• Call Us
  • +251465512106

የወላይታ ስርወ መንግሥታት

የወላይታ ስያሜ መነሻ

የአንድ አከባቢና ሕዝብ ስያሜ የራሱ የሆነ መነሻ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ የአንድን አከባቢና ሕዝብ ትክክለኛ ስያሜ ለማግኘት ፀሐፊዎች ብዙ ጊዜ ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱም የእነዚህ ስያሜዎች መነሻ የሚሆኑ ክስተቶች በጊዜ ርቀት የተፈጸሙ በመሆናቸውና የጽሑፍ መረጃዎች ብዙን ጊዜ የማይገኙ ስለሆነ የአብዛኛዎቹ የአከባቢ ስያሜዎች  ትርጉም በአፈ-ታሪክ መረጃ የሚንተራሱ ይሆናሉ፡፡ የአፈ-ታሪክ መረጃዎች ደግሞ በረዥም ጊዜ ቆይታ በባህሪያቸው የመጨመር ወይም የመቀነስ አልያም ከታሪካዊ መነሻው ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸው ሆነው ሊገኙ ስለሚችሉ በዚህ ጉዳይ የጠራ መረጃ ለማግኘት የሚደረገው ጉዞ አድካሚና አሰልቺ ሊሆን ይችላል፡፡ ወላይታ በሚለው ስም ላይ ብዙ ፀሐፊዎች የተለያየ ስያሜና ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ 

ጥንት ለወላይታ ወጥ የሆነ የአካባቢው ስያሜ ባልነበረበት ዘመን ከአንድ በላይ ስሞች እንደነበሩት አንዳንድ የአፈ ታሪክና የተፃፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም መሠረት አካባቢው በአንድ ወቅት ወላይታ በማለት ፋንታ አሩጂያም ተብሎ እንደተጠራ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን አካባቢው በዚህ ስያሜ ይጠራ በነበረበት ወቅት ከተከሰተው ማህበራዊ እና ተፈጥሯዊ ሁኔታ በመነሳትአገራችን በአሩጂያ አገዛዝ ወቅት የሕዝቡ ቁጥር ቀነሰ፤ወራሪዎች አጠቁን በዚህ ስም መጠራት ከጀመርንበት ጊዜ ወዲህ አካባቢያችን በድርቀና በረሃብ ተመታ የጥንቱ ስማችን ይሻለናልበማለት ሕዝቡ እንዳስመለሰ አይሻ አማዶና ሌሎችም ጽፈዋል፡፡ ሌላው ደግሞ በወላይታ ሕዝብ ታሪክ ወላይታ ማላ ተብሎ የሚጠራ ጎሳ የወላይታ ስያሜ መነሻ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ይህ ጎሳ በጥንት ጊዜ ማለትም ሰዎች በዋሻ ውስጥ ይኖሩበት በነበረ ዘመን ኪንዶ ዲዳዬ ተራሮች በዋሻ ውስጥ ፍራፍሬ በመልቀምና እንስሳትን በማደን የሚኖር ሆኖ ሳለ ሰዎች ከዋሻ ወጥተው ጎጆ ቀልሰው  መኖር በነበሩበት ዘመን በሌሎች ላይ የመንገስ ዕድል ያገኘ ጎሳ ሲሆን የወላይታ ስያሜ ከዚህ ጎሳ ስያሜ እንደመጣ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የጎሳው የመጀመሪያ ንጉስ የሆኑት ካዎ ቢቶም ስማቸው የተወሰደው ጎሳው በምድር ዋሻ ውስጥ ከመኖሩ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፤ ምክንያቱምቢቶማለት መሬት(አፈር) እንደ ማለት ነው፡፡ የወላይታ መንግስታዊ አስተዳዳርም በዚህ ጎሳ እንደተጀመረ ይታመናል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወላይታ የሚለው ቃል የአከባቢውም ሆነ የሕዝቡ ስያሜ እንደነበር በርካታ የአፈ-ታሪክ እና የጽሁፍ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡

አሩጂያ የሚባለው ጎሳም ስልጣኑን ከወላይታ ማላ ዘረ-ግንድ ነገስታት ቀጥሎ የተረከበ ሲሆን በእነሱ ዘመን ሕዝቡም ሆነ አገሩ በስማቸው እንዲጠራ ሞክረው እንደነበር ይነገራል፡፡ ከአሩጅያ በኋላ ዳግመኛ በመጣው በሁለተኛው የወላይታ ማላም ዘረግንድ ነገስታትም ሆነ በወላይታ ዘረ-ግንድ ነገስታት ዘመን ሕዝቡም ሆነ አገሩ ወላይታ ይባል እንደነበር የተለያዩ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡  

በአሁኑ ጊዜ ወላይታ ብለን የምንጠራው ሕዝብና አከባቢ በታሪክ አሩጂያ፣ወላይታ፣ዳሞታ እየተባለ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አካባቢውና ሕዝቡ ወላይታን በማይወክል በሌላ ስም ከአፄ ምንሊክ ወረራ እስከ ደርግ መንግስት ድረስ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎች ይህ ስያሜ ከምንሊክ ወረራ በፊትም እንደነበረ የሚገልጹ ቢኖሩም የሕዝቡ አፈ ታሪክና አብዛኛዎቹ የጽሁፍ መረጃዎች  እንደሚገልጹት ስያሜው ከምንሊክ ወረራ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ነው፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚገለጸው የአጼ ምኒልክ ሠራዊት ወላይታን ለማስገበር በመጣበት ጊዜ የካዎ ጦና ሠራዊት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀውን የምኒልክን ሠራዊት ለመግጠም በፈረስ ሆኖ ሲመጣ አይቶ ምኒልክ ጦርና ጋሻ ይዛችሁ ጠብመንጃ ለመግጠም ትመጣላችሁ?” ብሎ በመገረም ከተናገሩት የስድብ ቃል እያደረ የምንሊክ አስገባሪዎች ወላይታ የሚለውን መጠሪያ በመተው ሌላ መጠሪያ እንዲኖረው አድርገዋል፡፡

ከታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው በምኒልክ ጦርነት ወቅት በሕዝቡ ላይ ከደረሰው ሰብዓዊና ሞራላዊ ኪሳራ በተጨማሪ ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ስርዓቱ በተከተለው ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና ምክንያት ከስያሜው ጀምሮ ያሉ የብሔሩ ማንነት መገለጫዎች ተቀይረዋል ወይም በአብዛኛው ጠፍተዋል፡፡ በመሆኑም ለብሔሩ ከስያሜው ውጪ ማንነቱንና ክብሩን የማይወክል  ሌላ ስያሜ አንደተሰጠው ብዙዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ዋናው ፍሬ ሃሳብ ግን ወላይታ የሚለው ስያሜ ጥንትም ሆነ አሁን የአካባቢውን ስያሜ የሚወክል መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የወላይታ ሕዝብ አንድም ጊዜ ከዚህ ውጪ በሆነ ስም ተጠቅሞም ሆነ ራሱንም በሌላ ስም ጠርቶ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ሌላ የትኛውም ስያሜ ከምኒልክና ከምኒልክ አስገባሪዎች ለወላይታ ሕዝብ ሥርዓቱ አምጥቶ የለጠፈው ስም እንጂ የወላይታ ትክክለኛ መጠሪያ አይደለም፡፡

በተጨማሪም የወላይታ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ራሱን የሚያውቀው ወላይታ በመሆኑና መጠሪያ ስሙም ወላይታ መሆኑን ነው፡፡ ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት በሕዝቡ ላይ ተጭኖ በነበረው ጭቆና ምክንያት ለብሔሩ ያለስሙ የበታችነት፣የማሸማቀቅ የስድብና የውርደት ስም ተሰጥቶት ሌላው ኢትዮጵያዊ ይህንን ስም የበታችነትና የስድብ መገለጫ አድርጎት እንዲቀበል ያደረገው የሥርዓቱ ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም ብሔሩ የሚታወቅበትን ጀግንነት፣ሥራ ወዳድነት፣አኩሪ ታሪክና ጥንካሬው ተሸፍኖ ሌላው ሕብረተሰብ በሌላ ማንነት እንዲረዳው ተደርጓል፡፡(ምንጭ፡አዳነ አይዛ፡፡ የገባር ሥርዓት በወላይታ ከ1887-1967)

 የወላይታ ህዝብ በታሪኩ በሦስት ስርወ መንግሥታት 50 ነገስታታ ተፈራርቆ አስተዳድረውታል፡፡ እነዚህም የወላይታ ማላ፣የአሩጂያና የወላይታ ትግሬ ስርወ  መንግስታት ሲሆኑ የወላይታ ህዝብ ከሁለት አብይ ጎሳዎች ማለትም ማላና ዶጋላ የሚመዘዙ ከ120 በላይ ጎሳዎች በውስጡ ይገኛሉ፡፡ የወላይታ መንግሥታዊ መዋቅር ከላይ ከንጉሱ ጀምሮ እስከ ታችኛው የመንደር መሪ ድረስ የደረጀ መዋቅራዊ አደረጃጀት ያለው ሲሆን በዘመኑ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግርና አሠራር እንደነበረው ይገለጻል፡፡

በወላይታ በሶስቱ ስርወ መንግሥታታ የነገሱ ነገስታት ከዚህ በታች የተዘረዘሩ ናቸው፡-

የመጀመርያው የወላይታ ማላ ዘረግንድ ነገስታት

  1. ካዎ ቢቶ
  2. ካዎ ቢዲንቶ
  3. ካዎ ሃንሴ
  4. ካዎ ሃጢዬ
  5. ካዎ ሃጤ
  6. ካዎ ዋርዴ
  7. ካዎ ዋዳ
  8. ካዎ ሳጋዳ
  9. ካዎ ቡሬ
  10. ካዎ ሃሩሮ
  11. ካዎ ሃላሌ

ቀደምት የሀሩጂያ ነገሥታት

  1. ካዎ ባዳ
  2. ካዎ ዳዲላ
  3. ካዎ ባዲግዲላ
  4. ካዎ ባርቺ ጎዲራ
  5. ካዎ ባዲያ(ባዴ)
  6. ካዎ ባየዋ
  7. ካዎ ቡራና
  8. ካዎ ጎንጋ
  9. ካዎ ዳንጉላ
  10. ካዎ ዳሞታ

ሁለተኛው የወላይታ ማላ ዘረግንድ ነገሥታት

  1. ካዎ ሳኔ
  2. ካዎ ሳቦሬ
  3. ካዎ ሳሞሬ
  4. ካዎ ሳጉሎ
  5. ካዎ ሳኦላ
  6. ካዎ ሳሊሞና
  7. ካዎ ሳሜ
  8. ካዎ ሳቴ
  9. ካዎ ዛቴ
  10. ካዎ ሳቴ ሞቶለሮቄ
  11. ካዎ ሳቴ ሞቶሎሜ
  12. ካዎ ታላሜ
  13. ካዎ ሞስካ
  14. ካዎ ሞቴ
  15. ካዎ ኦቼ
  16. ካዎ ላቼ

የወላይታ ትግሬ ዘረግንድ ነገሥታት

  1. ካዎ ሚካኤል(ሚሄላ) 1560-1585
  2. ካዎ ግርማ(ጉሩማ) ከ1585-1610
  3. ካዎ አዛኝ(ጋዛነ) 1610-1635
  4. ካዎ አዳዬ  1635-1660
  5. ካዎ ኮቴ    1660-1685
  6. ካዎ ሊባና  1685-1710
  7. ካዎ ቱቤ   1710-1748
  8. ካዎ ሳና  1748-1777
  9. ካዎ ኦጋቶ 1777-1811
  10. ካዎ አማዶ 1811-1830
  11. ካዎ ዳሞቴ  1839-1848
  12. ካዎ ጎቤ  1848-1890
  13. ካዎ ጦና  1890-1904 (ምንጭ፡-ፋንጮ ፋንታና ኢዮብ አጫ፡፡የወላይታ ህዝብ ታሪክ እስከ 1966)