• Call Us
  • +251465512106

የተጸውኦ ስም አወጣጥ በወላይታ

የሰው ልጅ በዕለት ተዕለት ኑሮው ለሚጠቀምባቸው ቁሳቁስ፣ ለእንስሳት፣ ለዕጽዋት፣ ለሰዎች ለቦታዎች ወዘተ… ስያሜን ይሰጣል፡፡ ይህም አንድን ነገር ከሌላው ለመለየት፣ ሀዘኑንና ደስታውን፣ ድሉንና ሽንፈቱን ለመግለጽ በስያሜዎች ይጠቀማል፡፡ ጥንት ሀሳብን በጽሁፍ መግለጽ ባልተለመደበት ጊዜ አንድ ማሕበረሰብ ባህሉን፣ ወጉን፣ እምነቱንና ታሪኩን በቦታ እና በሚወልዷቸው ልጆች ስም አማካኝነት ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ልጅ ከወለዱ በኋላ ለልጃቸው ስም ለመስጠት የተለያዩ አጋጣሚዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህም የተለያዩ ወቅቶች፡- የጦርነት፣ የደስታ፣ የሐዘን፣ የጥጋብ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች መለኮታዊ አስተሳሰቦች እና የጀግንነት ሁኔታዎች በተለምዶ የሚታዩ ዋና ዋና ከስም አወጣጥ ጋር የሚቆራኙ ናቸው፡፡

      በወላይታ ባህል፣ ለሚወለደው ልጅ ስያሜ መስጠት እንደ ሌላው የዓለም ሕዝብ የተለመደና የራሱ የሆነ የብሔሩ ባህላዊ የስም አወጣጥ ያለው ሲሆን በባህሉ መሠረት ሰዎች የወለዷቸውን ሕፃናት ሲሰይሙ ከሁኔታዎች ጋር እያቆራኙ እንደሚሰይሙ እንመለከታለን፡፡

የአሠያየም ሥርዓት

1. የመጀመሪያ ሆሄያትን በማመሣሰል መሠየም

      በወላይታ ሕዝብ ዘንድ አንድ ሰው ሲጠራም ሆነ ስሙ ሲጻፍ የአባትን ስም አስቀድሞ ነው፡፡ ይህ የአሰያየም ሂደት በራሱ ደግሞ ሌላ የአጠራር ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡ በዚሁ የአሰያየም ሁኔታ የልጁ እና የአባቱ ስም የመጀመሪያ ሆሄያት ተመሣሳይ የሚሆኑበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ፡- የአባትዬው ስም ጋንታ (Gantta) ከሆነ የልጁ ስም ጋጋ (Gaagga) ወይንም (Gallaso) ጋላሶ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አጠራሩም (Gantta Gaaga) ተብሎ ነው፡፡

ለአብነት የተወሰነውን እንመልከት

ጾታ

የአያት ስም

የአባት ስም

የልጅ ስም

ወንድ፡

መዳልቾ     

መና

ማንዳዬ

Madalchcho

Mana

Mandoye

ሴት፡- 

ዎዳጆ 

ዎጋሶ 

ዎይዛሬ

Wodaajo

Wogaaso   

Woyizaree

ከላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያ ፊደላት መመሳሰል በአባት ብቻ የሚታይ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜ ለእናት ስምም አስመስሎ የመሰየም ባህሉ ይዘወትራል፡፡

የተወለደበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ የመሰየም ሁኔታ

     አንድ ሕጻን ሲወለድ ስም ለመሰየም የወላይታ ሕዝብ ብዙም የስም ፍለጋ ወዲህ ወዲያ አይልም፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ አጋጣሚዎች ለወላጆቿ ትውስታ አላቸውና በሁኔታዎች ተደግፈው የመሰየም ባህል አሏቸው፡፡ በዚሁ የተወለደበትን(ችበትን) የቀኑን ስም እንደዋቢ አድርገው የመሰየም ሁኔታ በአብዛኛው ይስተዋላል፡፡ ይህም ከሰኞ እስከ እሁድ ያሉትን የሳምንት ቀናት በወላይታ የየራሳቸው ስም ስላላቸው ስም ለመሰየም አይቸግራቸውም፡፡ ይህንንም በሚከተለው ምሳሌ እንመለከታለን፡፡

 

 

ተ.ቁ

የዕለቱ ስም

ስሞች

ለወንድ

ለሴት

1

እሁድ woggaa

Woggaa(ወጋ)Wogaaso (ወጋሶ)

Woggaree(ወጋሬ), Ayyaanee (አያኔ)

2

ሰኞ Saynno Shagga

Saynno(ሰኞ),Borooda (ቦሮዳ)

Saynne (ሳይኔ)

3

ማክሰኞ Ciishshaa

Ciishshaa (ጭሻ)

Ciishshee (ጭሼ)

4

ረቡዕ Wollila

Tufaa(ቱፋ),Oroobaa (ኦሮባ)

 

5

ሐሙስ Shaaga

Anjjaa(አንጃ),Shaagaa (ሻጋ)

Shaagee(ሻጌ), Anjjoore(አንጆሬ)

6

ዓርብ Bizza

Tuqaa(ቱቃ) Arbaa(ዓርባ)

Arbbee (አርቤ)

7

ቅዳሜ Qeeraa

Giyaa (ጊያ)

 

 

  1. አንድ ሕጻን የተወለደበትን ጊዜ (ከቀኑ ውስጥ) በማገናዘብ መሰዬም

አንድ ሕፃን ሲወለድ የተወለደበት ጊዜ በዕለቱ ጥዋት፣ እኩለ ቀን፣ ከሰዓት ማታ ወይም እኩለ ሌሊት ቢሆን ይህንን ጊዜ በማስመልከት የመሰየም ባህል አለ፡፡ ይህም በሚቀጥለው ምሳሌ ተቀምጧል፡፡

ተ.ቁ

የተወለደበት ጊዜ

ስያሜዎች

ለወንድ

ለሴት

1

ጠዋት

Wontta(ዎንታ), Bakkaalo(ባካሎ) Dolaa(ዶላ)

ማላዶ(Maalladee)

2

እኩለ ቀን

Seeta(ሴታ) Gallasso(ጋላሶ)

ካዎቴ (kawotee)

3

ከሰዓት በኋላ

ላንኮ(Lankoo) ላንካ (Lankkaa)

ላንካሬ (Lankaree)

 

  1. የተወለዱበትን ወቅት አገናዝቦ መሰየም

ሌላው በወላይታ ሕዝብ ዘንድ የተለመደው በባህሉ አንድ ሕጻን ሲወለድ ከተወለደበት ወቅት ጋር በማገናዘብ የህጻኑን ስም የመሰየም ሁኔታ ነው፡፡ በአመት ውስጥ ያሉ አራት ወቅቶችን በማገናዘብ ነው ይህን የሚያደርጉት፡፡ አንድ ሕጻን ከእነዚህ መካከል በአንደኛው ጊዜ ቢወለድ ከዚያው ከተወለደበት ወቅትና ሁኔታ ጋር በማገናዘብ የመጠሪያ ስም ያወጡለታል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚሠየሙ ስሞችን በከፊል አንመልከት፡፡

 

ተ.ቁ

የተወለደበት ጊዜ

ስያሜዎች

ለወንድ

ለሴት

1

በልግ (Badhdheesa)

Badhdheeso, ባዴሶ Saphpheero (ሳጶ)

Badhdheere(ባዴሳ), Dubbee(ዱቤ)

2

ክረምት Balgguwa

Iroo(እሮ), Caree(ጫሬ), Balggoo(ባልጎ), Shaara(ሻራ)

Iree(ኢሬ), Calalee(ጫላሌ), Gubbanee(ጉባኔ)

3

በጋ Boniyaa

Gombillo, Bonaa

Bonee (ቦኔ)

4

ፀደይ Ofinttaa

Illilloo(እልሎ), Pinttaa(ፕንታ), Booqalsoo(ቦቃልሶ)

Booqalssee(ቦቃልሶ), Illilee(እልሌ)

 

5.ከዘመኑ ክስተትና ሁኔታ ጋር በማገናዘብ መሰዬም

     በማህበረሰቡ ዘንድ የተለመደውና ከሁኔታዎችና ከወቅቱ ክስተት ጋር አገናዝቦ የመሰየሙ ሁኔታ ለህዝቡ ልዩ ትኩረትና በሕይወታቸው ደግሞ እንደ አንድ ትውስታ ፈጥረው የሚያልፉ ክስተቶችን በማካተት ይሰይማሉ፡፡ ይህም አንድ ሕጻን በሚወለድበት ዘመን ጠቅላላ በዓመቱ ውስጥ ወይም ጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከሰቱትን ጉልህ ክስተቶች፣ ያሉና የሆኑ ሁኔታዎችን ከልጁ ውልደት ጋር በማገናዘብ በዘመኑ ጥጋብ፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ መኣት፣ ምርት፣ ዝናብ፣ መብረቅ፣ ድርቅ፣ ወዘተ… የመሳሰሉት ሁኔታዎች ጎልተው ከታዩ እነዚህን ከሕጻኑ ልደት ጋር በማገናኘት ስም ያወጡለታል፡፡ በተጨማሪም በዚያን ዓመት ውስት የተፈጠሩ የቤተሰብ ወይም የቅርብ ዘመድ ጥል፣ ዕርቅ፣ መለያየት፣ ሹመት፣ ሞት ወዘተ የመሳሰሉ ሁኔታዎች ከተከሰቱ ከተወለደው ሕጻን ጋር በማገናኘት ይሰይማሉ፡፡

ተ.ቁ

ክስተቶች

ስያሜዎች

ለወንድ

ለሴት

1

ጥጋብ (ምቾት) (kaluwaa)

Ishaloo(እሻሎ), Ayyaanoo(አያኖ)  konaaso(ኮናሶ), ushachcho(ኡሻቾ)

Mannanee(ማናኔ), Ishalee(እሻሌ)

Bala’’anne(ባልኣኔ), Kumetee(ኩሜቴ)

2

የምርት ጊዜን በማስመልከት የሚሰየሙት

Dorannaa(ዶራኖ), kumaa(ኩማ), Baraata(ባራታ)

Murutee(ሙሩቴ), Doraannee(ዶራኔ)

Kumetee(ኩሜቴ), Hiraysee(ህራይሴ)

3

ዝናብ (መብረቅ) ወጨፎ

Iroo(እሮ), Zullaa(ዙላ), Wolqqantta(ዎልቃንቶ)

Iree(እሬ),

4

ጦርነት

Baassaa(ባሳ), Tooruu(ቶሩ), Minotaa(ምኖታ), Qolchcha(ቆልቻ), Baabisoo(ባብሶ), Kombaaso(ኮምባሶ)

Minotee (ምኖቴ)

 

 

 

 

እነዚህንና ሌሎች ስሞች የሚሰጡ ሲሆን በዚህ መሠረት የሚሰየሙበት ምክንያትም በወቅቱ የተከሰቱትን ክስተት ክፉም ሆነ ደግ ለማስታወስ ነው፡፡

  1. በዓመታዊ በዓላት ወቅቱ ለሚወለዱ ልጆች የሚወጡ ስሞች

በወላይታ ባህላዊ፣ ህዝባዊ ወይንም ሃይማኖታዊ በዓል በሚከበርበት ወይም ዕለቱ በተቃረበበት ወቅት ሕጻን ሲወለድ በበዓሉ ስም የሚጠራበት አሊያም ተዛማጅ በሆኑ ስሞች ይጠራል፡፡ ቀጥለው የቀረቡ ምሳሌዎች ይህን እውነታ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

    • በወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል (Gifaataa) ወቅት ለሚወለድ ወንድ ሙናሳ(Munaasa)፣  ማስቃላ(masqallee)፣ ለሴት ደግሞ ግፋቴ(Gefaate)፣ ባሎቴ(Balote)፣ ማስቃሌ(Masqalee) በመባል ይታወቃል፡፡
    • ሌሎች ህዝባዊ በዓላት ባሉበት ወቅት ደግሞ ለወንድ AYaano (አያኖ) ለሴት Ayaanee (አያኔ) የሚል ስያሜ ይሰጣል፡፡
  1. የሕጻናት ሞት አከታትሎ በደረሰበት ቤተዘመድ የተለመደ አሰያየም

በጥንት ዘመንም ሆነ በአሁኑ በቅርብ ርቀት ባሰለፍናቸው ዘመናት አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ የተወለዱ ህፃናት በተደጋጋሚ የሚጠራበት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደተወለደ ሲሞት ሌላ ጊዜ ደግሞ በተወለደ በጥቂት ወራት ወይም ዓመታት ውስጥ ገና በህጻንነቱ ይቀጫል፡፡ በዚህ ሁኔታ በተከታታይ የሚወለዱ ህፃናት ሁሉ በሞት ሲነጠቁባቸው ጭንቅ የገባቸው ወላጆች ማምለጫ ፍለጋ ይጀምራሉ፡፡ ለዚህም እንደ ስልት የሚወስዱት ሞት ትቷቸው እንዲያልፍ ለልጆቻቸው የማይረባ፣ የስድብ እና የሚያቋሽሽ ስም በባህሉ ለጊዜውና ቢሆን ሞት የሚፀየፋቸው ስሞች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከእነዚሀ ስሞችም ለአብነት ፡-

ለወንድ፡- Curqqo(ጩርቆ), Darccoo(ዳርጮ), Obbollee(ኦቦሌ) Borkko(ቦርኮ), Manaa(ማና)

ለሴት፡- Sharfee(ሻራፌ), Cinashee(ጭናሾ), Muucee(ሙጨ) Kutushee(ኩቱሸ), Dorsee (ዶርሰ)

በማለት ሞት ለጊዜውም ጊሆን እንዲጸየፋቸው ብለው ይሰይሟቸዋል፡፡

  1. ውበትን (ደምግባትን በማገናዘብ መሰየም

ውበትን፣ ደምግባትንና  ቁንጅናን በማስመልከት ይሰይማሉ፡፡ ቆንጆ እና መልከ መልካም ከሆነ(ከሆነች) ይህንን በማስመሰል የሚሰጥ ስም ነው፡፡ ይህንን በሚቀጥለው ምሳሌ እናያለን፡፡

ለወንድ፡- Henjjeero(ሔንጀሮ), Diidoo(ዲዶ), Alleeqo(አለቆ) Bakaalo(ባካሉ), Malsaamo(ማልሳሞ)…

ለሴት፡- Malanchee(ማላንቸ ቆንጅት), Littishe(ልትሼ), Suufare(ሱፋሬ) Walqqasa(ዋልቃሴ), Alleqe(አለቄ) Sildidde(ስልድደ)…

እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ቁንጅናን የሚገልጹ ስሞች ይሰየማሉ፡፡

  1. ከብዙ ቆይታ በኋላ ለተወለዱ ልጆች የሚሰጡ ስሞች

በወላይታ ህዝብ ዘንድ አንዳንድ ጊዜ ሳይወለድ በሚዘገይበት ጊዜ በስለት ወይም በአከባቢው ቋንቋ (shiiqqetaan) ለሚወለዱ ህጻናት እንደሚከተለው ስም ይወጣላቸዋል፡፡

ለወንድ፡- Gam’’a, yaanaa, Anjjulloo, Ukkumoo, Go’’aa…

ለሴት፡- Anjjullee, Ukkumee, Laamotee, Imotee, Go’’itee…

በማለት እነዚህ ልጆች በስጦታ፣ በካሳ መልክ ከፈጣሪ ዘንድ እንደተሰጡ በመቁጠር ስያሜውን ይሰይማሉ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው እና ሌሎች ያልተጠቀሱ ለምሳሌ ከዝነኛ ስሞች ጋር በማመሳሰል ልጆቻቸው የእነዚያ ስሞች እድል ዓይነት እንዲገጥሟቸው በማለት የሚሰይሙበት፣ ከጠንካራ እና ጉልበታም በሆኑ አራዊት ስም የመሰየም እና ሌሎችም ባህላዊ የሆኑ የስም አሰያየም ሁኔታም በአሁኑ ወቅት እየቀረ እና ተተክቶ እናገኘዋን፡፡ በተለይም ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ከመጡ ፖለቲካዊ አስተዳደር ዘይቤዎች ከሃይማኖት እና ከዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ተጽእኖ ይሰተዋላልና፡፡ ባህሉ በዚሁ መሰረት ተጠንቶ መቀመጡ ለቀጣይ ትውልድ ባህሉን ለማስተላለፍ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡

ምንጭ፡-

  • የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲስ አበባ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት 1980 ዓ.ም
  • የጋብቻ የልደትና የለቅሶ ባህል በሰሜን ኦሞ ዞን በሰሜን ኦሞ ዞን ባህልና ማስታወቂያ መምሪያ (1990) አዲስ አበባ
  • The new Encyclopedia Britannica Vol. 8 15thed The university of Chicago 1995
  • Wogaa: የሰሜን ኦሞ ዞን ባህልና ማስታወቂያ መምሪያ ዓመታዊ መጽሔት (1990 ዓ.ም)