• Call Us
  • +251465512106

ባህላዊ  የቤት ዓይነቶች በወላይታ

      ሰዎች ከአራዊትና ከተለያዩ አደጋዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ የግላቸው የሆነ የተከለለ ቦታ ወይም ማረፊያ ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ ስለሆነም ሰው ከጥንት ዋሻ ውስጥ ኑሮ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የራሱ ወይም የግሉ የሆነ መጠለያ በመሥራት መኖር እንደጀመረ ይታወቃል፡፡

      የወላይታ ብሔርም ለመኖሪያነት አቅሙ የፈቀደውን ዓይነት ጎጆ ቤት በመስራት ይኖራል፡፡ የዚህ ጎጆ ቤት አሰራርም በአራት ዓይነትና ደረጃ ተከፍሎ የሚታይ ይሆናል፡፡

  1. ዙፋ ኬታ          3. ጉላንታ ኬታ
  2. ሜሾ ኬታ         4. ቡራሬ ኬታ በመባል ይታወቃል፡፡
  1. ዙፋ ኬታ (Zuufa keettaa):- ይህ ቤት ውስጣዊ አሠራሩ በግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ነው፡፡ ከታች ከወለሉ ጀምሮ እስከ ላይ ጣሪያ ማዋቀሪያ ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ ይማገራል፡፡ ዙፋ ቤት በአብዛኛው የማገሩ ማሠሪያ ሀረግ ነው፡፡ ከውጭ ደግሞ የሰንበለጥ ክዳን አሠራ ከሌሎች ባህላዊ ቤቶች እምብዛም አይለይም፡፡ ይህ ቤት በጣም በጥራት የሚሠራ ስለሆነ ለረዥም ጊዜ ወይም አመታት የመቆየት አቅም አለው፡፡ በተጨማሪም እጅግ የሚያምርና ተመራጭ ነው፡፡
  2. ሜሹዋ (Meeshsho keettaa):- ይህ ቤት በውበትም ሆነ ጥራትና ጥንካሬ በሁለተኛ ደረጃ የሚመደብ የቤት ዓይነት ነው፡፡ አመጋገሩም ከታች እስከ ላይ ጣሪያ (kaaraa) ውቅር ድረስ ጥቅጥቅ ተደርጎ የሚሠራ ነው፡፡ ግድግዳው ደግሞ ከወፍራም ፍልጥ ወይም (Guganttaa) የሚባል ጠንካራ የበረሃ እንጨት እና ቀጫጭን ወራጅ (Pariyaa) የሚሠራ ነው፡፡ ይህ ቤት (hegaama kaaraa)በተባለ የጣሪያ ዓይነት የሚሠራ ሆኖ (meshuwaa keettaa) ውስጥ አመጋገሩ ሰንሰለታማ ዛጎል (maccamiyaa yelelluwaa) አስተሳሰር ስልት በመከተል ከላይ እስከ ታች መሬት ድረስ በቀጥታ መስመር ይወርዳል፡፡ ይህ ቤት እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ስለሚሠራ ውበቱ እጅግ ይማርካል፡፡
  3. ጉላንታ (Gulanttaa Keettaa):- ይህ ቤት ሶስተኛ ደረጃ የሚሰጠው ቤት ሆኖ ከውስጥ በኩል አመጋገሩ ከላይ እስከ ታች በዘጠኝ ዘር ያህል ክፍተት የሚሠራ ነው፡፡ እያንዳንዱ የ “ጉላንታ” መዋቅር በግምት ከሃያ እስከ ሃያ አምስት ዙር ያህል ጥቅጥቅ ያለ ማገር ይዞ ይወርዳል፡፡ ከየ “ጉላንታው” (Gulanttaa) መሀል በግምት አስራ አምስት ካ.ሜ ያህል ክፍተት ይኖረዋል፡፡ ከአንዱ (Gulanttaa) መዋቅር እና ከሌላው (Gulanttaa) መዋቅር መሀል (moggaa) የሚባል ከቀጫጭን የማገር እንጨቶችና ከነጭ ወፍቾ ተጠምጥሞ የሚሠራ ጌጥ ልክ እንደ አምባር ዙሪያውን ይታሰርለታል፡፡ የ (Gulanttaa) ቤት የውስጥ ማገር በእጅ ከሚገመድ ቃጫ ወይም ነጭ የእንሰት ወፍቾ ዛጎል (yelelluwaa) በሚባል የአስተሳስር ስልት ይታሠራል፡፡
  4. ቡራሪያ (Buraariyaa keettaa):- ይህ የጎጆ ቤት ዓይነት ደግሞ ማንኛውም አቅም የሌለውም አርሶ አደርም ቢሆን ሊሰራው የሚችለው የቤት ዓይነት ነው፡፡ ምክንያቱም በማንኛውም በተገኘ የግድግዳ እንጨት እና ወራጅ አጠና እንጨት እንዲሁም ደግሞ ከቀርከሃ፣ ከሸምበቆ፣ ከአገዳም እንጨት ጭምር ሊሰራ የሚችል ነው፡፡ የዚህ ቤት የውስጥ አመጋገሩ ከወለሉ እስከ ግድግዳው ጫፍ ድረስ በሸምበቆ ወይም በማሽላ አገዳ ወይም (Hamakkaa) ከሚባል ቀጫጭን ዛፋ ሸብ ሸብ ተደርጎ ይታሠራል፡፡ ከግድግዳው በላይ እስከጣሪያው ውቅር ድረስ ጭራሮ ተሰብስቦ እየተያዘ በሚታሰር (zanddidaa) ዘርዘር ተደርጎ ይታሠራል ወይም ይማገራል፡፡ የዚህን ዓይነት ቀለል ያለ ቤት ብዙ ውጣ ውረድ ሳይበዛ ለሥራው የተጠሩ ሰዎች በአንድ ቀን ሰርተው ለባለቤቱ አስረክበው መሄድ ይችላሉ፡፡

   ለሁሉም የጎጆ ቤት ዓይነቶች አይቀሬ የሆኑ ተግባሮች አሉ፡፡ እነርሱም፡-

  1. ቦታ መረታና ቅየሳ
  2. የጣሪያ ሥራ
  3. ምሶሶ ማቆም
  4. በር ወይም መቃን ማዋቀር
  5. የቤት ክዳን መሥራት እና
  6. የቤት ውስጥ ክፍፍል … ናቸው፡፡
  1. ቦታ መረጣና ቅየሳ፡- የወላይታ ባህላዊ ጎጆ ቤት እንደመሬት ክብ ነው፡፡ ቤቱን ለመሥራት የወሰነው ግለሰብም ራሱ ቦታውን መቀየስ ይችላል፡፡ ግድግዳው ክብ የሚቆም ሲሆን እምብርቱን በጠንካራ ችካል ይቸከላል፡፡ በችካሉ ላይ ሲባጎ ወይም ወፍቾ በማሰር በጫፉ ሾል ያለ ነገር አስሮ በመወጠር ዙሪያውን በጥንቃቄ ይጭራል፡፡ ይህ የችካሉ ቦታ የምሶሶ ማቆሚያ ቦታ ይሆናል ማለት ነው፡፡
  2. የጣሪያ ሥራ፡- ቤቱ ከሚሠራበታ ቦታ ፈቅ ብሎ ለጥ ያለ ቦታ ተመርጦ አራት ጠንካራ ባለባላ እንጨት ይተከልና በባላዎቹ ላይ አራት አግዳሚ እንጨቶች ተጋድመው በላዩ ላይ የጣሪያ ሥራ ይጀመራል፡፡ ማቶት (Shidhdha) የተባለ ዙሪያውን ክብ የሆነ መቀመጫ መሳይ ነገር ቀጠን ካለ (Hamakka) ከሚባል ጭራሮ እና ወፍቾ (sussaa) ይሠራል፡፡ የጣሪያ ሥራም ሶስት ክፍሎች አሉት፡፡ እነዚህም ሸልአና ጣሪያ እና ደንገርጢያ የሚባሉ ናቸው፡፡ ዋናው ጣሪያ ማቶት (Shidhdha) ዙሪያ ላይ ጀምሮ ከሃያ አስከ ሃያ ሁለት ዙር ድረስ ሊሠራ ይችላል፡፡ እንደቤቱ ስፋትና ጥበት ታይቶ የመጨረሻው ዙር ግን የሚዘጋው አምባር (mogaa) ነው፡፡  (Dangerexxiyaa)ው ከጣሪው በተወሰነ ርቀት በአምባር (mogaa) ተጀምሮ በግምት አስራ አንድ ዙር ያህል ይሰራና ያበቃል፡፡ እነዚህ ሥራዎች በህብረት ወደ ዋናው ሥራ ከመገባቱ አስቀድሞ በቤቱ ባለቤት እና በጥቂት ጎሬበቶች ሃይል በቅድሚ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ጎን ለጎንም ለዋናው ሥራ ለሚመጡ የደቦ አባላት የሚደረገው ዝግጅትም ይጧጧፋል ማለት ነው፡፡
  3. ምሶሶ ማቆም፡- የምሶሶው ቁመት በቤቱ ስፋትና ጥበት የሚወሰን ሆኖ በሚቆምበት ዕለት ተቆርጦ ይጋደማል፡፡ ለምሳሌ ለአስራ ሁለት ክንድ ቤት ምሶሶውም በልኩ ተለክቶ ይቆረጣል፡፡ ከወደ ግንዱ በኩል ወደመጨረሻ አከባቢ በጠገራ ይበሳል፡፡ በቀዳዳው እርጥብ ብሳና (mayillo) የሚባል ሀረግ ገብቶበት በተሰበሰቡ ሰዎች ሃይል መሬት ለመሬት እየተጎተተ ቤቱ ወደሚሠራበት ቦታ ይመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ታዳሚዎቹ

        ሆሆ ሆያ ሆ

       ሆሆ ሆያ ሆ

       ሀያ ማዳ ማድያጎ

       ሀያ ማዳ ጦሳው

   ትርጓሜው፡- አጋዡ አምላካችን ናና አግዘን… ሆ… ሆ.. እንደ ማለት ነው፡፡ እያሉ በቅብብል እያዜሙ ወደቦታው ይደርሳሉ፡፡ የአቅራቢያው ሴቶችም በሙሉ ወጥተው ከበሮ እየደለቁ እና እልልታውን እያቀለጡ ቀየውን በደስታ ያደምቃሉ፡፡ ወንዶች ወደ በሩ ጋ ሲደርሱ ከላይ የተባለውን ዜማ በመቀየር

       “ኬታዋይ ጋኮሆ…

       ኬታዋይ እማታይ ጋኮሆ…

    ትርጓሜው፡- እንግዳው ደርሶ የለም ወይ ባለቤቱ ደርሶ የለም ወይ? ማለት ነው… እየደጋገሙ እያሉ እያዜሙ በሴቶች እልልታና ከበሮ ድለቃ ታጅቦ ምሶሶው በበር ገብቶ በቀጥታ መስመር አልፎ ይጋደማል፡፡

      የምሶሶው ማቆሚያ ጉድጓድ ጥልቀቱ በግምት ሶስት ክንድ ያህል ይሆናል፡፡ ምሶሶው ከጫፍ ወደ ግንዱ ጋ ሶስት ክንድ ያህል ተለክቶ በመሮ ይበሳና በቀዳዳው የ “ምጫፍሌ” የሚባለው መሳቢያ ይሰካለታል፡፡ ሌላው የምሶሶው ጫፍ ተደበልብሎ ይጠረባል፡፡ ከዚያም ተጎትቶ ቀና ይልና ከጫፉ አቅጣጫ ይጋደማል፡፡ ቀጥሎም ጣሪያውን ለማምጣትና ምሶሶው ጫፍ ላ ለመሰካት ምሶሶውን ጎትቶ ያመጣው ሰው ሁሉ ወደዚያው ያቀናል፡፡ “ጦሳ ማዳ.. ሃያ ማዳ.. እያለ በሴቶች ከበሮ ድለቃና እልልታ አጃቢነት በጫፉ ላይ ጣሪያውን ይሰካና ሲመለከቱት የማይቻል የሚመስለውን የተሰበሰበው ደቦ ህብረቱን አጠናክሮ ሆሆ.. ሆያ ሆ.. እያለ ብድግ አድርጎ ያቆመዋል፡፡ የሴቶቹም እልልታ እንደገና ይቀልጣል፡፡

      በዚህ መልኩ ምሶሶው እንደቆመ ወራጅ አጠና (ዛሮ ዛፍያ) ከውጭ በኩል ዙሪያው ይተከልለታል፡፡ ከህዝቡ ወይም ደቦ መካከል ሙያተኛ ናቸው የተባሉት ሁለት ወይም አራት ሰዎች ጣሪያው ላይ ይወጡና ወራጅ አጠናውን መሬት ላይ የቆሙ ሰዎች በቆልማማ (Hingettaa) በተሰኘው እንጨት መያዣ እየሳቡላቸው ይዘው በጣሪያው ላይ በማሠር የወራጅ ሥራ ይጠናቀቃል፡፡

  1. በር ወይም መቃን ማዋቀር፡- ቤቱ የሚሠራበት ቦታ ድልደላ እና ግድግዳው የሚቆምበት ጉድጓድ ተቆፍሮ እንደተጠናቀቀ የደረቀ ቀይ ባህር ዛፍ፣ ወይራ ወይም የበረሃ እንጨት ተቆርጦ በግድግዳነት ዙሪያወን ይቆማል፡፡ እንጨቱ ቆሞ እንዳበቃ አፈር ይመለስበታል፡፡ ቀጥሎ ከላይ ከአናቱ በኋላ ተቆርጦ የሚወድቅ ዙሪያው ሶስት ዙር ማገር (kenaa meegaa) የሚባለው ይማገርበታል፡፡ መቀን (qoreyaa)፣ ጉበን (qosilettaa)፣ መቀሪቀሪያ (gordde mittaa)፣ እና መቆለፊያ (kolbbiyaa) ከጎጭላ ጋር ይያያዛል፡፡ መዝጊያው በር ደግሞ ሀማካ ከሚባል እንጨት ተጠላልፎ የሚሠራ በብሔሩ ቋንቋ “እፒታ” ይገባበታል፡፡
  2. የቤቱን ክዳን መስራት፡­- ቤቱ ተሰርቶ ለሣር ክዳን ሲዘጋጅ በመጀመሪያ ግምድ ሣር (Konddaa) ይዘጋጃል፡፡ ግምዱን ለመሥራት አራት አጠና ባህር ዛፍ እንጨት ይቆማል፡፡ ምርጥ የክዳን ሣር ተለቅሞ በውሃ እንዲርስ ይደረጋል፡፡ ከዚያም በፈለገው ያህል ጭብጥ እየተያዘ በቋሚ አጠና እየተጠመዘዘ እንዲያልፍ ይደረጋል፡፡ ከመሬት እስከ ግድግዳው ጫፍ ድረስ በግምት አስራ አንድ ዙር ያህል በክርክም ተከድኖ ሊያበቃ የቀረው ግን የሰንበለጡን ቂጥ ወደላይ በመገልበጥ በማገር እየታሰረ ቤቱ አናት ድረስ በመዝለቅ ይጠናቀቃል፡፡ ቤቱ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ጉልላት (Gumbuwaa) የሚባለው ነገር በምሶሶው አናት ላይ ይደረጋል፤ ከጉልላቱ በታች  Woyzariyaa ወይም Dashetaa የተባለው የሣር ክዳን አደራረግ ይደረግለታል፡፡ ይህ Woyzariyaa ወይም Dashetaa በግምት ከዘጠኝ እስከ አስራ አንድ ዙር ያህል የሚሸፍን ሲሆን ጥቅሙም የቤቱ ክዳን ሲያረጅና ሳይረግፍ እንዲሰነብት ስለሚያደርግ ነው፡፡ ምክንያቱም ሣር ቤት ላይ ዝናብ በዘነበ ጊዜ የሚያርፈው ከአናቱ ስለሆነ ነው፡፡
  3. የቤቱ የውስጥ ክፍሎች ክፍፍል ሥራ፡- ባህላዊ ሣር ቤት ውጫዊ አሠራሩ ከተጠናቀቀ በኋላ የውስጥ ክፍፍል ሥራ ይጀመራል፡፡ በቤቱ ውስጥ ሳሎን (wuyigiiyaa) እና ጓዳ (qoli’uwaa) ለመለየት የሚሆን “ቁሩጡዋ” የሚባል ከማሽላ አገዳ ወይም ሸምበቆ ተሰርቶ ከምሶሶ አከባቢ ጀምሮ እስከ ግድግዳው ድረስ የሚቆም ከለላ ይሰራል፡፡ ሌላው ጋጣ (Gaxaattaa) የፈረስ ማደሪያ፣ የከብት ማደሪያ (Zazaluwaa) እና ከፍ ብሎ ደግሞ የእህል መከመሪያ (shakkuwaa) ይሠራለታል፡፡

በአጠቃላይ የወላይታ ባህላዊ ጎጆ ቤት በውስጥ አወቃቀሩ፣ በስፋት ጥበቱ፣ በዘመን ተሸጋርነቱ፣ ለመሥራት በሚፈጀው ጊዜና ቁሳቁስ ዓይነት በአጠቃላይ በጥርት ደረጃው በአራት ተከፍሎ ይታይ እንጂ የሚያመሳስለው እና ለሁሉም አይቀሬ የሆኑ ነገሮች እንዳሉት መታወቅ አለበት፣ ለምሳሌ የምሶሶ አቋቋም የግድግዳና የቢሮ ወይም መቃን አወቃቀር፣ የጣሪያ ሥራና የውስጥ ክፍፍል ወዘተ… ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የአሰራሩ ስልቱ ይለያይ አንጂ አራቱም ዓይነት ቤቶች ተመሳሳይ ደረጃዎችን ያልፋሉ፡፡

ለአራቱም የጎጆ የቤት ዓይነቶች ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ከዝግጅቶቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ ምሶሶ፣ ወራጅ፣ ሰንበለጥ፣ ወፍቾ… ወዘተ ቁሳቁሶችን መሰብሰብ የግድ ይሆናል፡፡

ማንኛውም ዓይነት ቤት ሲሰራ ለምሶሶ የሚሆነው ግንድ በቅድሚያ ተጠንቶ ሳይቆረጥ ይቆያል፡፡ ቤቱ ምሶሶ እንዲቆምለት ከተዘጋጀ በኋላ ግን የደቦ (Daguwaa) ህብረት ምሶሶው ቆርጦ ሳይውል ሳይድር ዕለቱኑ እንዲቆም ያደርጋል፡፡ ይኸም የሚሆነው ምሶሶው ከዋለና ካደረ ውሻ  ወይም ሌላ ጸያፍ እንስሳ በላዩ ላይ ቢያልፍ ቅስፈት ያመጣ የሚል እምነት ስላለ ነው፡፡ ለምሶሶነት የሚመረጡ የእንጨት ዓይነቶች ዋንዛ (moqqottaa)፣ ዶቅማ (ochchaa)፣ ግራር (odooruwaa)ና ብርብራ (ዛጊያ) ወዘተ ናቸው፡፡

እነዚህ የእንጨት ዓይነቶች በጣም ጠንካራ እና በሚሰጥ የማይደፈሩ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባህር ዛፍም ለምሶሶነት ተስማሚ (shaaga) ተብሎመከበር እንደተጀመረ ይታወቃል፡፡

ከደጃፉ ላይ የጥራጥሬ ማስቀመጫ ጎተራ፣ ከጓሮ ደግሞ በእንሰትና በተለያዩ ተክሎች የታጀበ ውብ የወላይታ ጎጆ ቤት በዚህ መልክ ተሰርቶ ይጠናቀቃል፡፡

ማጠቃለያ

      የወላይታ ጎጆ ቤቶች ለመኖሪያ ምቹ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ባህሉን ከማጉላትም ከማስተዋወቅም አንጻር ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ሆነው ሳለ በአሁኑ ጊዜ በሰዎች አስተሳሰብና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ተጽእኖ በቆርቆሮ ቤቶች አየተተኩና እየጠፉ ስለሆነም በአንዳንድ አከባቢዎች የሚገኙ ባህላዊ ቤቶችን የብሔሩ ተወላጆችም ሆነ ለባህሉ ተቆርቋር የሆኑ ግለሰቦች ትኩረት ሰጥተው ለታሪክ እንዲቆዩ ለማድረግ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ መልካም ነው እንላለን፡