ጠ/ሚ ዐቢይ የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፈቱ
ወላይታ ሶዶ፣ ሚያዝያ 23/2015 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት መርቀው ከፈቱ።
በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር በጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ አመካኝነት ከተፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ዳርቻ የሚገኘው የሀላላ ካብ በ'ገበታ ለሀገር' ኮይሻ ኮሪደር ፕሮጀክት አካል በሆነው ሃላላ ኬላ ሪዞርት ውስጥ ተካቶ የለማ ድንቅ የቱሪስት መስህብ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀላላ ኬላ ሪዞርት ከመዝናኛ ስፍራነቱ በተጨማሪ ታሪካዊና ባህላዊ ሙዚየሞችና የምርምር ማዕከላትን ያካተተ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የዳውሮ ዞን ለአይን የሚማርኩ መልከዓ ምድር፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ባለቤት ስለመሆኑም አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ለብዙ ስራዎች አእምሯችሁ እንዲከፈት የህዝብና አካባቢ ሰላም በእጅጉ በሚገኝበት የዳውሮ ዞን በመምጣት አዳዲስ ሀሳቦችን ለማፍለቅና ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሐላላ ኬላ ሪዞርት እንዲጎበኙም ጥሪ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሸትን በማለባበስ እውነት ማድረግ እንደማይቻልና ውሸትን ቀባብቶ እውነት ለማስመሰል መሞከር እንደ ሐላላ ኬላ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለመፍጠር አያስችልም ሲሉም አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊት የብዙ ባህልና ቋንቋዎች መገኛ ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ብዘኃነት እንደራስ መቀበልን መለማመድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ሀገር ናት የምንለው በባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም እጅግ ማራኪ ሕብረ ብሔራዊ ቀለማትን በውስጧ የያዘች ሀገር መሆኗን መረዳት ያስፈልጋል፤ በዚህም አንዱ አካባቢ ከሌላው የተለየ የራሱ ተፈጥሯዊ ገፀ በረከቶችን የያዘ በመሆኑ በአግባቡ በማልማት መጠቀም እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በመጨረሻም የዳውሮ ማህበረሰብ የሐላላ ኬላ ሪዞርት እንደቀደሙ አባቶች ቅርስ በመጠበቅ ለትውልድ እንዲያሸጋግርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል ።
በሌላ በኩል ደግሞ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በክላስተር ተከፋፍሎ በተሰራው የሀላላ ኬላ ሪዞርት ፕሮጀክት የልማት ስራው አካባቢዎች ካላቸው ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ጋር ተጣጥሞ መከናወኑ አካባቢውን ይበልጥ ሳቢ እንዳደረገው በምርቃት ወቅት ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ሐላላ ኬላ ሪዞርት የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ አካባቢው በደቡብ ክልል ስር የነበረ መሆኑን አስታውሰው አሁን ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አካል ሆኖ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ከሐላላ ኬላ ታሪካዊ መስህብ በተጨማሪ የዳውሮ ዞን በባህል ዘርፍም ማራኪ ጸጋዎችን የተላበሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ናቸው።
ከሦስት ዓመታት በፊት ከአካባቢው ማህበረሰበብ ውጪ ይህንን ስፍራ ብዙዎች ያውቁታል የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አሁን ለምረቃ የበቃው ሀላላ ኬላ ሪዞርት እንደ ሀገር ትልቅ የቱሪዝም አቅም የተፈጠረበት ስፍራ ነው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው እንደ ቱሪዝም ያሉ መስኮች ተፈላጊውን ሀገራዊ ጠቀሜታ እንዳይሰጡ ወደ ኋላ ከሚጎትቱ ጉዳዮች መካከል የሰላም እጦት አንዱ መሆኑን ገልጸው የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው ሀላላ ኬላ ሪዞርት ቱሪዝም ዋና የገቢ ምንጭ መሆኑን ያሳየ ፕሮጀክት ሆኖ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ሃላላ ኬላን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱት የሰላም ስምምነቱን ለመገምገም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተገናኙበትን ታሪካዊ እለት በመጥቀስ አሁን ግን ሪዞርቱ በተሟላ መልኩ ተጠናቅቆ መመልከታቸውን በበጎ እንደተመለከቱት ገልጸዋል።
የቱሪዝም ፕሮጀክቶችን ማስፋት ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አንጻር እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሪቱ ያላትን አቅም በመረዳት የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ ቀርቧል ስል ዋልታ ዘግቧል ።
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza