አሜን!” በማለት ይቀበላቸዋል፡፡ ጃላው ተገራዡን ግንባሩ ላይ ይስመውና በጉልበቶቹ ላይ የገንዘብ ሽልማት ያኖርበታል፡፡ በድሮ ጊዜ ከ6-10 ጠገራ ብር (ማሪያ ተሬዛ) እንደሚሰጥ አዛውንቶች ያስረዳሉ፡፡
ሐ. ድህረ- ግርዘት ክዋኔዎች
ከግርዙ ሥርዓት ቀጥሎ መስተንግዶ ይጀምራል፡፡ ጃላውና አጃቢ ጓደኞቹ በክብር ይጋበዛሉ፡፡ በብሔሩ ባህል በምርጥ ምግብነት የሚታወቁ “ማልእያ ቁማ” በዓይነት በዓይነት ይቀርብላቸዋል፡፡ እንደፍላጎታቸው ከመረጡት የሥጋ ብልት እንዲበሉ ምርጥ ምርጥ ብልት ከስል ቢላዋ ጋር ይሰጣቸዋል፡፡ ለማባያነት የቆጮና የበቆሎ ቂጣ በቅርፅ ተቆራርጦ በቅቤ ከተዘጋጀ ዳታ በርበሬ ጋር ይቀርብላቸዋል፡፡ ምግቡና መጠጡ ተትረፍርፎ ይጋበዛሉ፡፡ ለማሳረጊያው በቅቤ የተፈላ ቡና ጠጥተው ይሸኛሉ፡፡
የተገረዘው ልጅ በመጀመሪያ የቀዘቀዘ ትኩስ ወተት እንዲጠጣ ይደረጋል፡፡ በመቀጠልም ከገብስ ወይም ማሽላ ዱቄት በቅቤ ብቻ የሚሠራ “ኤሬታ” (ገንፎ) በወላጅ እናቱ አልያም በቅርብ ዘመዶቹ ተሰርቶ ይቀርብለታል፡፡ የዚህ ዓይነት አመጋገብ ለተገረዘ ልጅ፣ ጫጉላ ቤት ላሉ አዲስ ሙሽሮች ወይም ለትኩስ አራስ ሴት በተለይም በጅምር ወቅት ይዘጋጅላቸዋል፡፡ ትኩስ ወተትም በየሰዓታት ልዩነት ይጎነጫል፡፡ ቁስሉ እስኪሽር ድረስ መጋረጃ ተጋርዶለት በተኛበት ከጓደኞቹ ጋር ይጫወታል፡፡ የቡልኣ ገንፎ፣ ከጥሬ ሥጋም ለስለስ ያለው ከጉበት ጋር እየተፈራረቀ ይቀርብለታል፡፡
ለዕለቱ ደስታ የተጠሩት እድምተኞች ቤተሰቡን “hashshu hashshu kuntti be’ite kuntti be’itte!” እያሉ ይመርቃሉ፡፡ ትርጓሜው እንኳን ደስ ያላችሁ! ደስታችሁን ጌታ ፍፁም ያድርገው እንደማለት ነው፡፡ ወደ ድንኳን ወይም ዳስ ይገቡና ሞቅ ያላ ግብዣ ከመብሉም ከመጠጡም ይደረግላቸዋል:: ሲወጡ ዝም ተብሎ አይኬድም፡፡ እንደየቅርበታቸው የገንዘብ ስጦታ (yessa) ያበረክታሉ፡፡ ቤተሰቡም “qaxaran bulachchan zaariso!” እያሉ ይቀበላሉ፡፡ ትርጓሜው፡- በዓለም፣ በሲሳይ እንዲህ ባለ ግርዝ፣ በሠርግ ለመመለስ ያብቃን ነው፡፡ ተገራዡን ልጅ ደግሞ “sakenani paxo, aye awa kushshiya birshsho, midobay uyidobay sifa gido, menttani dangarssan ata!!” ብለው በመመረቅ ይሰናበታሉ፡፡ ቁስሉ እንደውሻ ቁስል በቅጽበት ያሽርልህ፣ በተትረፈረፈ እንድትጋበዝ የወላጆችህን እጅ ይፍታልህ፣ እስክትነሣ ሁሉም ነገር ጤና ይሁንልህ እንደማለት ነው፡፡
በነጋታው የጃላው ሚስት ከ4-6 ከሚሆኑ አጃቢዎች ጋር ልጁን ልትመርቅ ቅቤና ወተት ይዛ አጃቢ ሴቶች ጋር ትመጣለች፡፡ በግርዙ ቤት ለባለቤቷ የተደረገው አክብሮት የተላበሰ መስተንግዶ ለእርሷም ሳይጓደል ይደረግላታል፡፡ ካመጣችው ለጋ ቅቤ ከአጃቢዎቿ የአንዷን አናት ቀብታ የተገራዡን አናት እንድትቀባ ትጋብዛለች፡፡ ከወተቱም እንዲጎነጭ ታስቀርብለታለች፡፡ በባህሉ በዕለቱ የጃላው ሚስትና ተገራዡ ግምባር ለግምባር ፈጽሞ አይገናኙም ምክንያቱም ከተነሣ በኋላ ቤቷ ቅልጥ ያለ ግብዣ አዘጋጅታ ከጓደኞቹ ጋር ጋብዛ የተገራዡ ቁስል ሽሮ የምትፈጽመው ባህላዊ ሥርዓት ስላለ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት “አይፌ ጋቱዋ” ይባላል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ተገራዡን ከቅቤ፣ ከሥጋ፣ ከአይብና ከቅመማ ቅመም የተዘጋጀ ምግብ (kaacaa) መስተንግዶ ታደርግለታለች፡፡ የካጫ ሥርዓት አሟልታ የፈጸመች ጃላ ሚስት በጣም ትሞገሣለች፣ ትከበራለች፤ ተገራዡም ልጅ ዕድሜ ልኩን በአንቱታ እንዳከበራት ይኖራል፡፡ ካጫ ባበላች ዕለትም እንዲህ እያሉ ያሞጋግሷታል፡፡
Kaacida jaaliya wobaxan uttu
Balxxin uttu balxxin uttu
Ba aayero hnawusu ba aasaaga hanawusu
Ebelo na’ee ayaana gitee
A sheeshshawu hoola isheeshshawu hoola
ትርጓሜው “እንዲህ ያለች ወግ ደንብ አክባሪ ሴት ትውለድ ትክበር ሰጋር በቅሎ ይገባታል፡፡ ወግ ባህል ከሚያውቅ ቤተሰብ ተወልዳ ነው”፡፡ እንደማለት ነው፡፡
በአንፃሩ ይህንን የብሔሩን ወግ ያላሟላች የጃላ ሚስት በሕብተረተሰቡ እጅግ ትወገዛለች፤ በቃላዊ ግጥምም በየአጋጣሚው እንደሚከተለው ትወረፋለች
Kaaccenna jaaliya okashe booziya
Zazzariyan uttu qonashiya danccu
Baayero hanawusu… baawaaro hanawusu
I zariyasi poora… I zariyasi poora
ጠቅለል ያለ ትርጉሙ ለባህሉ ያልተገዛችን ሴት መዝለፊያ ሲሆን “እንዴት ያለች ገልቱ ሴት ነች፤ ክብር የማይገባት ነች፤ ይብላኝ እንዲህ ላሳደጉ ዘሮቿ!” የሚል እንድምታ አለው፡፡
ጃላው ተገራዡ ግርዙ በተፈጸመ ሶስተኛ ቀን ለተገራዡ የመኝታ መከለያ ቅርጮ (ቃርጣ)፣ ከጓደኞቹ ጋር የሚዝናናበትን የገበጣ መጫወቻና ክራር ይዞ ይመጣል፡፡ በሂደት በቃርጣው ምትክ የመጋረጃ ጨርቅ፣ በገበጣ ፈንታ የካርታ መጫወቻ ካርዶች እየተተኩ ነው፡፡ እንዲህ ሥርዓቱን ሳያጓድል የፈጸመን ጃላ ልጁ ዕድሜ ልኩን በአንቱታ ይጠራዋል፡፡ በደስታም በሐዘንም ከቤተሰቡ ጋር ይቆራኛል፡፡
በብሔሩ ልማድ ወንድ ልጅ አካሉን የሚያዳብርበት ወቅት የግርዛት ሥርዓት ወቅት ነው ተብሎ ስለሚታመን ተገራዡ ወርና ከዚያ ለበለጠ ጊዜ በሚገባ የአመጋገብ እንክብካቤ ታቅዶበት የሚከናወን በመሆኑ ፈጽሞ አይሰሰትም፡፡
የግርዛት ሥርዓት ማሳረጊያ
የተገረዘው ልጅ ቁስሉ ሽሮ ከሕብረተሰቡ ጋር በነባሩ ባህል እንዲሁ አይቀላቀልም፡፡ ተገራዡ አደን ወጥቶ አውሬ በመግደል ወንድነቱንና ብርታቱን ማስመስከር እንዳለበት ባህሉ ያዝዛል፡፡ ሥርዓቱን ያልፈጸመ በነባሩ ባህል በጣም ይናቃል፡፡ በለስ ቀንቶት አውሬ ገድሎ የተመለሰ ደግሞ ይፎክራል ያቅራራል፡፡ ቤተሰብ ዘመዶቹም በጣም ስለሚኮሩበት የገንዘብና የቁሳቁስ ስጦታ ያበረክቱለታል፡፡ ይህ ስጦታ “ዎይቱዋ” (woytuwa) ይባላል፡፡ ለግርዙ ሥርዓት ማሳረጊያ አውሬ ገድሎ ከተመለሰ “ቃጣራ ባጫላ ኬሊስ” ተብሎ ሲሞገስ ካልቀናውና ባጆ እጁን ከመጣ “ሞንቻ” (moonnichaa) ተብሎ እንደሚከተለው ይሰደባል፤ ይዘለፋል፡፡
Ne tamale…laa ne tamale
Awude laa ne kushee meeccttidoy
Yeleelle kushiyara de’iyaago
Neeni moonnichcha gidikki
Ta meeppe ,ommauoso
Ta aayee ta aawaa hayttaa kessaas.
ጠቅለል ያለ ትርጉሙ “ከግርዘት በኋላ ግደጃችንን ፈጽመን ወንድነታችንን አረጋግጠን የቤተሰባችንን ስም አኩርተናል፡፡ አንተ ግን ማፈሪያ ነህ የግርዘት ንፅህናህን ያላስመሰከርክ ከንቱ ነህ፡፡” እያሉ ያንኳስሱታል፡፡ በነባሩ ባህል ከግርዝ በኋላ አደን ወጥቶ ግዳይ ጥሎ መፎከር ባህል ነበር፡፡
የግርዘት ሥርዓት የማሳረጊያው ምዕራፍ ከሕብረተሰቡ “ሶፌ” (soofee) መውጣት ነው፡፡ በነባሩ ባህል ሶፌ የተገረዙ ልጆች ወይም የጫጉላ ጊዜያቸውን የጨረሱ ሙሽሮች ገበያ በመውጣት ራሳቸውን የሚያሳዩበት ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱ የሚከናወነው በአከባቢው ትልቅ በሆነ የገበያ ቦታና ቀን ነው፡፡
በሶፌ ቀን ተገራዡ ልጅ በአዲስ ልብስና ጫማ ተሸላልሞ አምሮበት በጓደኞቹ ታጅቦ ወደ ገበያ ይመጣል፡፡ የቤተሰቡ አባላትና ዘመዶቻቸውም በክት ልብሶቻቸው አሸብርቀው አብረውት ይወጣሉ፡፡ ከዚያም በገበያው ጥላ ያለበት ምቹ ከፍታ ሥፍራ ይመረጥና ይቀመጣሉ፡፡ ከቤት ለዚህ ሥርዓት ተብሎ በአህያ ተጭኖ የመጣ ጠላና ቦርዴ እየተቀዳ ይታደላል፡፡ ከመጠጡ ጋር ዘፈኑ ቀስ በቀስ ይጀምርና ጭፈራ ይከተላል፡፡ ግብዣውን የተቋደሱ ሁሉ ይመርቋቸዋል፡፡ “Hashshu hashshu! Kumtti be’ettte! Woriyooga b’ida yelinika be’itte” ይሏቸዋል፡፡ ትርጉሙ እንኳን ደስ ያላችሁ! የልጃችሁን ወንድነት አይተናል፤ ወልዶ ለመሳም ዳግም ያብቃችሁ ነው፡፡
የጃላው ባለቤት በዕለቱ በርከት ያለ ሎሚ በቅርጫት አሸክማ ታመጣና በልጁ ፊት ትዘረግፋለች፡፡ የመጣ ሁሉ እያነሣ ይበላል፡፡
የተገራዡ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የመጨረሻ ግብዣ በዕለቱ ያደርጉለታል፡፡ ከዕለቱ ገበያ በርከት ያለ ሥጋ ገዝተው ወደቤት ይወስዱና አስፈላጊው መሰናዶ ሁሉ ተደርጎለት ለቤተሰቡ ይቀርባል፡፡ ከመስተንግዶው መልስ ቅልጥ ያለ ዘፈንና ጭፈራ ተደርጎ የግርዛቱ ሥርዓት ማሣረጊያ ይሆናል፡፡
ተገራዡ እነዚህን ሂደቶች ሁሉ ካለፈ በኋላ ለዘወትሩ ተግባር ከሕብረተሰቡ ጋር ይቀላቀላል፡፡
በወላይታ በትኩረት ከሚከበሩ ባህላዊ ክዋኔዎች አንዱ የግርዘት ሥርዓት መሆኑን በአጭሩ ለመቃኘት ተሞክሯል፡፡
የግርዘትን ሥርዓት ሕዝቡ ከሃይማኖታዊ ዓላማው በይበልጥ ባህላዊ ትርጉም ሰጥቶት ያከብረዋል፡፡ ልጁ ለአካለ መጠን ለመድረሱ እንደዋዜማ ስለሚቀበሉት የመራቢያ አካል ንፅሕና ማጣሪያ ነው ይላሉ፡፡ የዕድሜ እርከኑ ደርሶ ይህን ያልፈጸመ ፀያፍ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ልጁም ከፍተኛ የስነልቦና ጫና ይፈጠርበታል፡፡ ከዚህ የተነሣ ወላጅ ቤተሰብ በሕይወት ዘመኑ እያለ ለልጆቹ ለመፈጸም በጥብቅ ከሚመኛቸው ኃላፊነቶች አንዱ ይህንን ሥርዓት መፈጸም ነው፡፡ በርግጥም ሳይንሱም የወንዶችን ግርዘት በዚሁ መልኩ ይደግፈዋል፡፡
ቃላዊ ግጥሞቹም የብሔሩን የግርዘት ሥርዓት ክወና ከማንፀባረቅ አንጻር ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በየትኛውም ጊዜና ቦታ አስተማማኝ አቅምና የኑሮ ደረጃ ያለው ጀግና ብርቱ ሰው በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ከ “ጃላ” አመራረጥ አስታክከው ያሣዩናል፡፡ የብሔርን ባህልና ወግ መጠበቅ ግድ እንደሆነ ለማሣየት ተገራዡን ልጅ ሲያደፋፍሩበት እናያለን፡፡ ባህላቸውን ያከበሩ እናቶች ሲሞገሱ ከባህል ያፈነገጡ ሲዘለፉ ማሳየት ችለዋል፡፡
በርግጥ ስነ-ቃል በባህሪው ተለዋዋጭ ነውና በነባሩ ባህል ገጽታ ላይ ለውጥ መኖሩ አይካድም፡፡ ከወቅቱ በስልጣኔና ትምህርት መምጠቅ ጋር ተያይዞ በርካታ የቅርጽ ለውጦች ተከስተዋል፡፡
በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ግን ይህንን ባህላዊ ሥርዓት ሕብረተሰቡ ጠንካራ ጎኑን እያዳበረ ጎጂ ጎኑን እየተወ ቢጠብቀው ከስነቃል ሀብትነቱ አኳያ የማህበረሰቡ መለያ ከሆኑ የባህል እሴቶች አንዱ በመሆን እንደሚያገለግል ይታመናል፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza