ከወላይታ ቀደምት ሥልጣኔዎች መካከል የሽመና ጥበብ አንዱ ሲሆን የባህላዊ አልባሳትና የአለባበስ ሥርዓቱም ዕድሜን፣ ጾታን፣ ማህበራዊ ደረጃን፣ የተለያየ አውዶችን (የጀግንነት የንግስና)፣ የአደን፣ የሀዘን፣ የደስታ፣ የአምልኮ… ወዘተ ስርዓትን መሰረት ያደረገ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዚህ መነሻ የብሔሩ የተለያየ የባህልና የዕደጥበብ ነፀብራቅ የሆነ የባህላዊ አልባሳት አሰራር እና የአለባበስ ሥርዓትን በዚህ ጽሑፍ እንቃኛለን፡፡
ለ. ሰሬ ሀዲያ (Seere hadiyaa) በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸው የማህበረሰቡ አካላት ከሚለብሷቸው የሀዴ ዓይነት ሁለተኛው ሆኖ አሰራሩ ልክ እንደ ዱንጉዛ በእጅ ጥበብ የሚሰራ የሀዴ ዓይነት ነው፡፡ አሰራሩም በቅድሚያ የተለያዩ ቀለማት ያሏቸው ክሮች ይዘጋጁና በሽመና እቃ ወይንም በአከባቢው ቋንቋ (Harppa) ውስጥ በአግባቡ ወጥ በሆነ ሁኔታ ይሰራል፡፡ ሲሰራም ቀይ፣ ቢጫ እና ጥቁር ሶስቱ ቀለማት ይዘትና ድምቀትን አጣምሮ በያዘ ሁኔታ በዝግዛግ ክህሎት ባለው ባለሙያ ይሰራል፡፡ እንደ ድንጉዛ ሀዴ ሁሉ ሴሬ ሀዴም በአብዛኛው እንደሚታወቀው ስራው ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ቅርጹና ይዘቱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በእጅ ከታች ወደ ባተለቱ አከባቢ ሰፋ ተደርጎ ለአለባበስ በሚመች ሁኔታ ይሰራል፡፡ ወገቡ ላይ ደግሞ ሙሉ ወደ ላይ ከለበሱ በኋላ በአከባቢው አባባል (Menttuwaa gixxiyooga) ለሚባለው አለባበስ በሚመች ሁኔታ ወደ ታች እንዲታጠፍ አመቻችተው ይሰፉታል፡፡ ይህን ልብስ የሚለብሱት የጦር ጀግኖች፣ የአደን መሪዎች፣ እንዲሁም ባለሀብቶች ናቸው፡፡
ሐ. ጉቱማ (Guttuma) ሀዲያ ይህ በወላይታ ብሔር ዘንድ በሶስተኛ ደረጃ የሚመደበው ሀዲያ ሱሪ እንደሌሎቹ በሸማኔዎች እጅ የመጀመሪያ ደረጃ ሂደቱን ካበቃ በኋላ በታዋቂ ባለሙያዎች በእጅ የሚሰፋ ነው፡፡ ጉቱማ ሀዲያ ማንኛውም ሰው ለሥራ ሲሄድ ይለብሳል፡፡ አሰራሩ እንደሌሎቹ ሆኖ ለማንኛውም ስራ በሚመች ሁኔታ ከሌሎቹ የሀዲያ ዓይቶች በትንሹ ተለይቶ ማለትም ወገብ ላይ ልክ እንደ ዘመናዊ ሱሪ ሆኖ ይዘጋጃል፡፡
ቡሉኮ በወላይታ ብሔር ዘንድ ከጥንት ጀምሮ እንደ ዘመኑ እየተሻሻለ የመጣ አሰራር የሚከተልና በተለያዩ አውዶች ከሚለበሱ አልባሳት መካከል ይጠቀሳል፡፡ በክብደትና በአሠራር ጥበብ የቡሉኮ ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው፡፡
ሀ. ፓታላ ቡሉኮ (Pattaala Bullukkuwa):- ይህ ቡሉኮ የሚሰራው ከድርና ከማግ ሲሆን አሰራሩ ድርብ ሆኖ በአከባቢው አጠራር አራት እጥፍ (oyddu achcha bullukuwa) የሚባል ሲሆን ርዝመቱም 16 ክንድ ነው፡፡ ይህንን የሚለብሱት ነገስታት የጦር መሪዎች መንግስት ሲፈቅድ እና ግዳይ የጣሉ ጀግኖች ፓታላ ቡሉኮን ይለብሳሉ፡፡
ለ. ቆጦጦ ቡሉኳ (Qoxooxo Bullukkuwa):- ቆጦጦ የሚሰራው ከቀይ እና ጥቁር ጥለት (ቀለም) ፈትል ሲሆን የሚለብሱት የጦር መሪ፣ የአደን መሪ እና በብሔሩ ባህል ብዙ ሀብት ያከማቹ በተለይ ከብት በማርባት የታወቀች እና ከመቶ በላይ ከብት አርብታ ያስቆጠረች (የግሟ) ሥርዓት የፈጸሙ ባልተቶች ይለብሱታል፡፡
ሐ. ጫጫፎ ቡሉኳ (Caccafo Bullukkuwaa):- ጫጫፎ ቡሉኮ የሚሰራው ከቅቤና ከቀይ አፈር (Baara) በሰፊው ከተለወሰ እጅግ ውብ በሆነ መንገድ የሚዘጋጅ የቡሉኮ ዓይነት ሲሆን ግዳይ የጣሉ የጦር ጀግኖች እና የአደን መሪዎች (Gaadawa) ይለብሱታል፡፡
መ. ሻሎ ቡሉኳ (Shaalo Bullukkuwaa):- ይህም እንደ ጫጫፎ ከቀይ አፈር (Baara) በመጠኑ በተለወሰው ማግ በሸማኔዎች ተሰርቶ የሚለበስ መለስተኛ ቡሉኮ ሲሆን የሚለብሱትም ማንኛውም ባለሀብት እና ጀግናዎች ናቸው፡፡
ሠ. ጊጤቷ (Gixettuwaa):- ጊጠቷ እንደ ሌሎች የቡሉኮ ዓይነቶች በባህላዊ የሽመና መሳሪያ (Harppaa) የሚሰራ ሲሆን ለአዘጋጃጀቱ ነጭ ጥጥ ተፈትሎ ከተገመደ በኋላ ተለቅሞ በሥርዓት ተደውሮ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ልብስ ሴቶች ከወገባቸው ዙሪያ ካገለደሙ በኋላ በመቀነት አሰሪው ወደ ላይ በኩል የሚቀረውን አጥፊው ወደታች ይለቁና ከላይ ጥብቆ ይደርባሉ፡፡
ረ. ጥብቋ (Xibbiquwa):- ጥብቆ እንደ ሌሎች የቡሉኮ ግብአቶች ልብሶች ወጥ በሆነ መንገድ ተሰርቶ በእጅ ከተሰፋ በኋላ ሴቶች በቡሉኮ ላይ የሚደርቡት አላባሽ ነው፡፡ ጥብቆ ሲዘጋጅ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ከተዘጋጀ የራሱ የሆነ ልዩ ውበት አለው፡፡ ጥብቆ በአንድ ፈርጅ በነጠላም ሆነ በድርብ ተሰፍቶ ሊለበስ ይችላል፡፡
2. የባህላዊ አልባሳት የአለባበስ ሥርዓት
በወላይታ ብሔር የአለባበስ ዕድሜን፣ ጾታን እና ነባሩ ማህበራዊ ደረጃን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡
የጀግንነት አለባበስ
አንድ ሰው ጀግና የሚባለው በተለያየ ጊዜያት ያከናወናቸው ጀብዶችና የሰራቸው ገድሎች በማህበረሰቡ ዘንድ ጀግንነቱን የሚገልጹ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ በወላይታ ብሔር ዘንድ እነዚህ ጀግኖች የጀግንነታቸው መገለጫ የሆኑ አልባሳትና ተያያዥ ጌጦችን ይጎናጸፋሉ፡፡
ለአብነት ያህል፡- ንጉስ በንግስና ወቅት የሚለብሷቸው ካባ ከላይ መደረብ፣ ዱንጉዛ ሀዲያ በወላይታ በሔር ዘንድ ልዩ ስፍራ ያለውን በመልበስ ከላይ ደግሞ (oyiddu achcha bullukuwaa) ትልቁን ቡሉኮ በመደረብ በጭንቅላቱ ላይ ንግስናውን የሚገልጽ አስራ አምስት ጡቶች ያለበትን ካላቻ kallachcha (ዘውድ) በመጫን በግራ እጅ መሐለኛው ጣት ከብር በቀኙ ደግሞ ከወርቅ የተሰራውን ቀለበት በማድረግ የንግስና ሥርዓቱን ይፈጽማል፡፡
በጦርነት መሪ (Tooraa Gadaawaa) በመሆን የመራ ሰው እና በአደን ግዳይ የጣለ የአደን መሪ ወይንም (shankka gadaawa) ዱንጉዛ ሀዲያ በመልበስ ከቀይ አፈር ቀለም (Baaraa) እና በተነጠረ ቅቤ የተለወሰ የጠነከረ ቡሉኮ (cacafo afalla) ለብሶ በክንዱ ሂርቦራ (hirbboora) የሚባል ከዝሆን ጥርስ የሚሰራ አምባር በማድረግ በጸጉሩ ሰጎን ላባ ይሰካል፤ በግምባሩ ደግሞ ዘውድ (kallachcha) በማሰር በጦርነት ሰውን ወይም በአደን ነብር ከገደለ በጆሮው ከብር የተሰራውን በሌጫ ዱንዳ (Belecaa dundda) ያንጠለጥላል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ አደን ሥፍራ ሲሂዱ ወንዶች ዱንጉዛ ሀዲያን ታጥቀው ከላይ መደረቢያውን (Shamaciya) ይደርባሉ፡፡
የሰርግ ወቅት ልብሶች
በወላይታ ባህል ልዩ እና ተመልካችን የሚያስደምሙ የሠርግ ወቅት የአለባበስና የአጊያጌጥ ሥርዓት ነበር፡፡ ሙሽራው ሙሽሪትን ከቤተሰቦቿ ዘንድ ለማምጣት ሲሄድ ሀዲያ የተባለውን ባህላዊ ሱሪ በመታጠቅ ከላይ መደረቢያውን አሳራ (Asaraa) የተባለውን መለስተኛ ጋቢ በመደረብ ጦር ይይዛል፡፡ ሚዜዎቹም ከጎኑ በመሆን ሴሬ ሀዲያ በመልበስ በላያቸው ላይ አሳራን በመደረብ በፈረስ ላይ ተቀምጠው ወደ ሙሽሪት ቤት ያመራሉ፡፡ ሙሽሪት ቡሉኮ አገልድማ ጥብቆ (ሻማጭያውን) ደርባ ፊቷ እንዳይታይ በነጠላ ትሸፈናለች፡፡ የሴት ጓደኞችም ቡሉኮ አገልድመው ጥብቆ በመደረብ ሙሽሪትን አጅበው ለባኦ (Ba’o Jaalaa) አዛይ ሚዜ ያስረክቧታል፡፡
ሙሽሪት የጫጉላ ጊዜዋን ጨርሳ ከመውጣቷ በፊት በባህሉ መሰረት የሚፈጸመውን የሶፌ ሥርዓት ትፈጽማለች፡፡ ለዚህ ሶፌ ስርዓት ከምትለብሳቸውና ከምታጌጣቸው አልባሳትና ጌጣጌጦች መካከል ቡሉኮ፣ ጋቢ፣ ወይንም ነጠላ፣ ሻማጪያ የአንገት መስቀል፣ የጣት ቀለበት (Migiduwa)፣ አምባር (sagayuwaa) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዘንባባ እና ከቀርከሃ የሚሠራውን ዲባቢያ (ባህላዊ ጃንጥላ) በመያዝ የሶፌ ሥርዓት ትፈጽማለች፡፡
በወላይታ ብሔር ባህል የለቅሶ ሥርዓት ለሕጻን፣ ለወጣት፣ ለጎልማሳ እንዲሁም የዕድሜ፣ የፆታና ማህበራዊ ደረጃን ያገናዘበ የአለቃቀስና የአለባበስ ሥርዓት ያለው ሲሆን ጀግና ወይንም ሀብታም ከሞተ አዋጅ ነጋሪው (araddiyage) ለምድ በመልበስ በፈረስ ላይ በመቀመጥ ገበያ ወዳለበት በመሄድ የሟቹን ጀግንነት፣ የቤተዘመዶቹን ጉብዝና በእንጉርጉሮ እና በቀረርቶ ካሰማ በኋላ የለቅሶው ሥነ-ሥርዓት የሚፈጽምበትን ዕለት ያውጃል በለቅሶው ዕለት ለቀስተኞች የሟች ዘመዶች ልብሳቸውን ገልብጠው ይለብሳሉ፡፡ በዕለቱ ወንዶች ሀዲያ ሱሪ በመታጠቅ ከላይ የነብር ወይም የአንበሳ ቆዳን፣ ለምድ (ካባ) በመደረብ በራሳቸው ላም ከጉሬዛ ቆዳ የሚሰራውን ኮፊያ (Ukaa) ኡካ በመድፋትና ጦር በመያዝ ያቅራራሉ (zilaalosona)::
ወጣት ወንዶች ለአቅመ አዳም የደረሱ ወጣት ወንዶች ከጥጥ ተፈትሎ በሸማኔዎች የተዘጋጀውን አሳራ (asaraa) የተባለውን ግማሽ ጋቢ መሳይ አገልደመው ከወገባቸው በላይ ደግሞ ይደርባሉ፡፡ ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶችም እንደዛው በሕጻንነታቸው የሚለብሱትን ማሽኮ (mashkoo) በመተው አሳራ መልበስ ይጀምራሉ፡፡ የማሽኳ (mashkuwaa) አሰራር ድር በብዛት ከአንድ ስንዝር ባልበለጠ ሁኔታ ተገምዶ በጫፉ ላይ ዛጎል (yeleeluwa) እና ከስስ ብረት ነክ (shappuwaa) ከሚባሉ ጌጣጌጦች ተሠርቶ ዛጎል የሚያያዝለት ሲሆን ሕጻናቱ ሲንቀሳቀሱ በሚሰጠው ድምጽ አልፎ የተገመደውን ድር ነፋስ እንዳያነሳው ክብደት እንዲኖረው ይረዳል፡፡
የሴቶች አለባበስ
አንዲት ሴት የግሟን ሥርዓት በምትፈጸምበት ጊዜ የምትለብሳቸው (qoxooxuwaa) የሚባል በቀይ እና ጥቁር ቀለማት አሸብርቆ የሚሰራ ትልቅ የክብር ልብስ በመልበስ፣ ካላቻ ከዝሆን ጥርስ የሚሰራውን በግምባሯ ላይ ታደርጋለች፡፡ በጸጉሯ ላይ የሚሰካውን የሰጎን ላባ ወይንም ከብረት የሚሰራውን ባሊያ (baalliyaa) በማድረግ በእጇ ግሞ ጉሙቧ (Gimo Qumbbuwa) ትይዛለች፡፡ ሌላው የዚህ ሥርዓት መገለጫ የሆነውን ከነሐስ የሚሰራውን ግሞ ብራት (Gimo Birattaa) ከኋላዋ የምታጅበው አጀቢ ትይዝታላች፡፡ ባለሀብቷ በጣቶቿ የሚደረጉ ከብር የሚሠሩ (Bira migiduwaa) በእጇ የምታጠልቀው አምባር (sagayuwa) በእጇ፣ በክንዶቿ wogoruwa በማሰር ሥርዓቱን ትፈጽማለች፡፡
ያገቡ ሴቶች በባህሉ እንደየአቅማቸው የተለያዩ ደረጃ ያላቸውን የቡሉኮ ዓይነት (qooxuwaa, gixetuwaa, iriichchuwaa) በዳሌ አከባቢ ሰፋ ካለ ተናፋነፍ መሳይ ሱሪ (liqa suriyaa) ጋር ለብሰው ከጥጥ ፈትል የሚሠራዉን ሻማጭያ shmaciya እና ጥብቆ (xibiqo) አላባሽ በመልበስ ነጠላ ከላይ ይደርባሉ፡፡
ሴቶች ቡሉኮቸውን ሲለብሱ ወንዶች በጦርነት አውዶች Dancuwa (መቀነት) ይታጠቃሉ፡፡ የሴቶች መቀነት ልብሱን አጥብቆ እንዲይዝላቸው ሲታጠቁ የወንዶች መቀነት ደባላ ዳንጩዋ (Dabala Dancuwaa) ወንዶች በጦርነት ጊዜ የሚታጠቁት ሆኖ በጦርነት አውድ ከቆሰሉ ደም እንዳይፈስበት ለማሰር እንደሆነ የዕድሜ ባለጸጎች ይገልጻሉ፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza