• Call Us
  • +251465512106

ባህላዊ የሀብት ማብሠሪያ ሥርዓት በወላይታ

   የሰው ልጅ ማህበራዊና ባህላዊ ክንዋኔዎችን ግዑዝነት ካላቸው ነገሮች ጋር የተያያዙና እነዚህም የማንነት መገለጫዎች፣ የፈጠራ ጥበቡና የክብሩ መታወቂየዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህም ማህበራዊ ክንዋኔዎችና ሥነ-ሥርዓቶች ማህበራዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ… አንዲሁም ፍላጎቱን ለማሟላት በግልና በጋራ የሚከናውናቸው ድርጊቶች ናቸው፡፡

   በወላይታ ብሔር በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የሚከናወኑ የተለያዩ ባህላዊ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ባህላዊ የሀብት ማብሠሪያ ሥርዓት “Daala, liiqaanne gimuwaa” ዳላ፣ ሊቃ እና ግሟ ይጠቀሳሉ፡፡

Daalaa (ዳላ)

የዳላ (daala) ሥርዓት የሚፈጸመው አንድ አርሶ አደር ለፍቶ፣ ጥሮ ግሮ ያከማቸውን ሀብቱንና ንብረቱን በአግባቡ ጠብቆ እንደዛውም ከብቶችን በየሰው ቤትና በራሱ ቤት በማስጠበቅ ቁጥራቸው አንድ መቶ ሲሞሎ የሚፈፀም ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ በወላይታ ነባር ባህል የከብት ርቢ ከሀብት መገለጫዎች ዋነኛው ሲሆን ይህንን ብልጽግናውን ማብሰሪያ ሥርዓት Daala (ዳላ) በመባል ይታወቃል፡፡

የሀብት ብሥራቱ ሥርዓት ሂደት ባለሀብቱ ከብቶች ቆጠራ የሚከናወን ሲሆን በሥርዓቱ ከከብቶቹ መካከል ተመርጦ በተዘጋጀው በሬ ከሚታሰር daala (ቃጭል) ጋር ይያያዛል፡፡የዳላ ሥራዓት ለመፈጸም አርሶ አደሩ የከብቶቹ ቁጥር መቶ መድረሱን ማረጋገጭ ነው፡፡ የከብቶቹ ቁጥር አንድ መቶ መድረሳቸውን ካረጋገጨ በኋላ ለሥርዓቱ አፈጻጸም አስፈላጊው ዝግጅት ይደረጋል፡፡ የዝግጅቱ የመጀመሪያ ተግባር ለወዳጅ ዘመዶች፣ ለመንደርተኞ እና ለሥርዓቱ ታዳሚዎች ቀጠሮውን ማሳወቅ ሲሆን የዳላ ሥርዓት የሚፈጸምበት ቅዳሜ ዕለት ይሆናል፡፤ ምክንያቱም ዕለቱ ገዳም ቀን ተብሎ ስለሚታመን ነውና፡፡

ለሥርዓቱ ክዋኔ አንድ ሳምንት ሲቀረው ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ ቆጠራ የሚካሄድበትን ሥፍራ የሚያዘጋጁ ሲሆን ሥፍራው በግለሰቡ ቀዬ ላይ ሆኖ ሰፋ ተደርጎ ዙሪያ ክብ በጸዳቂ እንጨት ይታጠራል፡፡ በመሀሉ ምሶሶ አይነት ጫፉ ሳይቆረጥ እንዲቆም የሚደረግ ሲሆን አዘገጃጀቱም ለቆጠራ የሚሰበሰቡት የከብቶችን ቁጥር ባገናዘበ መልኩ እንጨት የሚቆምበትን ሥፍራ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡በአጥሩ መግቢያው ባሀብቱና ቆጣሪው ረዳት ቆጣሪዎች ይቆማሉ፡፡ ለድግሱ ዝግጅት በባህሉ መሰረት ከሚሰናዱ ምግብና መጠጥ መካከል ዋና ዋናዎቹ ሙቿ(muchchuwaa), ፖሻሙዋና (Pooshamuwaa)፣ ሎጎሙዋ(loggomuwaa) ሲሆኑ ቦርዴ (bordiyaa) መጠጦች ይጠቀሳሉ፡፡

ከሥርዓቱ ዕለት አንድ ቀን ቀደም ተብሎ የእግዶች ማረፊያ ይዘጋጃል፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ዋዜማ ዳላውን (ቃጭሉን) ያዘጋጀው ባለሙያ ከነቃጭሉ እና ከብት ቆጣሪው ባለሀብት ቤት  (Gabarachchaw) እየበሉና እየጠጡ ባለሀብቱን እያሞገሱ ያድራሉ፡፡

በዳላ ሥርዓት ጅማሮ የባለሀብቱ ባለቤቱ ከሳሎን ሚስትዬው ከጓዳ በእምብርክክ እንደ ከብት ወደ ቆጣሪው (Gabarachchaw) ዘንድ በመቅረብ የተዘጋጀላቸው ትኩስ ወተት “yeesuwaa” አብረው ይጎነጫሉ (Daggoosona):: በመቀጠል መሰል ዳላ ሥርዓት ለመፈፀም ዕቅድ ያለው ባለሀብት በዕለቱ ከሚፈፀመው ባለሀብት ጋር አብረው የ“daggetta” ሥርዓት ያከናውናል፡፡ በመቀጠል ጋባራቻው “Gabarachchaw” ከቀንድ በተሠራው ማኒኪያ (mooqiyaa) የቀረበላቸውን ምግብ በባለሀብቱና ባለቤቱ ጀምሮ ታዳሚዎችን ያጎርሳቸዋል፡፡

በመቀጠል ቆጣሪው “Gabarachchaw”፣ ባለሀብቱ እና ታዳሚዎች የተጋበዙ ዘመድ አዝማድን ወደ ተዘጋጀው የቆጠራ ቦታ ይመራሉ፡፡ የቆጠራውን ሂደት ለመከታተል ታዳሚዎች የአጥሩን ዙሪያ ከብበው የሚቆሙ ሲሆን “Gabarachchaw” እና ባለሀብቱ ወደ ቆጠራው መግቢያ በተዘጋጀላቸው ስፍራ በመቆም ቆጠራወን ያከናውናሉ፡፡

   በዳላ ሥርዓት ከብቶችን ለመቁጠር የሚጠራው “Gabarachcha” ለራሱ ከአራት ዓመት በፊት ይህንን ሥርዓት የፈጸመ መሆን እንዳለበት ባህሉ ያዝዛል፡፡ አለበለዚያ የተቆጠሩ የግለሰቡ ከብቶች አይበረክቱም ተብሎ ይታመናል፡፡

ዋናው ቆጣሪ እሱን በቆጠራ ከሚያግዙት ከሌሎች ስድስት ሰዎች ጋር በአጥሩ መግቢያ በር አጠገብ በመቆም ቆጠራውን የሚካሂድ ሲሆን ቆጠራውን ሲጀምር በቅድሚያ ወደ አጥር ውስጥ እንዲገቡ የሚደረጉት በባለሀብቱ ቤት የሚኖሩ ከብቶች ናቸው፡፡ ቀጥሎ ከውጭ የመጡት እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ “Gabarachcha” ከብቶቹ ወደ አጥሩ ውስጥ ሲገቡ በያዘው ለስለስ ባለ የቀርከሃ ቅርንጫፍ ጀርባቸውን እየነካ የሚቆጥር ሲሆን በቆጠራው ከሚረዱት ቆጣሪዎች ቆጠራውን ከጣናቀቀ በኋላ ባለሀብቱን እንደሚከተለው ይመርቃል፡፡

            Xilikke xinxxichchoy geloppo!

            Aaquwaan geloppo!

            Ullattay geloppo!

            Hayqqoy harge geloppo!

እያለ ይመርቃል፡፡ ትርጓሙ ክፉ አይንካችሁ፣ በሽታ አይንካችሁ፣ ሞት አይግባባችሁ እንደማለት ነው፡፡

ይህ የቆጠራው ሥርዓት ሲጠናቀቅ ባለሀብቱ ለቆጣሪው እና ቃጭሉን ላዘጋጀው የእጅ ባለሙያ የመደባቸውን ከብቶች በስጦታ መልክ ያበረክታል፡፡ በመቀጠል የሁሉቃ (hulluqaa) ሥርዓት ይከናወናል፡፡

      በሥርዓቱ  ከአጥሩ (ከበረቱ) አከባቢ በሁለት ሜትር ጥልቀት ተቆፍረው ውስጥ ለውስጥ በተገናኙ ጉድጓዶች ውስጥ ባለሀብቱ ለሥርዓቱ ማስፈፀሚያ የተዘጋጀው አንድ ጋን ቦርዴ፣ ወተት፣ የተነጠረ ቅቤ፣ ማር አንድ ላይ በመጀመሪያው ጉድጓድ ውስጥ አፍሰው ወደ ሁለተኛው ጉድጓድ እንዲተላለፍ ያደርጋል፡፡ በተጨማሪ በጉድጓድ ውስጥ አንድ በሬ እና በግ ባለሀብቱ በጦር የሚባርክ ሲሆን የእንስሳቱ ደም ቀድሞ ከነበረው ፈሳሽ ጋር ይቀላቀላል፡፡  በጉድጓድ ውስጥ የታረደውን ሥጋ የአከባቢው ወጣት አርሶ አደሮች ወደሌላ ሥፍራ በመውሰድ እንደቅርጫ ይከፋፈሉታል፡፡

      ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ባለሀብቱ በጉድጓዶች ውስጥ ሾልኮ የማለፉ ሥርዓት (hulluqaa) ይፈፀማል፡፡ በሂደቱ መጀመሪያ በአንደኛው ጉድጓድ ውስጥ በመስመጥ ወደ ሁለተኛው በማስተላለፊያ ቱቦ በኩል ሾልኮ በማለፍ በሁለተኛው ጉዳጓድ ውስጥ ገብቶ ቀጥ ብሎ ይቆማል፡፡ ባለሀብቱ ያገባች ልጅ ካለችው የሴት ልጇ ባል (አማቹ) የባለሀብቱን እጅ በመያዝ ከጉድጓድ ውስጥ ያወጣዋል፡፡ የ hulluqaa ሥርዓት የሚፈጸመው በባህሉ ሀብቱ በትክክለኛ እና እውነተኛ መንገድ የተሰበሰበ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡

      ባለሀብቱ ከጉድጓድ ውስጥ እንደወጣ ሽለላውን በዜማ ያሰማል፡፡ በዚህ አኳኋን የዳላ ሥርዓት እንደተፈጸመ እንግዶች ወደ ምሳ ግብዣው የሚያመሩ ሲሆን በወቅቱ ጋባራቻው

Zaqqi zaaqoua ashuwa

Zaaliyaa billamaan qanxadda,

Biilliyawu coraa shiishshidogaan,

Masoppiyan giigaan uttisiidoogan,

Maxidi haarido miishshappe

Abbuulla kareen ogidoogaan… እያሉ ያሞግሰዋል፡፡

ሥርዓቱ እንደተፈጸመ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

  1. Liiqa (ሊቃ)

 “ሊቃ” ማለትም ላቀ ዘልቆ ሄደ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በብሔሩ ባህል መሠረት በቁጥር አንድ ሺህ እና ከዚያ በላይ ቁጥር ያላቸው ከብቶች ያረባ አንድ ግለሰብ ድግስ ደግሶ እና ዘመድ አዝማዱን ጠርቶ ከብቶን እንደ ዳላው በማስቆጠር ሀብቱን የሚያበስርበት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ለሥርዓቱ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችም ሆነ አስፈላጊው ሁሉ ልክ እንደ ዳላው ተመሳሳይ ሲሆኑ የአጥሩ (በረቱ) አዘገጃጀት ከፀዳቂ እንጨት ሆኖ የተቆጣሪ ከብቶችን ቁጥር በማገናዘብ ነው፡፡

በ Liiqaa ዋዜማ ዕለት ወደ ባለሀብቱ ቤት ተጋብዘው መጥተው ባደሩ እንግዶችና በዕለቱ  ዕድምተኞች ታጅቦ የሊቃው ፈፃሚ ባለቤት እየፎከረ እና እየሸለለ ወደ ቆጠራ ማማ ያደርሱታል፡፡ የከብት ቆጠራ ደምቆ ሥርዓት ከመጀመሩ ቀደም ተብሎ አንድ ሰንጋ በሬና አንድ በግ ታርዶ ደማቸው ከተቀላቀለ በኋላ “ሞላና (mollanaa)” የተባለው በባህሉ የ Liiqaa ከብቶችን እንዲቆጥር ሥልጣን የተሰጠው ግለሰብ ጣቱን በደም እየነከረ በተሰበሰቡ ከብቶች ላይ ይረጭባቸዋል፡፡ ሥርዓቱ ከብቶቹን በሽታ እንዳይነካቸውና የአርቢያቸውም ዕድሜም እንዲረዝም ያደርጋል ተብሎ በባህሉ ስለሚታመን ነው፡፡ ባለሊቃው ማማው ላይ ከመውጣቱ አስቀድሞ ደምና ትኩስ ወተት በተቀላቀለበት ጉድጓድ ውስጥ ይገባና እንዲሻገር ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም እንደ ዳለ ሥርዓት ሁሉ ከብቶቹ የራሱ እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለማረጋገጥ ሲባል ሲሆን  የሰውን ከብት ቀላቅሎ ሥርዓቱን ከፈፀመ ከብቶቹ በሙሉ ያልቃሉ የሚል የብሔሩ ባህላዊ እምነት ስላለ ነው፡፡

   በመቀጠል ሰውዬው ማማው ላይ ወጥቶ በመቀመጥ ሥነ-ሥርዓቱን ይከታተላል፡፡ በቅድሚያ በግለሰቡ ቤት ረዥም ዕድሜ የቆየች ላም ተመርጣ በቀዳሚነት ወደ በረቱ እንድትገባ ይደረጋል፡፡ በመቀጠል ቆጣሪው “ሞላና (mollannaa)” የተሰበሰቡ ከብቶችን አንድ በአንድ በእርጥብ ቀርከሃ ቅጠል እየነካ ወደ በረቱ ሲገቡ ይቆጥራቸዋል፡፡ “ሞላና (mollanaa)” ይህን ተግባር ለማከናወን የግድ የሊቃን ሥርዓት ከፈጸመ አንድ ዓመት ሞልቶ ያለፈው መሆን እንዳለበት ባህሉ ያዝዛል፡፡ ነገር ግን ዓመት ሊሞላው አንድ ቀን ቢቀረው እንኳን “ሞላና (mollanaa)” ተብሎ ከብት እንዲቆጥር ሥልጣን አይሰጠውም፡፡ ይህም የሚደረግበት ዋናው ምክንያት ልክ እንደ ዳላው የባሀብቱ ከብቶች አይበረክቱም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ከብቶቹ ተቆጥረው ሲያልቁ በመጨረሻ ወደ በረት በሚገባው በሬ አንገት ላይ “ዳላ” ቃጭል ይንጠለጠልበታል፡፡ በመቀጠልም በሬ ይታረድና የሥነ-ሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል፡፡

የቆጠራው ሥነ-ሥርዓት እንዳበቃ ባለ ሊቃው ግለሰብ ከሸማ ተሠርቶ በጥለት የተዠጎረጎረውን ሴሬ ሃዲያ የሚባለውን ባህላዊ ሱሪ በመታጠቅ ከላይ በሻማጪያ ላይ የነብር ወይም የአንበሳን ቆዳ ደርቦ በፀጉሩ ላይ የሰጎን ላባ ይሰካል፡፡ ባጌጠ ፈረስ ላይ ሆኖ በከብቱ ቁጥር በክር የተያያዘ የሾላ ወይም የእንቧይ ፍሬ አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ በማገጥ በእጁ ቃጭል ይዞ በእድምተኞች ታጅቦ ከሚስቱ ጋር በመሆን በአቅራቢያው ወደሚገኘው ገበያ ያመራሉ፡፡

በገበያ ውስጥ uldduduwaa (የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ) እየተነፋ ወደ ገበያው ሲደርሱ ሚስቱ በተቀመጠችበት ፈረስ አስረግጣ አንድ ጋን ሙሉ ቦርዴ ከሰበረች በኋላ ተነጥሮ ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቦታ በመሄድ ባልና ሚስት ቦርዴውን ባንድ ቅል (daggetta) በጋራ ይጠጣሉ፡፡ እየተጫወቱ ከቆዩ በኋላ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ የሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል፡፡

ግሟ (Gimuwaa)

      በነባሩ የወላይታ ባህል በአብዛኛው ጊዜ የሊቃ እና የዳላን ሥርዓት ያከናወነ ግለሰብ ባለቤት ግሟ (የሴቶች ባህላዊ የሀብት ብስራት) ሥርዓት ትፈጽማለች፡፡  ወይንም እንድት ሴት ጠንክራ ሰርታ በራሷ ያረባቻቸው ከብቶች መቶ እና ከዚያ በላይ ከሆነ ደግሞ ይህንኑ ሥርዓት ትፈጽማለች ማለት ነው፡፡

      በ Gimuwa ሥርዓት ከብት የምታስቆጥር ሴት የመውለድ ዕድሜን የዘለለች (ያረጠች) መሆን አለባት፡፡ ሥርዓቷን የፈጸመች ሴት ከፍተኛ ማህበራዊ ከበሬታ የሚሰጣት ሲሆን የማማከር ሚና የምትጫወት ሲሆን የማጀትም ሆነ የግብይት ሥራ አታከናውንም አገልጋዮቿ ያከናውኑላታልና፡፡ እንዲሁም ከብረት የተሠራውን ግሞ ብራታ       “Gimo birataa” አምባር በእጇና በእግሯ አጥልቃ በአሽከሮቿ ታጅባ ወደ ሥፍራው ትሄዳለች፡፡

      የግሟ ሥርዓት የምትፈጽመው ሴት ሀብቷን ለማብሰር ከባሏ ጋር ወደ ገበያ ስትገባ  በተዘጋጀላቸው ስፍራ ሲቀመጡ ታዳሚዎችም በዙሪያቸው የሚቀመጡ ሲሆን ሶስት ጋን ቦርዴ መስተንግዶ ይደረግላቸዋል፡፡ በሂደቱ ብልጽግና ለመግለጽ የተወሰኑ ሳንቲሞች በመበተን በገያተኞችን ትሸልማለች፡፡

      በዚህ ሁኔታ ሥርዓቱ እየተፈጸመ እያለ ከሰራተኞቿ የተወሰኑት ወደ ገበያ ውስጥ በመግባት ለሽያጭ ከቀረቡት የዕቃ ዓይነቶች አንዳንድ በመግዛት ያመጣሉ፡፡ ይህንን ሰራኞቿንና አጃቢዎቿን አሸክማ በእነርሱ ታጅባ ወደቤቷ ትመለሳለች፡፡ ከዛን ቀን ጀምሮ “onakka gimaasu” ተብላ ትከበራለች፡፡ ይህ የሥነ-ሥርዓቱ ማብቂያ ይሆናል፡፡

      ከፍ ብሎ በአጭሩ የተመለከትነው ማራኪው እና ተመልካችን የሚመስጠው የወላይታ ብሔር የሀብት ማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ሲከበር እና በብሔሩ ተወላጆች ሲከናወን የኖረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የአከባበሩ ሥርዓት ጥንታዊ ባህላዊ ይዘቱን እየለቀቀ የመጣ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል ባለሀብቶችን የሚያወድሱ ነባር ሥነ-ቃላት በሌሎች ተተክተዋል፡፡ ይህ እና ሌሎችም የሥርዓቱ መልኮች እየተበረዙ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ሥርዓት ቁጠባንና ተግቶ መሥራት የሚያበረታታ በመሆኑ አጠናክረው ቢይዙ ለተያያዝነው ልማታዊ ባለሀብት ማፍራት ስትራቴጂ እንደሚጠቅም ይታመናል፡፡