የወላይታ ሶፊያ ስርዓት አጭር ቅኝት
ሀገራችን የበርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል ባለቤት ናት፡፡ የሶፊያ ስርዓት በወላይታ ብሔር የወንድ ልጅ ግርዛት፣ በጦር ሜዳ ጠላት የመግደል፣ በአደን አንበሳ፣ ነብር፣ ጎሽ፣ ዝሆንና የመሳሰሉትን የዱር እንስሳት ግዳይ የመጣል፤ የሴት ልጅ የሙሽርነትና የአራስነት ወቅት ማሳረጊያ የደስታ ብስራት ክዋኔ ነው፡፡ በሂደቱ የስርዓቱ ተዋንያን አጊጤውና አምረው በዘመድ አዝማዶቻቸው፣ በጓደኞቻቸውና በጎረቤቶቻቸው ታጅበው በአከባቢያቸው ወደሚገኝ ታዋቂ ገበያ በመሄድ ዝናቸውንና ገድላቸውን፣ ስኬታቸውን ከአንድ የሕይወት ምዕራፍ ወደ ሌላኛው ጤናማ ሽግግራቸውን በደስታ እያወጉ “parssuwaa”/ቦርዴ በመጠጣት እየተዝናኑ የሚያሳልፉበት ስርዓት ነው የሶፊያ ስርዓት፡፡ በሌላ አነጋገር የሶፊያ ስርዓት ገድልን፣ ማህበራዊ ደረጃን፣ ስኬትንና ከአንድ የሕይወት እርከን ወደሌላኛው ጤናማ ሽግግር ላይ በሁለቱም ጾታዎች የሚከወን ደስታዬን እወቁልኝ /ተጋሩልኝ መድረክ ነው፡፡
1. የወንዶች የሶፊያ ስርዓት
የወንዶች የሶፊያ ስርዓት በጦር ሜዳ ጠላት የገደሉ ወንዶች ለጀግንነት ማብሰሪነት Beleca-Dunddaa ከብር የተሰራ ቀለበት መሰል ጌጥ በጆሮአቸው ካንጠለጠሉ በኋላ የሶፊያ ስርዓት ለመፈጸም ቀጠሮ በማስያዝ በአከባቢው ወደሚገኝ ታዋቂ ገበያ ዘመዶቹ፣ ጓደኞቹ፣ ጎረቤቶቹና ከዚህ ቀደም መሰል ጀብድ የፈጸሙ ሰዎች እንዲገኙ በመጋበዝ በገበያው “shidhdhaa”/ከእንሰት ኮባ በተሰራው ባህላዊ አግዳሚ ወንበር ላይ ታዳሚዎች እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡
የሶፊያ ስርዓት የሚፈጸመው ግለሰብ ከታዳሚዎቹ መካከል እንዲቀመጥ ተደርጎ ለታዳሚዎች ቦርዴ (parssuwaa) እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ታዳሚዎቹ ቦርዴ እየጠጡ ይጨፍራሉ፤ ይዘፍናሉ፤ ያቅራራሉ፤ ይሸልላሉ፡፡ በዕለቱ ከታዳሚዎች መካከል በዕድሜ አንጋፋና ከዚህ በፊት ስርዓቱን ያከናወነ ሽማግሌ ተመርጦ እንዲመርቅ ይደረጋል፡፡ ሽማግሌው ዓመቱ የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆን በመመኘት ይመርቃቸዋል፡፡ በዚህ መልክ እየተዝናኑ ያመሹና የስርዓቱ ፍጻሜ ይሆናል፡፡
ከፍ ብሉ እንደተጠቀሰው ወንዶች በአደን ከባድ የዱር እንስሳትን መግደል፣ ባህላዊ የዳኝነት ሹመት ማግኘት እና ግርዛት በሶፌ ስርዓት ይታጀባል፡፡ በአደን ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የዱር እንስሳትን ግዳይ የመጣል ሶፊያ ስርዓት በጦነት ግዳይ ከፈፀመው ሰው ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ሲሆን ልዩነቱ ግን በዚህን ጊዜ የሚታደሙት አብዛኞቹ የአንበሳ ወይም የነብር ግዳይ የፈጸሙ ግለሰቦች ወይም አንበሳና ነብር ከገደሉ ቤተሰቦች የተወለዱ ሰዎች መሆናቸው ነው፡፡
በነባሩ የወላይታ አስተዳደር ወቅት ባህላዊ አስተዳደር (Daannatettaa) ማዕረግ የተመረጡ ሰዎች ማዕረጉን ተቀብለው ወደ አከባቢያቸው ሲመለሱ በፈረስ ታጅበው ወደ ገበያ በመግባት የሶፊያ ስርዓት የሚፈጽሙ ሲሆን በሥርዓቱ ቀደም ሲል የባህላዊ አስተዳደር (Daannatettaa) ማዕረግ ያገኙ ቤተሰብ የሚያከናውኑት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ማዕረጉን የተቀበለው ግለሰብ አከባቢ የሚገኘው ህብረተሰብ ወደ ገበያ በመውጣት “እንኳን ደስ ያለህ! Daannatettaa ያዳብርልህ!” በማለት የሚመርቁ ሲሆን የብሔሩ ሽማግሌዎች ደግሞ በማዕረጉ የተመረጠው ሰው ለህብረተሰቡ ትክክለኛ ፍትህ እንዲሰጥና ሕዝብን እንዳይበድል ምክር ይለግሳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሥራ ዘመኑ የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆን ምኞታቸውን በመግለጽ ይመርቁታልም፡፡ ተሿሚው ግለሰብም “አሜን” በማለት አጸፋውን ይሰጣቸዋል፡፡
በወላይታ ብሔር ዘንድ ወጣቶች ከተገረዙ በኋላ በወላጆች ዘንድ በጥሩ እንክብካቤ ተቀልበው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ገበያ ሲወጡ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሶፊያ ስርዓት የሚፈጽሙ ሲሆን ወጣቶች የሶፊያ ስርዓት ፈጻሚውን ባገኙበት ቦታ ምግብና ቦርዴ በመጋበዝ የሚያዝናኑበትና “እንኳን ከጓደኞችህ ጋር በሰላም ተቀላቀልክ!” በማለት የሚመርቁበት ስርዓት ነው፡፡
የሴቶች የሶፊያ ስርዓት
አንድ ሺህ እና ከዛ በላይ ከብቶችን ያረባች ሴት ለሀብቷ ብስራት (ግሟ ስርዓት) ለመፈጸም በመሰል ሴቶች ታጅባ በቅሎ በመጋለብ ነው በገበያ የሶፊያ ስርዓት የምታበስረው፡፡ የመዝናናቱ ስርዓት ከወንዶቹ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን የሶፊያ ስርዓቱ ሲጠናቀቅ በቅሎ በመጋለብ በአጃቢዎቿ ታጅባ ወደቤቷ ትመለሳለች፡፡
የአራስ ጊዜዋን ያጠናቀቀች ሴት የሶፊያ ስርዓትን ለመፈጸም አቅም ያላት ከሆነች ከአራስ ቤት ከመውጣቷ አስቀድማ ባህላዊ ልብስ ገዝታ ካሟላች በኋላ የሶፊያ ስርዓት ትፈጽማለች፡፡ የአራስነት ወቅት ማሳረጊየ ሶፊያ ስርዓት ያለመፈጸም በአንጻራዊነት ባህላዊ ጫና አያስከትልም፡፡ የሶፊያ ስርዓትን መፈጸም ክብርና ዝናን ከማትረፍም በተጨማሪ ስርዓቱን የፈጸሙ ሰዎችና በባህሉ በማናቸውም ማህበራዋ ኑሮ የተከበሩና ባለዝና እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
ከወንዶች የሶፊያ ስርዓት አውዶች ማለትም ጦርነትና አደን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን በመሆኑ የሶፊያ ስርዓታቸውም በአብዛኛው የከሰመ ሲሆን የሴቶች የሶፊያ ስርዓት እስከዛሬ ድረስ የቀደምት ወላይታ አሻራ በአንጻራዊነት ባልደበዘዘ መልኩ በሚስተዋልበት በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
Copyrights 2019. . All Rights Reserved.
Developed by SNNPRS-SITB & SNNPRS-wza