• Call Us
  • +251465512106

ሳንታሪያ/በወላይታ ወንጀልን በጋራ የመከላከል ባህል/

  "ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ" የሚለውን ቃል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዘውትረን እንሰማለን፡፡ መንግስት የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የተሻለ አማራጭ ብሎ ከቀየሳቸው ስልቶች አንዱ ወንጀልን ከሕብረተሰቡ ጋር በጋራ የመከላከል መንገድ ነው፡፡ የወላይታ ሕዝብ ወንጀልን በጋራ የመከላከል ሥርዓት ከረዥም ጊዜያት በፊት ጀምሮ ሲተገብረው መኖሩን ያውቁ ይሆን? "ሳንታሪያ"ን በተመለከተ ከዚህ ቀጥለን የምናስነብበው ፅሑፍ በቂ ምላሽ ይሰጥዎታል፡፡

      "ሳንታሪያ" የሚለው ቃል እና ትግበራው ከ1940ዎቹ መግቢያ አከባቢ ጀምሮ በወላይታ ሕዝብ ዘንድ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

      ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ጊዜ ከህብረተሰቡ መካከል የወጡ ጋጠወጥ ወሮበሎች ሕዝቡን እጅግ ያስጨንቁት ነበር፡፡ ወሮበሎቹ  ቤት እየሰረሰሩ በመግባት ሀብት ንብረት መስረቅ፣ ከብቶችን መዝረፍና አላመች ሲላቸው ቤት በሌሊት ማቃጠል ሥራቸው አድርገው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወንዝ ውሃ ልትቀዳ የወረደች፣ ወይም ከገበያ የምትመለስ ወይም  በተለያዩ አጋጣሚዎች መንገድ ላይ ያገኟትን ኮረዳ ይጠልፉ ስለነበር ሕዝቡ እጅግ ይማረር ነበር፡፡ ከዚህም በመነሳት  "ምን ይበጀናል? እንዴት እናድርግ?" በሚል ሲመክርና ሲዘክር በተናጠል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ከየጎጡ በጋራ በመደራጀት ጥበቃ ማድረግ መፍትሔ ሆኖ ያገኙታል፡፡ ለትግበራውም በስምምነት ህግና ደንብ በማውጣት የአከባቢውን ሰላም የማስጠበቅ ሥርዓት ማጠናከር እንደተቻለ የዕድሜ ባለጸጋዎች ያስረዳሉ፡፡

      "ሳንታሪያ" የሚለው ቃል ስያሜ በየጎጡ ከተቀለሱ ጥበቃ ማዕከላት ጋራ ተያይዞ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በወቅቱ በየሥፍራው የሚታዩትን የጥበቃ ማዕከላትና የተቀለሱበትን ዓላማ የተረዳ አንድ እንግሊዛዊ "ሴንተር" (center of crime protection) በማለት መጥራት ይጀምራል፡፡ እናም ሕብረተሰቡ "ሴንተር"  የተባለውን በራሱ የአጠራር ዘይቤ በመለወጥ "ሳንታሪያ"  ብሎ እንደጠራና እስከዛሬም በዚሁ እንደሚጠራ መስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

      ሳንታሪያ የሚቀለስበት ቦታ አመራረጥና አሠራሩ ከሌላው ቤት ይለያል፡፡ መቼም ቢሆን ሳንታሪያ የሚሠራው በመስቀለኛ መንገድ ጠርዝ ላይ ወይም በቀዬው መንትያ መንገድ አማካይ ቦታ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ወንጀል ፈጽመው ከአንዱ ቀበሌ ወይም ሠፈር የሚወጡትን መንገድ ዘግቶ ለመያዝ ሰለሚመች ነው፡፡ በመሆኑም ለወንጀል ተጋላጭ የሆኑ አከባቢዎች ልዩ ትኩረት ያገኛሉ፡፡

      የጥበቃ ማዕከሉ (ሳንታሪያ) ሲሰራ የቦታ መረጣ ብቻ ሳይሆን ዲዛይኑም በጥንቃቄ ይሰራል፡፡ ቤቱ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች ለማየት በሚመች መልኩ የተሠሩ መስኮቶችና ከመንገድ ትይዩ የሆኑ ሁለት በሮች አሉት፡፡ አገልግሎቱም ተረኛ ጠባቂዎች በየአቅጣጫው የሚታዩ መንገደኞችን ማንነት እንዲለዩና በቀላሉ በመቆጣጠር ስለሚረዳቸው ነው፡፡

      ሳንታሪያ በየጎጡ ስለሚገነባ በአንድ ቀበሌ ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰሩ በርካታ ሳንታሪያዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከአንድ ጎጥ ወንጀል በግልም ይሁን በቡድን ፈጽመው የሚወጡ ወሮበሎች ሲመጡ ከአንዱ ሳንታሪያ ጠባቂዎች ጋር መገናኘት ግድ ነው፡፡ ከአንዱ ሳንታሪያ አምልጠው በሌላ አቅጣጫ እንዳያፈተልኩ የሚጠብቃቸው ሌላ ሳንታሪያ ስላለ ሳይወዱ በግድ በሳንታሪያ ጠባቂዎች ቀለበት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በደመነፍስ እግሬ አውጪኝ ሩጫ ቢጀምሩ እንኳን ቀድመው ያገኙዋቸው ጠባቂዎች "ቆሞራ ቃጣ! ጋርሣራ ቃጣ!" (Qommoora Qaxxan Garssaara qaxxaa) እያሉ ከፍ ባለ ድምጽ ይጮሃሉ፡፡ ትርጓሜው ከላይም ከታችም ያላችሁ መንገዱን ቶሎ ዝጉ! የሚል አስቸኳይ ጥሪና መልዕክት ነው፡፡ ይህ ድምጽ እንደተሰማ በየጎጡ ያሉ የሳንታሪያ ጠባቂዎች በየመስመራቸው በተጠንቀቅ ይቆማሉ፡፡ ሕብረተሰቡም ቀን ይሁን ሌሊት ከሳንታሪያ አከባቢ እንዲህ ዓይነቱን የጩኸት ድምጽ እንደሰማ በየቤቱ ይወጣና የመንገዶችን መግቢያ መውጫ በመያዝ ወንጀለኞችን መፈናፈኛ ያሳጣል፡፡ ወንጀለኞቹም  በቁጥጥር ሥር ይውላሉ፡፡

      እነዚህን ወንጀለኞች የየጎጡ ሳንታሪያ ጠባቂዎች ለየጎጡ ቡድን መሪ ያስረክባሉ፡፡ የቡድን መሪው ከተጠናቀረ መረጃ ጋር በወቅቱ ለነበረው የአከባቢው አስተዳደር ያቀርባል፡፡ የአከባቢው አስተዳደርም የወንጀሉን ሁኔታ አመዛዝኖ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ነባሩ  የወላይታ ባህላዊ ወንጀልን በጋራ የመከላከል ሥርዓት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይበልጥ ተጠናክሮ በተደራጀ መልኩ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡

      የሳንታሪያ ጥበቃ ጥብቅ የሆነ ደንብ አለው፡፡ ቀንም ሆነ ማታ የሳንታሪያ ጥበቃ በፍጹም አይቋረጥም፡፡ ቀን ቀን ሁለት ተረኞች ሲመደቡ ማታ ማታ ከሁለት አስከ ስድስት የሚሆኑ ተረኞች ይመደባሉ፡፡ የጥበቃ ተራ ድልድል በቡድን መሪው የሚወጣ ሲሆን ጥብቅ ቁጥጥርም ይደረግበታል፡፡ በአንድ ጎጥ ነዋሪ የሆነ አባወራ በሙሉ ተራ ይደርሰዋል፡፡ አባወራው በሕመም ወይም በእርጅና ተራውን መጠበቅ ባይችል ከቤቱ ዘኪ ልጅ ወይ ዘመድ ይሰጣል እንጂ አይታለፍም፡፡ ከአቅም በላይ እክል ያጋጠመው ሰው ከመግቢያው ሰዓት ቀድሞ ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አለበቂ ምክንያት ተራውን ያልጠበቀ ሰው በሕዝብ እጅግ ይወገዛል፡፡ ለወሮበላ አሳልፎ እንደሰጣቸው ስለሚቆጠር ባወጡት የጋራ ደንብ ይቀጣል እንጂ በዋዛ አይቀርም፡፡

      ተራኛ ጠባቂዎች የተራ ልውውጥ ሲያደርጉ አስረካቢዎች ልዩነታቸው ሲቀርብ
"ያዳ ገላ! ያዳ ገላ!" (Yaada gelaa, yaada gelaa) እያሉ ከፍ ባለ ድምጽ ጅራፍ የሚያስጮሁ ሲሆን ትርጉሙም ና ግባ! ና ግባ! ብሎ እንደ መጣራት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጥሩንባ ድምጽ አንዳንድ ቦታ በደወል መጠቀም ተተክቷል፡፡ ተረካቢ ተረኞችም የመግቢያ ሰዓታቸውን ወይም ጦር፣ ጎራዴ፣ ዱላ የመሳሰሉትን በመያዝ እገሰገሱ ደርሰው ይተኩከቸዋል፡፡

      በአጭሩ የወላይታ ብሔር የሳንታሪያ ሥርዓት ወንጀልን ከመከላከል አንጻር ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት በሕዝቡ ውስጥ እየሰረጸ ጠንካራ መሰረት ይዟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገር ደረጃ የተጀመረው "ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ" በይዘቱም በዓላማውም ከሳንታሪያ ጋር በእጅጉ ስለሚመሳሰል ከቀድሞ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ነባር የወላይታ ወንጀል በጋራ የመከላከል ባህል ተጠብቆ ለቀጣዩም ትውልድ ቢተላለፍ፣ ከዚህም አልፎ ወደሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ቢሰፋ የሚያስገኘው ጠቀሜታ እጅግ ከፍተና መሁኑንም ለመጠቆም እንወዳለን፡፡