የካቲት 13/2015 ዓ/ም
በዘንድሮ በግማሽ በጀት ዓመት ለ5 ሺ 549 ዜጎች በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ፕሮግራም የስራ ዕድል እንደተፈጠረ ተገለጸ ።
በዛሬው ዕለት በወላይታ ሶዶ ከተማ የደቡብ ክልል የ2015 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት የከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም /UIIDP/ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል ።
በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ባስተላለፉት መልዕክት ስኬታማ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ በተሰራበት ማግስት የተካሄድ መድረክ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስትር በግማሽ ዓመቱ ባደረገው የአፈጻጸም ግምገማ የደቡብ ክልል ከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ቢሮ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን ለዚህ ደረጃ የተጉ አመራሮችና መዋቅሮችን አመስግነዋል ።
በግማሽ ዓመቱ በከተሞች ሁለንተናዊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል ።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይልማ ሱንታ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ዘንድሮ የሚጠናቀቅበት ዓመት በመሆኑ በቀሪ ወራት በፕሮግራሙ በሚሰሩ ተግባራት ላይ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል ።
በግማሽ ዓመት አፈጻጸሙ 5 ሺ 549 ዜጎች በፕሮግራሙ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ዳታ ተናግረዋል ።
የስራ ዕድሉ ከተፈጠረላቸው መካከልም 50%ቱ ሴቶች መሆናቸውን ነው አቶ ዳምጤ አክለው የገለጹት ።
አቶ ዳምጤ በበጀት ዓመቱ በUIDP 1.7 ቢሊዮን ብር በፕሮግራሙ ተመድቦ ወደ ስራ እንደተገባና 216 ሚሊዮን 969 ሺ 462 ብር ስራ ላይ እንደዋለ አስታውቀዋል ።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በከተሞች የመሬት ፋይል ማኔጅመንት፣ ምዝገባና አስተዳደር ተግባራት በአግባቡ ባለመስራታቸው የባለጉዳዮች መጉላላት መኖሩን ተናግረዋል ።
የተዛማች መዋጮ በወቅቱ ያለማስገባትና ከግዥ ስርዓት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ተሳታፊዎች ሀሳብ ተሰጥተዋል ።
በመድረኩ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የከተሞች ከንቲባዎችና የስትሪንግ ኮሚቴው አባላት ተሳትፈዋል ። የከተማ ልማትና ኮ/ቢ/ኮ
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza