"የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተልዕኮ የዕለት ጉርስ ከመሸፈን ባሻገር ሀብት በመፍጠር ላይ የተመሠረተና ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብና ለሀገር የሚበቃ ተልዕኮ ነው" የኢፌዴሪ የሥራና ክሂሎት ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለ4ኛ ዙር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች የሚሰጠው ሀገር አቀፍ ስልጠና በወላይታ ሶዶ ከተማ ተጀምሯል።
ወላይታ ሶዶ፣ የካቲት 14/2015 (ወ/ዞ/መ/ኮ/ጉ/መምሪያ) የኢፌዴሪ የሥራና ክሂሎት ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በቪርቿል(ዙም ቴክኖሎጂ) ለሠልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክታቸው የሠልጣኞች ተልዕኮ የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ሳይሆን ሀብት በመፍጠር ላይ የተመሠረተና ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብና ለሀገር የሚበቃ ተልዕኮ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ወ/ሮ ሙፈሪያት አክለውም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ማጠናከርና ማስፋት የወደፊት የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስንና ሀገራችን ያለመችውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማምጣት ሚናው ከፍተኛ ነው ብለው ትኩረት በተሰጣቸው የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የቱሪዝም የማዕድን፣ የሰው ኃይል ልማትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ አጠናክሮ ለመቀጠል ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ባንኩ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘንድ የሚታዩ ማነቆዎችን የዕውቀትና የዝግጁነት ችግሮችን ለመፍታት በማሰብ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሠልጣኞች ሥልጠና በማዘጋጀቱ ማኔጅመንቱንና ዶክተር ዮሐንስን አመስግነው የሠልጣኞች ወላጆች ልጆቻቸውን በመደገፍና ሠልጣኞችም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመጋፈጥና ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር በሥልጠናው የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር እንዲያሳዩ አሳስበዋል ሚንትሯ።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ለሠልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክታቸው ሠልጣኞች የጀመሩትን ሥልጠና በቁርጠኝነት እንዲያጠናቅቁና በሠለጠኑት ዕውቀት የቢዝነስ ዕቅድ በማዘጋጀት ባንኩ የሚያቀርበውን የሊዝ ፋይናንስ ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የግል ጥረትና ቁርጠኝነት እንደሚያሻቸው ተናግረው የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ለማለፍ ሥልጠናው አቅም እንደሚሆናቸውም ገልጸዋል።
በዕውቀትና በገንዘብ ዕጥረት ምክንያት ሥራ መፍጠር ላልቻሉ ወጣቶችና አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አንቀሳቃሾች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እየሠራ ያለው ተግባር ፋና ወጊ ነው በማለት ሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት በኢኮኖሚ፣ በትምህርት እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ተጠቃሚ ያልሆኑ ወገኖቻችንን ተጠቃሚ ለማድረግ አሠራራቸውን ተደራሽ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው የልማት ባንክ ላደረገው አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
ሠልጣኞች በሚሠሩት ሥራ በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን እንዳለባቸው አሳስበው በሥልጠናውና በቢዝነስ ዕቅዳቸው መሠረት የመሥሪያ ቦታ ለሚጠይቁ መንግስት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ዶክተር ዮሐንስ አያሌው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕረዚዳንት የአራተኛ ዙር ሥልጠናውን ልዩ የሚያደርገው ከዚህ ቀደም ሥልጠናው ያልተዳረሰባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና የትግራይ ክልሎችና ሌሎች አካባቢዎች እንዲሳተፉ መደረጉ ነው ብለው ሥልጠናው በ95 ማዕከላት እና በ57 ከተሞች የሚሰጥ ሲሆን ለዚህ ዙር ከተመዘገቡ 435ሺ ተመዝጋቢዎች 112 ሺ ተሳታፊ እንደሆኑ በቪርቿል ቴክኖሎጂ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ገልጸዋል።
እስከ ሶስተኛ ሥልጠናውን ለወሰዱ ከ33 ሺህ በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የሊዝ ካፒታል ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት ፕረዚዳንቱ።
አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች
የሥራ ዕድልና የገበያ አማራጭ በመፍጠር ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ያሉት ዶክተር ዮሐንስ ሠልጣኞች በሚሰጣቸው ሥልጠና ታግዘው ካፒታል በማምረት ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና የዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ተመስገን ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሀገራችን የወጣቶች ሀገር በመሆኗ ተስፋ ያላት ሀገር ነች ብለው እያንዳንዱ ዜጋ ሥራ ለመፍጠር ዝግጁ እንዲሆን አሳስበዋል።
ለወጣቱ ሥራ ዕድል መፈጠር ስጋት የሆነው የሥራ ፍላጎትና ተነሳሽነት አለመኖር በአጠቃላይ የሥራ ባህል ችግር መቀረፍ እንዳለበት ተናግረው ባንኩ ያመቻቸውን ዕድል ወጣቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ምክር ለግሰዋል።
በኢትዮጵያ የልማት ባንክ የወላይታ ሶዶ ዲስትርክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን ሳውል ባንኩ የአሠራር ሪፎርም በማድረግ በሽርክና ወይም በአክሲዮን ተደራጅተው ብድር ለሚጠይቁ ሁሉን ነገር ማመቻቸቱን ገልጸው ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው የሥራ ዕድል ላላገኙና ራዕይ እያላቸው በገንዘብ አቅም ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ላልቻሉ ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ዲስትርክቱ በሠጠው ሥልጠና እስከ ሶስተኛ ዙር ሠልጥነው ሴርቴፍኬት ከወሰዱ 3,350 ሰልጣኞች 450 የቢዝነስ ዕቅድ ያቀረቡ ተጠቃሚዎች ከ870 ሚሊዮን ብር በላይ ባንኩ ብድር ማቅረብ መቻሉን አስረድተው ሠልጣኞች እስከመጨረሻው በቁርጠኝነት በሥልጠናው እንዲሳተፉ አሳስበዋል።
በአራተኛው ዙር ዲስትርክቱ ከመዘገባቸው ከ24 ሺህ 500 በላይ ሠልጣኞች በዚህ ዙር ከ6 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች በአምስት ማዕከላት እንደሚሰጥም ገልጸዋል አቶ ሰሎሞን።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም የዕውቀትና የገንዘብ ዕጥረት በመቅረፍ ብቁ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ እና አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።
ሥልጠናው በቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ በፋይናንስ ሒሳብ አስተዳደር፣ በንግድ ሥራ አመራር፣ በገበያ ጥናትና ቢዝነስ ቅኝት አስተዳደር፣ በሰው ሀብት አስተዳደር እንዲሁም በግብይት አመራርና ሊዝ ፋይናንስ አሠራር ዙሪያ ከየካቲት 14-18/2015 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚሰጥም ታውቋል።
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza